Get Mystery Box with random crypto!

#ጥር_6_ታላቋ_ሰማዕት_ቅድስት_አርሴማ_የተወለደችበት_ዕለት_ነው። የቅድስት አርሴማ እናት ቅድስት | ዝክረ ብሒለ አበው

#ጥር_6_ታላቋ_ሰማዕት_ቅድስት_አርሴማ_የተወለደችበት_ዕለት_ነው።

የቅድስት አርሴማ እናት ቅድስት አትናሲያ አባቷ ቅዱስ ቴዎድሮስ ይባላሉ፤ እናትና አባቷ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ከካህናት ወገን የሆኑ መልካም ምግባር የነበራቸው ነበሩ፤ ልጅ ስላልነበራቸው ልጅ እንዲወልዱ ስዕለትን ተሳሉ፤ እግዚአብሔርም ልጅን ሰጣቸው፡፡ በሥነ ምግባርና ብሉይና አዲስ ኪዳንን እያስተማሯት አደገች፡፡

በሥነ ምግባር ታንጾ ለመኖር ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይገባል፤ የእግዚአብሔር ወዳጅ ቅድስት አርሴማ በጥሩ ሥነ ምግባር ካደገች በኋላ ለወላጆቿ እየታዘዘች በሥርዓት ኖረች፡፡ ጾመኛ፣ ጸሎተኛ፣ ደግ ሴትም ነበረች፡፡ ለሰዎችም ታዝን ነበር፤ ካደገች በኋላ ደግሞ በድንግልና ሕይወት መኖርን መረጠች፤ መንኩሳም በገዳም ታገለግል ጀመር፡፡

እርሷ በነበረችበት ዘመን እግዚአብሔርን ክዶ የሚያስክድ ዲዮቅልጥያኖስ የተባለ ጨካኝ ንጉሥ ነበር፤ ክርስቲያኖችን ለጣዖት ስግዱ እያለ መከራ አጸናባቸው፤ ቅድስት አርሴማ እና ሃያ ሰባት ደናግል በገዳም በጾም በጸሎት በነበሩ ግዜ ጨካኙ ንጉሥ በሰይጣን ተገፋፍቶ ቅድስት አርሴማን ሊያገባት ፈለገ፡፡ እርሷ ግን በድንግልና ሕይወት መንኩሳ መኖርን መርጣ ነበርና ከጓደኞቿ ጋር ሆና አርማንያ ወደ ተባለ አገር ተሰደዱ፡፡

ለጊዜው ከጨካኙ ንጉሥ አምልጠው በገዳም ውስጥ በጾም በጸሎት ተግተው ሳለ ንጉሡ ለአርማንያ አገረ ገዢ ለንጉሥ ድርጣድስ መልእክት ላከ፤ ‹‹ አንተ አገር ተሰደው የመጡ ደናግል አሉና ይዘህ ላክልኝ ›› አለው፤ ከዚያም አፈላልገው ቅድስት አርሴማን አገኟት፤ ድርጣድስ ባያት ጊዜ ከደም ግባቷ ማማር የተነሣ ‹‹ ላግባሽ›› ብሎ ጠየቃት፤ እርሷም ‹‹ እኔ በድንግልና ሕይወት የምኖር የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ ማግባት አልፈልግም ›› አለችው:: በግድ አስገድዶ ሊያገባት ሲሞክር እጁን ጠምዝዛ በዐደባባይ ጣለችው፤ በዚህን ጊዜ በጣም አፈረ፤ በእርሷ እና በጓደኞቿ ደናግል መከራ እንዲያጸኑባቸውም አዘዘ፡፡

አንበሶች እንዲበሏቸው አንበሳ ካለበት ከተቷቸው፤ አንበሶቹ ግን ሳይበሏቸው ቀሩ፤ ዳግመኛም በረኃብ እንዲሞቱ ምንም መብልና መጠጥ በሌለበት ቤት አሠሯቸው፤ እግዚአብሔርም የሚበሉትን በሞሶብ የሚጠጡትን በጽዋ ከሰማይ አወረደላቸው፤ ከእሳትም ሲጨመሯቸው ደግሞ እሳቱ አላቀጠላቸውም፤ ይህን ድንቅ ተአምር እግዚአብሔር አድርጎላቸው፤ ከግፈኞች እጅ አስጣላቸው፡፡

እግዚአብሔር ብቻ ለማምለክ ቆርጠው በተነሱ ደናግሉ ላይ ይህ ሁሉ መከራ ደርሶ ለጣዖት ባለመስገዳቸው አሁንም ንጉሥ ድርጣድን አበሳጨው፤ ቅድስት አርሴማን ለማስፈራራት ብሎ አብረዋት የነበሩትን ጓደኞቿን አንድ በአንድ በግፍ በሰይፍ ቀላቸው፤ ለሚሰውት (ለሚገደሉት) ሁሉ አክሊል ከሰማይ ይወርድላቸው ነበር፤ ቅድስት አርሴማም ‹‹ ይህን እያየች አይዟችሁ ጽኑ›› ትላቸው ነበር፡፡

ንጉሡም በቁጣ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆና ጸንታ የቆመችውን ቅድስት አርሴማን ‹‹ አንቺን እንደነርሱ በቀላሉ አልገድልሽም ›› በማለት ብዙ መከራ አጸናባት፣ ዓይኖቿን አወጣ፤ በብዙ ዓይነት ሥቃይም አሠቃያት፤

ስለስሙ በመመስከሯ፣ በድንግልና ሕይወት በመጽናቷ፣ የዚህን ዓለም ኑሮ ንቃ በብሕትውና በመኖሯ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ቃል ኪዳን ገባላት፤ ስሟን ጠርቶ የሚማጸን፣ ገድሏን የጻፈ ያነበበ፣ የሰማ፣ በስሟ የመጸወተውን እንደሚምርላት ቃል ኪዳን ሰጣት፤

በመስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀንም በሰይፍ ተሰይፋ ሰማዕትነትን ተቀብላለች፡፡ የእግዚአብሔር አገልጋይ እናታችን ቅድስት አርሴማ ለሰው ልጆች ድኅነት ፈጣሪን ተማጽና ምሕረትን አሰጥታለች፤ በዘመኗ ብዙ ድንቅ ተአምራትን አድርጋለች፤ መከራ ላደረሱባትም ጸልያለች፤ ከብዙ ዘመን በኋላም እርሷን እንድትገደል ያደረገው ጨካኙ ንጉሥ ድርጣድስ ከክፉ ሥራው ተመልሶ ንስሓ ገብቶ እርሱም ስለ ክርስቶስ መስክሮ ለክብር ሕይወት በቅቷል፡፡

በእናታችን ቅድስት አርሴማ መከራ ላደረሱባት በመጸለይዋ ሳያውቁ ይሠሩት ከነበረው ክፉ ሥራቸው እንዲመለሱ አድርጋቸዋለች፡፡

ልደቷ ጥር 6
ሰማዕትነት የተቀበለችበት መስከረም 29
ቅዳሴ ቤቷ ታህሳስ 6 ታስቦ ይውላል ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቷ ጸሎት ይማረን!!!