2022-12-04 15:27:30
#ኅዳር_26_ዕረፍቱ_ለአቡነ_ሀብተማርያም_ጻድቅ
#ልደቱ
አምስቱን መቅሰፍቶች የማስወገድ ስልጣን የተሰጠው ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያም የነበረበት ዘመን 1486 ዓ.ም ንጉስ እስክንድር በነገሰበት ጊዜ ነው፡፡ አባቱ ፍሬ ቡሩክ እናቱ ዮስቴና ይባላሉ፡፡ ፍሬ ቡሩክና ዮስቴና በህገ እግዚአብሔር በሃይማኖት በትሩፋት በምግባር ፀንተው የሚኖሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡
የፃዲቁ አቡነ ሀብተ ማርያም እናት ቅድስት ዮስቴና ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያምን ከመውለዷ በፊት ሰው ሁሉ ዓለሙን ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል የሚለውን የወንጌል ቃል ተረድታ መንና ወደ በረሃ ሄደች፡፡ በበረሃ ውስጥም ከሰው ተለይቶ የሚኖር ባህታዊ በዋሻ ውስጥ አገኘች፣ ''የመጣሁት ለምነና ነው ጌታ በወንጌሉ እርፍን ይዞ ወደ ኋላ የሚያርስ የለም እንዳለ ወደ ዓለም አልመለሰም'' አለችው፡፡ (ሉቃ 9፣62) ይህም ባህታዊ ''ምናኔ ምንኩስና ለአንቺ አልተፈቀደልሽም ከህጋዊው ባልሽ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ ይተርፋል በፀሎቱም ብዙዎቹን ይጠቅማል እንደ መልአክትም ክንፈ ጸጋ ተሰጥቶታል'' በማለት ነገራት፡፡ ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባህታዊ ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች ''የፈጣሪዬ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ'' ብላ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
ጥቂት ጊዜያት ከቆየች በኋላ ግንቦት 26 ቀን ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያም ተወለደ፡፡ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታ ሆነ 40 ቀን ሞልቶት በተጠመቀ ዕለትም ሀብተማርያም ተብሎ ተሰየመ፡፡ ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያም በፈሪሃ እግዚአብሔር በትምህርት አደገ፡፡
ከዕለታት በአንድ ቀን ካህናቱ በቤተክርስቲያን ምህላ ሲያደርሱ ''እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ'' እያሉ ሲፀልዩ ሰምቶ በልቡናው ይህች ፀሎት በጣም ጥሩና መልካም ፀሎት ናት አለ በዚህ ፀሎት ከዓለም አሳችነት ከገሃነም እሳት እንድንባት ዘንድ አውቃለሁ የንስሐ መንገድ ናት ብሎ ተናገረ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አባታችን አቡነ ሀብተማርያም በዚህች ፀሎት ተጠምዶ በጾምና በፀሎት በስደት የሚኖር ሆነ፡፡
#የአገልግሎት_ጥሪው
አባቱ ፍሬ ብሩክ አቡነ ሀብተማርያምን የበግ ጠባቂ አደረገው እግዚአብሔር ግን በኋላ ለብዙዎች ስውራን ቅዱሳንና በዓለም ለሚኖሩ ምዕመናን በጎች ጠባቂ ያደርገው ዘንድ ወዶ መርጦታልና ያ ቀን እስኪደርስ ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቡነ ሀብተማርያምን ይጠብቀው ነበር፡፡
አባታችን አቡነ ሀብተማርያም ከአባቱ አጠገብ ተኝቶ ሳለ ‹‹ሀብተማርያም ሀብተማርያም›› የሚል ድምጽ በሌሊት ከሰማይ መጣ፡፡ አባቱ በአጠገቡ ተኝቶ ስለነበረ የጠራው መስሎት አባቴ ሆይ አለሁ ሲል መለሰ ከዚህ በፊት ቃል ከሰማይ ጠርቶት አያውቅም ነበርና እንደ ሳሙኤል ጌታዬ ባሪያህ ይሰማሃል ተናገር አለ፡፡ (ሳሙ3፤3) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አናገረው፡፡
ከዚህም በኋላ አባቱ ከሀገሪቱ ታላላቅ ሰዎች አንዷን እጮኛ አጨለትና ታገባለህ አለው አባታችን አቡነ ሀብተማርያም አባቴ ሆይ እኔ ራሴን ለክርስቶስ በድንግልና ለመኖር አጭቻለሁ ተራክቦዬም ቃለ ወንጌልን መስማት እንጂ ሌላ አይደለምና ለምን እንዲህ ትለኛለህ አለ፡፡ አባቱም ያለ አቡነ ሀብተማርያምፈቃድ ሙሽራይቱን ለማምጣት ሄደ፡፡ አባታችን አቡነ ሀብተማርያምም ሀገር ጥሎ ለመሰደድ ከቤት ተደብቆ ወጣ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በመብረቅ አምሳል አባቱን ገሰፀው በዚህ ድንጋጤ ምክንያት የስጋ አባቱ ከዚህ ኃላፊ ዓለም አረፈ፡፡
#አገልግሎቱና_ተአምራቱ
አባታችን አቡነ ሀብተማርያምም የአባቱን እረፍት ሳያይ አፋር ወደምትባል ሀገር ወደ አሰቦት አቡነ ሳሙኤል ገዳም ሄደ አባ ሳሙኤል ከሚባሉ ደግ መነኩሴ ቦታ ገብቶ ኖረ፡፡ በዚያም ገዳም ውሃ በመቅዳት እንጨት በመስበር፣ ልብስ በማጠብ እህል በመፍጨት አበው መነኮሳትን ሲያገለግል ኖረ፡፡ በአባታችን ላይ መነኮሳት ተቆጥተው ሲነሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በገሃድ ተገልፃ ትገስፃቸውም ነበር፡፡
በዚህ አገልግሎት ላይ ሳለ ገዳሙ ካለበት ተራራ ላይ ወደ በረሃ ወርዶ ውሃ ቀድቶ ተሸክሞ ሲመለስ ውሃውን በእንስራ እንደተሸከመ እግሩን አደናቀፈው፡፡ የቀዳው ውሃ ሊደፋበትና እንስራውም ሊሰበርበት ሲል ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አድነኝ ትወድቅ ዘንድ አትተዋት ብሎ ፀለየ፡፡ ይህን ብሎ በተናገረ ጊዜ የውሃዋ እንስራ ሳትወድቅ ቆመች እጅም ሳይነካት ተመልሳ በትከሻው ላይ ተቀመጠች አባ ሳሙኤልም ይከተሉት ነበርና ይህን ጽኑ ተዓምር አይተው አደነቁ፡፡ (ማር. 9፡23)
እንዲሁ ከዕለታት በአንድ ቀን በሌሊት መብራት ለአባ ሳሙኤል እያበራ ሳለ መብራቱ ከእጁ ወድቆ ጠፋ፡፡ ስለ መምህሩ ስለ አባ ሳሙኤል ቁጣ፣ ፍራቻ፣ ታላቅ ድንጋጤ ደንግጦ ፈጥኖ ባነሳው ጊዜ በእግዚአብሔር ተዓምር ራሱ በራ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይህን ተዓምራት አይተው የዚህ ቅዱስ ልጅ የዓለም ሁሉ የጥበብ መብራት ይሆናል ሲሉ ትንቢት ተናገሩ፡፡ በዚህችም ገዳም 12 ዓመት ከትህትና ጋር እየታዘዘ ቤተክርስቲያንን እያገለገለ ኖረ፡፡
ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያም ከአባ ሳሙኤል ገዳም ወጥቶ እለ አድባር ወደ ተባለ ገዳም ሄደ፡፡ ከአባ መልኬጼዴቅ እጅ የምንኩስናን ስርዓት ተቀበለ፡፡ ከዚያም በመቀጠል በጥልቅ ባህር ገብቶ 150 መዝሙረ ዳዊትና አራቱን ወንጌልና ሌሎች የፀሎት መጽሐፍትን እየፀለየ አምስት መቶ ጊዜ ይሰግድ ነበር፡፡ እህል መብላትን ትቶ እንደ በረሃ ዋልያ ቅጠል መብላት ጀመረ፡፡ አርባ ቀን የሚጾምበት ጊዜና ሰማንያ ቀንም የሚጾምበት ቀን ነበር፡፡ ቅጠልም ቢሆን እህል ቀዝቃዛ ወይም ምንም አይቀምስም ነበር፡፡ ፊቱም እንደ ንጋት ኮከብ ያበራ ነበር፡፡አራቱን ወንጌላት ይጸልያል።
አባታችን አቡነ ሀብተማርያም እንዲህ ባለ ስራ ላይ ሳለ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ እርሱ መጥቶ:- ''ልጄ ሀብተማርያም የምለምንህ ነገር አለና እሺ በለኝ በሀገሬ ላይ የታዘዙ 5 መቅሰፍቶች አሉ የአንተም አጽም በውስጡ የተቀበረ እንደሆነ አጥንቴ የተቀበረባት ሀገሬ ከነዚህ መቅሰፍታት ትድናለች ከተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበር ቃል ኪዳን ግባልኝ'' አለው፡፡
በአቡነ ሀብተማርያም አጽም የራቁት መቅሰቶች እነሱም፡- 1. መብረቅ፣ 2. ቸነፈር፣ 3. ረሃብ፣ 4. ወረርሽኝ፣ 5. የእሳት ቃጠሎ ናቸው፡፡
#ዕረፍቱ
ከዚህም በኋላ መልአኩ ለአቡነ ሀብተ ማርያም ክብሯ እንደ ጽርሐ አርያም የሆነች ቦታን አሳያቸው፡፡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውም ቅዱሳን መላእክት በውስጧ ተድላ ደስታ ያደርጉባት ነበር፡፡ አባታችንም መልአኩን ‹‹ይህች ክብሯ ፍጹም የሆነችን ቦታ ማን ትባላለች በውስጧ ለመኖር በእጅጉ ወድጃለሁና›› ብለው ሲጠይቁት መልአኩም ‹‹ይህችማ ቦታ የአባትህ የተክለ ሃይማኖት አጽም ያረፈባት ደብረ ሊባኖስ ናት፤ ከእርሱም ጋር በክብር እስክትነሣ ድረስ በውስጧ ትቀበርባት ዘንድ ለአንተም ተሰጥታሃለችና ደስ ይበልህ፡፡ አባትህም እንደ ኢየሩሳሌም እንደትሆንለት ቃልኪዳን ተቀብሎባታል›› አላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ የአባታችን የአቡነ ሀብተ ማርያም ዕለተ ዕረፍታቸው በደረሰ ጊዜ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በታላቅ ምስጋና ወደ ብፁዕ አባታችን መጥቶ ‹‹ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሆይ! ዛሬ ወደ አንተ የመጣሁት ከድካም ወደ ዕረፍት እወስድህ ዘንድ ነው፣ ሰባት የጽድቅ አክሊሎችን አዘጋጅልሃለሁ›› በማለት ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ጌታችን አባታችንን ሦስት ጊዜ ሳማቸው፡፡ ያን ጊዜም ከመድኃኔዓለም ጣዕም ፍቅር የተነሣ ኅዳር 26 ቅድስት ነፍሳቸው ከሥጋው ተለየች፡፡
የጻድቁ አባታችን በረከት ረድኤት ከእኛ ጋር ይሁን!!!!
21 viewsbisrat, 12:27