2023-03-24 19:17:55
የቅንነት ወይስ የቅንዐት መንፈስ!!
የእግዚአብሔርን እጅ በህይወታችን ላይ በኃይል ከሚያንቀሳቅሱና በጨለማው አለም ሥርዐት ወጥመድ ውስጥ በቀላሉ ወድቀን እንዳንሰባበር ከሚያደርጉን መንፈሳዊ እሴቶች መካከል ዋነኛው ቅንነት ይባላል........ቅንነት የምንለው ለሰዎች፣ ለነገሮች እንዲሁም ለሁኔታዎች ያለን የተቃናና ያልተዛባ እንዲሁም በተፈወሰ ህሊና ላይ የተመሰረተ ድንቅ መረዳት ሲሆን ይህም የተጣመመና የተዛነፈ ድምዳሜ ፈጥነን እንዳናደርግ ይጠብቀናል......ቅንዐት ግን ለሌሎች ሰዎች አንዳች ነገር ቢደረግ እንኳን በዚያ ጉዳይ አብሮ ከመደሰት ይልቅ ቆይ ለኔስ ግን ብሎ በመቆጣት ሁሉንም ነገር ከራስ ጥቅም አንፃር ብቻ ማየት ሲሆን ምንጩም አጋንንት ነው(መልካም የሆነ መንፈሳዊ ቅንዐት መኖሩን ግን አምናለሁ).....መፅሃፍ ቅዱሳችን ከቅንዐት መንፈስ ተላቅቀን በቅንነት መንፈስ እንድንመላለስ ደጋግሞ ይመክረናል......ቅንዐት ከሥጋ ሥራዎች መካከል ዋነኛው ሲሆን ልቡ በዚህ መንፈስ የተሞላ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቷል፤ በተቃራኒው ደግሞ በቅንነት የተሞላ ልብ ለእግዚአብሔር እንደ ጣፋጭ መስዋዕት በመሆኑ በቀላሉ የጌታ መገኘት በህይወታችን ላይ በኃይል እንዲበዛ ያደርጋል....ሃሌሉያ....በአለማችን ላይ ከመቼውም ግዜ ይልቅ ቀናነት እየጠፋ ቅንዐት ግን እንደ አሸን እየፈላ ያለበት ግዜ ላይ እንገኛለን ብል ማጋነን አይሆንም፤ በዘመናት መካከል ግን እግዚአብሔር የተጠቀመባቸውን ሰዎች ህይወት ብናጠና ዋናው መገለጫቸው የቅንነት ህይወታቸው ነው...ለምሳሌ ያህል ዳንኤልን፣ ኢዮብን,,,መመልከት ይቻላል:-
“በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው።”ዳንኤል 6፥22
እግዚአብሔር ስለ ኢዮብ ቅንነት የተናገረውን እናንብብ:-
“እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፤ በከንቱም አጠፋው ዘንድ አንተ በእርሱ ላይ ምንም ብታንቀሳቅሰኝ፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ይዞአል።” ኢዮብ 2፥3
ኢየሱስ ራሱ በናትናኤል ልብ ውስጥ ተንኮል እንደሌለ መስክሯል:-
“ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፦ ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።”ዮሐንስ 1፥48
ቅንዐት የዚህ አለም(የአጋንንት) ጥበብ መገለጫ ነው.....በቅንዐት መንፈስ ህይወቱ የተሞላ ሰው ወደደም ጠላም የጠላት መጠቀሚያ ሆኗል:-
ያዕቆብ 3
¹⁴ ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ።
¹⁵ ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤
¹⁶ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና።.
በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መነጋገር ይቻላል ሆኖም ግን ለዛሬ እዚህ ጋር ላብቃ.....እንዲህ ግን ልባርካችሁ:- በልባችን ውስጥ የተሰገሰገ የቅንዐት መንፈስ ምናልባት ቢኖር አሁን ከልባችን ውስጥ ተጠራርጎ በኢየሱስ ስም ይውጣ፤ ጌታ ልባችንን በቅንነት መንፈስ ይሙላው.....ተባርካችኃል!!
“ዘሩ በምድር ላይ ኃያል ይሆናል፤ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች።”መዝሙር 112፥2
“የኀጥኣን ቤት ይፈርሳል፤ የቅኖች ማደሪያ ግን ያብባል።”ምሳሌ 14፥11
“የኀጥኣን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው።”ምሳሌ 15፥8
@ZaphnathPaaneah1
@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
999 viewsYonatan Worku, 16:17