2023-04-10 16:28:57
እግዚአብሔርን በቆይታ መፈለግ!!
አስቀድመን መረዳት ያለብን እውነት ቢኖር እግዚአብሔር መታወቅ የሚወድና እንዲታወቅም ራሱን በልዩ ልዩ መንገዶች የገለጠ መሆኑን እንጂ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ከፍጥረታት ሁሉ ተደብቆና ተሸሽጎ መኖር የሚፈልግ አምላክ አይደለም!!
“በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፦ በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ ቅንንም አወራለሁ።”ኢሳይያስ 45፥19
እግዚአብሔርን መፈለግ ማለት ህይወትን፣ ሰላምን፣ እረፍትን፣ ደስታን፣ እርካታን፣ በረከትን,,,ወዘተ እንደመፈለግ ይቆጠራል፤ እርሱ የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ነውና...ሃሌሉያ!
“ባለጠጎች ደኸዩ፥ ተራቡም፥ እግዚአብሔርን የሚፈልጉት ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም።”መዝሙር 34፥10
የሰው ልጆች ሁላችን አንድ ልናውቀው የሚገባን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር አምላክ ከምንገምተውና ከምናስበው በላይ እንደሚያስፈልገንና ያለእርሱ ህይወታችን ከንቱና ባዶ እንዲሁም ትርጉም አልባ መሆኑን ነው!!
“ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።”ሐዋርያት 17፥28
እግዚአብሔርን መፈለግ የሚገባን በፍፁም ልባችን፣ነፍሳችን፣ ሃሳባችን ኃይላችን ሲሆን በፈለግነው መጠንም እናገኘዋለን......በጣም የሚገርመው ምንም እንኳን አምላካችን ይታወቅ ዘንድ ለሁሉም ሰው ራሱን እኩል የገለጠ ቢሆንም ሁላችንም ግን እኩል አናውቀውም፤ የተጠጋነውንና የቀረብነውን ያህል ብቻ እንጂ!!
አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔርን የመፈለግ አፒታይታቸው ብዙም ባለመሆኑ ከትንሽ ፍለጋ በኃላ ይደክማቸዋል ከዚያም ያቆማሉ......ሌሎች ደግሞ አሉ አሣ ከውኃ ውስጥ ወጥቶ መኖር እንደማይችል በቃላት ሊገለጥ በማይችል ረሃብ እግዚአብሔርን ቀንና ሌሊት የሚናፍቁ ፤ እንደዚህ አይነት ሰዎች አንድ የበራላቸው እውነት ስላለ እግዚአብሔርን በሙሉ ትኩረትና በፍፁም መሻት እንዲሁም በረጅም ቆይታ ሲፈልጉት ይታያል....ጌታ ሆይ እባክህ እኔንም እንደነዚህ ልባሞች አድርገኝ!!
መዝሙር 42
¹ ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች።
² ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?
ተወዳጆች ሆይ እግዚአብሔርን መፈለግ ብለን ስናወራ ለእርሱ ያለን ትኩረት፣ ረሃብ፣ ናፍቆት፣ ጥማት ብቻ ሳይሆን ግዜን(ቆይታ) ይመለከታል.....ወደድንም ጠላንም ለአንድ ነገር ያለን እውነተኛ ፍቅር የሚለካው ለነገሩ በምንሰጠው ግዜ እንጂ የንግርት ቃል ብቻ አይደለም......በጣም ቢዚ ነኝ እንኳን ብለን ብናስብ ከልብ ለምንወደው መቼም ግዜ አናጣም(ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም)
እግዚአብሔርን በቆይታ ውስጥ በፅናት መፈለግ ወደ እኛና ወደነገራችን ዘንበል እንዲል ያደርገዋል....እርሱን የመፈለጋችን እውነተኝነት የሚረጋገጠው በግዜ ውስጥ እንደወርቅ ተፈትኖ ሲያልፍ ነው.....እግዚአብሔርን መፈለግ አለብኝ ብለው መንገድ የሚጀምሩት ብዙ ቢሆኑም ፍለጋቸው ፍሬ አፍርቶ ናፍቆታቸው ጋር የሚገናኙ ግን በጣም ጥቂቶችና እስከመጨረሻ የፀኑ ብቻ ናቸው!!
ዳዊት በመዝሙሩ የሚያስታውሰን ይንኑ ነው፤ ዛሬ ለሁላችንም እፀልያለሁ:-"እግዚአብሔርን ወደህይወታችን ዘንበል የሚያስደርግ በፊቱ የምንቆይበት መለኮታዊ ፀጋ በኃይል ይለቀቅልን..በኢየሱስ ስም!!"
መዝሙር 42
¹ ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች።
² ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?
@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
1.0K viewsYonatan Worku, 13:28