2022-12-28 21:01:44
#ታህሳስ_20_ዕረፍቱ_ለነቢዩ_ሐጌ
ሐጌ ማለት በዓል፣ ደስታ ማለት ነው፡፡ የስሙ ትርጓሜ ሕዝቡ ከምርኮ የሚመለሱ ስለኾነ ይኽን ደስታ የሚያስረዳ ነው፡፡
#ነቢዩ_ሐጌ_ማነው?
ነቢዩ ሐጌ ከ ፲፪ [12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ሲሆን የተወለደው በምርኮ በባቢሎን ሲኾን ትንቢቱን ሲናገር የ፸፭ [75 ዓመት ሽማግሌ ነበር፡፡ የእስራኤል ቅሪቶች ወደ ኢየሩሳሌም በዘሩባቤል አማካኝነት ሲመለሱ ነቢዩ ሐጌም ከተመለሱት ጋር አንዱ ነበር፡፡
በ፭፻፴፰ [538 ቅ.ል.ክ. ላይ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ አንድ አዋጅ አስነግሮ ነበር፡፡ አዋጁም አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ የሚፈቅድ ነበር /ዕዝራ ፩፡፩-፲፩/፡፡ በዚኽም መሠረት የቤተ መቅደሱን ሥራ በ፭፻፴፮ [536 ላይ የቤተ መቅደሱን ሥራ ዠምረዋል፡፡ ነገር ግን አይሁድ ወደ አገራቸው ሲገቡ አገራቸው ባድማ ኾና ስለነበር፣ የዘር ፍሬ በአገሩ ስላልነበረ፣ እንዲኹም በሌሎች ችግሮች ምክንያት ቤተ መቅደሱን መሥራት ትተው ወደየግላቸው ተግባር ተሰማርተው ነበር፡፡
በመኾኑም መንፈሳዊ ሕይወታቸው ዝሎ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ነቢዩ ሐጌንና ነቢዩ ዘካርያስን የላከበት ዋና ምክንያትም የተዠመረውን ቤተ መቅደስ እንዲያጠናቅቁት ለማሳሰብ ነበር፡፡ ነቢዩ ሐጌ በሚያገለግልበት ወራት የነበረው ንጉሥ ዘሩባቤል ሲኾን፤ በዚያ ሰዓት የነበረው ሊቀ ካህናት ደግሞ ኢያሱ ይባላል /፩፡፩/፡፡
#ትንቢተ_ሐጌ
በብሉይ ኪዳን በመጨረሻ የምናገኛቸው ሦስቱን መጻሕፍት ማለትም ትንቢተ ሐጌ፣ ትንቢተ ዘካርያስና ትንቢተ ሚልክያስ ከምርኮ በኋላ ስላለው ጊዜ እንዲኹም አይሁድ ከምርኮ እንዴት ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ በዚያ አንጻር ግን ደቂቀ አዳም ከዲያብሎስ ምርኮ እንደምን ወደ እግዚአብሔር እንደተመለሱ የሚያስረዱ ናቸው፡፡
ነቢዩ ሐጌ በእግዚአብሔር ሰዓት የእግዚአብሔር ሰው ኾኖ የተገኘ ነቢይ ነው፡፡ አገልግሎቱን በ፭፻፳ [520 ቅ.ል.ክ. ላይ ሲዠምር ጠንካራና ፬ ተከታታይ ስብከቶችን በመስጠት ነበር፡፡
ለሕዝቡ የቤተ መቅደሱ ሥራ እንደተቋረጠ ነገራቸው፤ ሕዝቡ ከቤተ እግዚአብሔር ይልቅ የራሳቸውን ቤት በመሸላለም እንደተሳቡ ገለጠላቸው፡፡ አራቱ ስብከቶቹ በአጭሩ እንደሚከተለው የቀረቡ ናቸው፡-
1. የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲያጠናቅቁት አሳሰባቸው /ምዕ. ፩/፡፡
2. የኹለተኛው ቤተ መቅደስ ክብር እንዴት እንደኾነ አስረዳቸው /፪፡፩-፱/፡፡
3. የመታዘዛቸው ውጤት የኾነ በረከትን እንደሚባረኩ ነገራቸው /፪፡፲-፲፱/፡፡
4. በመታዘዛቸው ምክንያት ሊመጣ ያለው በረከት እንዴት እንደኾነ አስታወቃቸው /፪፡፳- ፳፫[23/፡፡
#እኛስ_ከዚኽ_ምን_እንማራለን?
መጽሐፉን በጥንቃቄ አንብበነው ከኾነ ቃሉ መጣ የሚለው “በነቢዩ በሐጌ እጅ” ነው የሚለው /፩፡፩፣ ፪፡፩፣ ፪፡፲/፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚመጣው በነቢያት አፍ ነው፤ እዚኽ ግን የተገለጠው በነቢዩ እጅ ነው፡፡ ምን ለማለት ነው? ጄሮም የተባለ የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ እንዲኽ ይላል፡- “እጆቻችንን ለመልካም ሥራ ስናነሣ ክርስቶስም በኹለንተናችን ላይ ይነግሣል፤ ዲያብሎስን ከእኛ ያርቅልናል፡፡ እጅ ሲባል መልካም ሥራን የሚያመለክት ነው፡፡ … እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን የሚመጣው ስለ ተናገርን አይደለም፤ መልካም ሥራን ስንሠራ እንጂ፡፡”
አይሁድ ቤተ መቅደሱን ላለመሥራት ሲያመካኙ የነበረው “ኢኮነ ጊዜሁ - ጊዜው ገና ነው” በማለት ነበር፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ብዙዎቻችን በዚኽ መንፈስ የተያዝንበት ዘመን ቢኖር አኹን፡፡ “ጊዜው ገና ነው፤ ቤተ መቅደሱን የምሠራበት ጊዜ አይደለም፤ ገና ወጣት ስለኾንኩ አኹን ወደ እግዚአብሔር የምቀርበብበት ዘመን አይደለም” እያልን እናመካኛለንና፡፡ ነገ በሕይወት ለመኖራችን ግን እርግጠኞች አይደለንም፡፡ እንኪያስ ሰባኪው እንዳለው የጭንቅ ቀን ሳይመጣ፣ በጕብዝናችን ወራት፣ አፈርም (ሥጋችን) ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ ፈጣሪያችንን እናስብ እንጂ በማመካኘት ጊዜአችንን አናጥፋ /መክ.፲፪፡ ፩፣፯/፡፡
በተራራው ስብከቱ ላይ ጌታ፡- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይኽም ኹሉ ይጨመርላችኋል” እንዳለን / ማቴ.፮፡፴፫/ በሕይወታችን ላይ እግዚአብሔር የማናስቀድም ከኾነ ግን ብዙ ብንዘራም የምናስገባው ጥቂት ነው፤ ብንበላም አንጠግብም፤ ብንጠጣም አንረካም፤ ብንለብስም አይሞቀንም፤ ደመወዛችንን ብንቀበልም በቀዳዳ ኪስ እንደማስቀመጥ ነው /ሐጌ.፩፡፮/፡፡ አዝመራውን በእርሻው ሳለ ባየነው ጊዜ ብዙ ቢመስለንም ወደ ቤታችን ሲገባ በረከት የለውም፤ ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ይነሣል (ይከለክላል)፤ ምድር የዘራንባትን አታበቅልም፤ የተከልንባትን አታጸድቅም፡፡ በአጭር ቃል በረከት ከእኛ ይርቃል /ሐጌ.፩፡፱-፲፩/፡፡
በወልድ ውሉድ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ተጠርተን ሳለ፣ በጥምቀት ከማይጠፋ ዘር ተቈጥረን ሳለ ምድራዊ ቤትን (ፈቃደ ሥጋን) ለመሥራት አማናዊው መቅደሳችንን (ፈቃደ ነፍሳችንን) የምንረሳ ከኾነ በዚኽ ምድር ከእኛ የባሰ ጐስቋላ ሰው የለም /ሐጌ.፩፡፲-፲፩/፡፡
ቤተ መቅደሱን (ፈቃደ ነፍሳችንን) የምንሠራ ከኾነ ግን እግዚአብሔር በረድኤቱ ከእኛ ጋር ይኾናል፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ ትበዛለች፡፡ “ቤተ እግዚአብሔርን ከሠራችሁበት ቀን ዠምሮ እኽሉን ወይኑን በአውድማ ትርፍርፍ ብሎ ታዩታላችሁ፤ በለሱን ሮማኑን ዘይቱን የሚያፈራውን እንጨት ኹሉ ከዛሬ ዠምሮ አበረክታለኹ” ሲል ይኽን ያመለክታል /ሐጌ.፪፡ ፳/፡፡
ይኽን እንድናደርግ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!!
29 viewsbisrat, 18:01