2023-01-27 20:13:35
#ጥር_21_የእመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም_የዕረፍቷ_መታሰቢያ_ዕለት_ነው ።
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞት ነገረ ማርያም፣ ስንክሳር እና ተኣምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በ16 ዓመተ ዓለም ከኢያቄም እና ከሐና ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሣ ፤ በ15 ዓመተ ዓለም ግንቦት 1 ቀን ፤ በሦስት ዓመቷ ታኅሣሥ 3 ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገባች ፤ ለ12 ዓመታት በቤተ መቅደስ ስታገለግል ቆይታ ፤ በ15 ዓመቷ የዓለሙን መድኃኒት በቤተ ልሔም ወለደች ፤ ለ33 ዓመት ከ3 ወር ያህል ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከኖረች በኋላ ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ እናቱን ‹‹እነኋት እናትህ›› ብሎ ለዮሐንስ ወንጌላዊ አደራ ሰጣት ፤ እመቤታችን በቅዱስ ዮሐንስ ቤትም ለ15 ዓመታት ያህል ቆየች፡፡ ከዚህም በኋላ ስላለው የእመቤታችን የሕይወት ታሪክ በመቀጠል እንመለከት፡-
እመቤታችን 64 ዓመት በሆናት ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ‹‹ከኀዘን ወደ ደስታ ትሔጂ ዘንድ ሙቺ›› አላት ፤ እርሷም ‹‹ልጄ ሆይ አንተን ወልጄ ያንተ እናት ሆኜ እኔ እንዳት ልሙት›› አለችው፡፡
ጌታችን በሲኦል ያለ 99,999 አሳያት ፤ እመቤታችንም የእነዚህን ነፍሳት መከራ ልቅሶና ጭንቀት ስትመለከት “አስታረቀሽ አማልደሽ አድኝን” የሚለውን ጩኽታቸውን ስትሰማ ፤ ‹‹ልጄ ወዳጄ ሆይ ማርልኝ›› አለችው፡፡ ጌታም መልሶ ‹‹እኔ የአዳምን ልጆች ያዳንኩት መከራን ተቀብዬ ተሰቅዬ ሞቼ ነው ፤ አንቺም ለእነዚህ ነፍሳት ካልሞትሽላቸው ወደ ገሃነም ይገባለ›› አላት፡፡
እመቤታችንም ለፍጥረታት ካላት ፍቅር የተነሣ ‹‹እነዚህ ነፍሳት ወደ ገሃነም ከሚወርደ እኔ ሰባት ጊዜ ልሙት›› በማለት ያለ መከራ ያለ ጭንቅ ጥር 21 ቀን በ49 ዓ.ም ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች፡፡ ሐዋርያት የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን እረፍት በሰሙ ጊዜ ጊዜ ፈጽመው አዘኑ ፤ ስለ ሰማያዊ ምሥጢር የምትነግራቸው ፤ እንደ እናት የምትንከባከባቸው እርሷ ነበረችና ኀዘናቸው ፍጹም ነበረ፡፡ በሥርዓቱም መሠረት እመቤታችንን በጨርቅ ገንዘው በአልጋ ላይ አድርገው እያለቀሱ ሉቀብሯት ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ አይሁድ ድንግል ማርያም ሞተች የሚለውን ዜና በሰሙ ጊዜ ፤
‹‹አስቀድሞ ልጇ ከሞተ በኋላ ተነሥቷል ተብሎ ሀገር ሲታወክ ነበረ ፤ አሁንም ደግሞ እርሷም ሞታ ተነሣች ተብሎ በሀገሩ ሁሉ ሉወራ ነውና ቶሎ ብለን ሥጋዋን እናቃጥለው፡፡›› ብለው ተስማምተው ፤ ከመካከላቸው አካለ የገዘፈ ፈርጣማ የሆነ ታውፋንያ የተባለውን ሰው ሥጋዋን ከሐዋርያት ነጥቆ እንዲያቃጥል ላኩት፡፡ እርሱም በተላከው መሠረት እመቤታችን ያረፈችበትን አልጋ በእጆቹ በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ እጆቹን ቆረጠው ፤ እጆቹም በአልጋው ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ ፤ ታውፋንያም “በድያለሁ ማሪኝ” በማለት መጮኽ ጀመረ ፤ በዚህ ሰአት እመቤታችን አማልዳው ፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ጸልዮ የታውፋንያ እጆች እንደቀድሞው ሆኑ፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስንና የእመቤታችንን አካል ሰውሮ ወደ ሰማይ ወሰደው ፤ የድንግልንም ሥጋ በዕፀ ሕይወት ሥር አሰቀመጠው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስም ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት ተመልሶ የእመቤታችን አካል የት እንዳረፈ ቢነግራቸው እነርሱም ዮሐንስ የእርሷን የሥጋዋን መቀበር አይቶ እኛ ሳናይ ብለው መንፈሳዊ ቅንዓት አድሮባቸው ሱባኤ ገብተው በ14ኛው ቀን ነሐሴ 14 እለተ እሐድ ፤ አምላካችን የእመቤታችንን በድን ሥጋ ሰጣቸው ፤ እነርሱም በደስታ ተቀብለው በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በሚያስተምርበት ሀገር አስተምሮ አጥምቆ በደመና ላይ እየተጓጓዘ ሲመለስ ፤ ነሐሴ 16 ቀን ማክሰኞ እለት እመቤታችን በመላእክት ታጅባ ስታርግ አግኝቷት የተገነዘችበትን ሰበን ይዞ ወደ ሐዋርያት ሄዷል።
እንደማያውቅ ሆኖ ቅዱሳን ሐዋርያትን ስለ እመቤታችን ነገር ጠየቃቸው ጥር 21 ማረፏን ነሐሴ 14 ደግሞ መቃብሯን ነገሩት እርሱም‹‹እንዴት ሞት በጥር ፤ በነሐሴ መቃብር ይሆናል? እኔ አላምንም›› አላቸው እነርሱም ያምናቸው ዘንድ ወደ ጌቴሴማኒ የመቃብር ሥፍራ ወስደው ቢያሳዩት ምንም ነገር የለም ፤ ሁሉም ተመለከቱ አንዳች ነገር አላገኙም ፤ በደነገጡም ጊዜ ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ‹‹አትደንግጡ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች ፤ ሥጋዋን ካላሳያችሁኝ አላምንም ያልኩት ፤ እንዳትጠራጠሩኝ ነው›› ብሎ የተገነዘችበትን ጨርቅ አውጥቶ አሳያቸው ለበረከት እንዲሆናቸውም ሁሉም ተከፋፈሉት፡፡
ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን እኛንም በእመቤታችን ጸሎት ይማረን በረከቷ ይደርብን!!! አሜን
63 viewsbisrat, 17:13