2023-01-11 20:21:33
የድንግል ማርያም የቅድስና ጠባያት 1)የንጽህና ህይወት
እመቤታችን ድንግል ማርያም ንጽህት ቅድስት ናት እመቤታችን ከጥንት አብሶ (ከውርስ ኃጢያት) ንጽህይት ነች ይህንንም ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን ገሞራንም በመሠልን ነበር” እንዳለት. ኢሳ.1:9 ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረ የእመቤታችን የማርያም ንፅህና ከመላእክትም ይበልጣል ብሏል በዚህም ምክንያት አምላክ ከእርሷ እንዲወለድ መረጣት ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስም ነስቶ ሰው ሆነ የፀሀይ መገኛም ስለሆነች ምስራቅ ተባለች፡፡
2.የትህትና
ትህትና ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ በድንግሊቱ ሕይወት ውስጥ ተገልጧል መልአኩ ወደእርሷ በመጣ ባበሠራትጊዜ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ…” ነበር ያለችው ሉቃ.1:38 በእርግጥም እርሷ ይህንን ያለችው እናቱም አገልጋዩም ስለሆነች ነው፡፡አምላክንም ከጸነሰች በኃላ ወደ ኤልሳቤጥ ዘንድ ሄደች መንፈስ ቅዱስም ለኤልሳቤጥ የእመቤታችንን ክብር በገለፀላት ጊዜ በትህትና “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆነኛል?”ብላለች ሉቃ143 እመቤታችን ወደኤልሳቤጥ የኄደችው አምላክን ከጸነስች በኃላ ነው በጣም አድካሚ ወደሆነው ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ የመጣቸው ፡፡ ከዚህ በኃላ ኤልሳቤጥም እስክተወልድ ድረስ ለሦስት ወራት ያህል በዚህ ተቀምጣለች፡፡ ሉቃ139-56፡፡ ለእርሷ የተሰጣት ድንቅ የሆነ ክብር ትህትናዋ ፈጽሞ አልቀነሰውም በፀሎቷም ጊዜ “የባሪያውን ትህትና ተመልክቶአልና… ”
በክብር የተሞላ የሥጋዌን ምስጢር ለማንም አለመናገሯ ደግሞ ሌላው ድንቅየ ትህትናዋ መገለጫ ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ማርያም በቤተመቅደስ የኖረች በቅስስናናበንፅህናነው፡፡አይሁድ ግን ከቤተመቅደስ እንድትወጣ በጠየቁ ጊዜ አልተቃወመችም እንደዚህም በአንድ ሰው ጠባቂነት ስር እንድትኖር በተደረገ ጊዜም አንዳችም የተቋውሞ አሳብ አላቀረበችም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አሰራር በድንግልና እናት እንድትሆን እግዚአብሔር ሲፈቅድ ሉቃ135 ሰፊ የውይይት አጀንዳ እንዲከፈት አልፈቀደችም ይልቁንም ባልተቀየረ ቃሏእንዲህ አለች እንጂ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ…” ሉቃ138 ይህን በማለቷ በመታዘዟም የእግዚአብሔር እናት ሆነች፡፡ እሜታችን ቅድስት ማርያም ወደ ግብጽ እንድትሰደድ በመልአኩ በኩል በታዘዘች ጊዜ በዝምታ ነበር የወረደችው፡፡ ከግብጽ ወደ ቅድስት ሀገር እንድትመለስ ይኸው ትእዛዝ ሲደርሳት በዝምታ ነበር የፈፀመችው፡፡ከቤተልሄም ወጥታ ወደ ናዝሬት በመሄድ በዚያ እንድትኖር በታዘዘች ጊዜም ጋር የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን ብላ ነበር የታዘዘችው፡፡እናታችን ያለምንም ውይይት በመታዘዝ ሕይወት ውስጥ ያለፈች የሰው ዘር ናት፡፡
3)የትዕግስት የጽናት ሕይወት
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆቿ በሞት የተለዩአት ገና የስምንት ዓመት ብላቴና ሳለች ስለሆነ ያደገችው ያለወላጅ ነው፡፡ይህ በመሆኑም ያለወላጅ የማደግን ችግር በጽናት ተቋቁማለች በቤተመቅደስ መኖርንም የጀመረችው ገና በሕፃንነት እድሜዋ በመሆኑ ብቸኝነትንም ተጋፍጣለች፡፡በአንድ ጠባቂ ሰው ጥላ ስር ለመኖር ከቤተመቅደስ ከወጣች በኃላም የድህነትን ህይወት ተቋቁማለች፡፡ “በዚህም የመውለጃዋ ወራት ደረሰ የበኩር ልጅዋንም ወለደች በመጠቅለያም ጠቀለለችው በእንግዶችም ማረፊያ ስፍራ ስላልነበረቸው በግርም አስተኛችው” ሉቃ27 ተብሎ እንደተጻፈ አንድያ ልጇን ክርስቶስንም ከወለደች በኃላ መከራን በጽናት ተቀብላለች በጠባቂዋ በዮሴፍ ቤት በነበረች ጊዜም የኃላፊነትን ቀንበር ተሸክማለች፡፡
ድንግል ማርያም ገና በ15 አመቷ ብላቴና ሳለች የግብጽን የደርሶ መልስ አድካሚ ጉዞ በጽናት ተወጥታለች፡፡ በዚያ ከልጇ ጋር ለሦስት አመት ከስድስት ወር በስስት ስትቀመጥ የግብፅ ጣኦታት በልጀዋ ፊት እየተሰበሩ ይወድቁ ስለነበር በትንቢተ ኢሳይያስ እንደተፃፈ ጣኦት አምላኪዎች ከአንዱ ከተማ ወደሌላው ከተማ ያሳድዷቸው ስለነበር ይህንንም በትዕግስት በጽናት ተቋቁማለች፡፡ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በልጇ ላይ የወረደውን ስድብ እንግልት ግርፋትና ህማማተ መስቀል እየተመለከተች ከመሪር እንባ ጋር በጽናት ቆይታለች፡፡
ድንግሊቱ እነዚሁ ሁሉ መከራዎች ቢገጥማትም በልጇ የሚሆን ደስታዋን ስላላጣቸው በምሥጋና ፀሎቷ ውስጥ እንዲህ ብላለች“…መንፈሴም በአምላኬ በመድኋኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” ብላለች ሉቃ147፡፡
4)የእምነትና የመቀበል ሕይወት
እርሷ ስለተቀበለቻቸው መከራዎች አንድ ጊዜ እንኳን ይህ ለምን ሆነ አላለችም፡፡ሄሮድስ ልጇን ለመግደል አውሬ ሆኖ በተነሳበት ጊዜና ወደግብጽ ስትሰደድ እንዲሁ አይሁድ ያን ሁሉ መከራ ሥቃይ ሲያደርሱባት በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ይነግሳል ለመንግስቱም ፍፃሜ የለውም ብሎ መልአኩ የነገረኝ ቃል ወዴት ደረሰ? ብላ አልተናገረችም ሉቃ132-33፡፡ እናታችን ቅዱስት ማርያም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና እንደምትወልደው አምናለች ይህም ተከናውኖላታል፡፡ ምንም እንኳን ልጃ ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት ቢወለድም ስለእርሱ“…ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዘብሔር ልጅ ይባላል” ሉቃ135 ተብሎ በተነገራት የምስራች ቃል አምናለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ልጇ ሕማማተ መስቀል እንደሚገጥመውና በመስቀል ተሰቅሎ እንደሚሞትና ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሳ ስላመነች ይህንን በአይኗ ተመልክታለች፡፡ ማቴ28
5)ዝምታ ፀሎትና ተመስጦ
እናታችን በእግዚአብሔር ፈቃድ ቤተመቅደስ ውስጥ ስላደገች የብቸኝነትን የዝምታን በፀሎትና ተመስጦ ራሷን ጽሙድ በማድረግ በዚህ ተምራለች፡፡ እርሷ በልጅነቷ የወላጆቿን ፍቅርና እንክብካቤ ብታጣም ፍቅሯን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር በማድረግ አድጋለች በዚህም በብቸኝነት ለሚኖሩ ለባህታውያን ትልቅ ምሳሌ ነች፡፡
እርሷ ድንቅ ልጇን በወለደች ጊዜ ገና ብላቴና ነች ከእድሜዋ ጋር ሲነፃፀር ከህሊና በላይ የሆነ ድንቅ ተአምራት ተከባ ነበር እርሷ የመላእክትን የእረኞች የስብሰባስገልን(ከሩቅ ምስራቅ ሐገር የመጡ የጥበበኞች ሰዎችን ድንቅ ቃላት ምሥጋና ሰምታለች ቢሆንም ግን አንድም ጊዜ በኩራት አልተናገረችም በወንጌል የተፀፈው “… ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር”፡፡ ሉቃ219እና52 ይህ ይሁንእንጂ እናታችን መናገር በሚገባት ጊዜ ስትናገር የተናገረቻቸው ንግግሮች ለትውፊታዊ ስብከቶች ምንጮች ነበሩ፡፡ሐዋርያትንና ወንጌላውያን ባቀረቧቸው ዜናዎቻቸው ላይ ከእርሷ ብዙ እንደተማሩ ገልጠዋል በተለይ ፍቅሩ እግዚእ ዮሐንስ ከፃፈው ወንጌልም እንደምንረዳው ከእርሷ ስለምስጢረ ሥላሴ ጥልቅ ነገር እንደተማረ ያስታውቃል፡፡ ድንግል ማርያም ብቸኝነትን ፀጥታን ከጸሎት ከዜማ ከመዝሙራት መፃሕፍትን ከማንበብ ያነበባቸውን ጥቅሶች በተለይም መዝሙረ ዳዊትን በተመስጦ ውስጥ ሆና በቃሏ በመውጣት ሙሉ ጊዜዋን በዚህ ታሳልፍ ነበር፡፡ በእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ያለው ዝምታ ለእኛ ትምህርት ሰጪ ነው እናም እባካችሁ እርስዋን ጥቂት በመናገርና ብዙ በመጸለይ በተመስጦ ውስጥ በመቆየት እንምሰላት፡፡
6)ሌሎች የቅድስና ጠባዮቿ
እግዚአብሔር ወላጆቿን በሕጻንነቷ እድሜ ያጣችውን ድሀ ድንግል እናት አደርጎ የመረጠው በሕልውናዋ(በአኗኗርዋ) ከሴቶች ሁሉ የምትልቅ እናት ሊያደርጋት ስለወደደነው እርሷ በጠባዮቿ ከገንዘብ ብልጽግና የሚልቁልዩ ጠባያት አሏት፡፡ ቅድስና ንፅሕና ድንግልና መንፈሳዊ ዕውቀት ሌሎችን ማገልገልና ለሐዋርያት አባቶች ያሳየቻቸው መንፈሳዊ እናትነት ከዋና ዋና ጠባዮቿ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በረከቷ ጸንቶ ይደርብን !!! አሜን
48 viewsbisrat, 17:21