Get Mystery Box with random crypto!

Zaphnath-paaneah

የቴሌግራም ቻናል አርማ zaphnathpaaneah1 — Zaphnath-paaneah Z
የቴሌግራም ቻናል አርማ zaphnathpaaneah1 — Zaphnath-paaneah
የሰርጥ አድራሻ: @zaphnathpaaneah1
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 648

Ratings & Reviews

2.50

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

1

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 3

2023-04-09 16:29:09 ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም!!
(Spiritual babies)

“እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥”ኤፌሶን 4፥14

ሐዋርያው ጳውሎስ በተደጋጋሚ እያነሣ ከሚነቅፈው ነገር ዋነኛው መንፈሳዊ ህፃንነትን ነው......መንፈሳዊ ብስለት ውስጥ የገቡ ሰዎች ሁሉ በስጋ ዕድሜያቸውም በጣም የጎለመሱ ናቸው ማለት ላይሆን ይችላል(ዕድሜ የራሱ አስተዋፅዖ ቢኖረውም)

መንፈሳዊ ጉዳይ የመገለጥ(የውስጥ ዐይን መከፈት) ጉዳይ በመሆኑ አንዳንድ ግዜ በስጋ ዕድሜያቸው ህፃናት ሆነው በመንፈሳቸው ግን የጎለመሱ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በተቃራኒው በስጋ ዕድሜያቸው የሸመገሉ ሆነውም እንኳን በመንፈሳዊ ህይወታቸው ህፃናት የሆኑ ብዙ አሉ!!

በአንደኛ የቆሮንጦስ መልዕክቱ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ ህፃናት እንደመሆናችሁ እንጂ መንፈሳዊ እንደሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልኩም ብሎ የፃፈላቸው ሰዎች በመሠረቱ በስጋቸው ህፃናት አልነበሩም ይልቁንም ከመንፈሳዊነት ይልቅ ስጋዊነትን በመካከላቸው በማየቱ ነው!!

መንፈሳዊ ህፃናት የሚባሉት በስጋ የሚመላለሱና ለመንፈስ ቅዱስ ድምፅና ሃሳብ ራሳቸውን ያላስለመዱ በአጭሩ የግዜውን የእግዚአብሔር አጀንዳ ያልተረዱ እንዲሁ በመሳለኝና በደሳለኝ(በግምት) የሚመላለሱ ሰዎች ናቸው.....ከዚህ በተጨማሪ መንፈሳዊ ህፃናቶች በእግዚአብሔር ቃል የታጠቀና የተሞላ ህይወት ስለሌላቸው በትምህርት ንፋሶች ወደዚህና ወደዚያ በቀላሉ የሚፍገመገምና የሚንሳፈፍ ባህሪ አላቸው!!

በዚህም ምክንያት ሐዋርያው እያዘነ ወተት ጋትኋችሁ ይላቸዋል:-

1ኛ ቆሮንቶስ 3
² ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤
³ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?

በገሃዱ አለም ልጆች ተወልደውና አድገው ራሳቸውን ወደ መቻል እንደሚመጡ በዚህም ወላጆች እንደሚደሰቱ በመንፈሳዊውም አለም አባታችን እግዚአብሔር እንድናድግለትና ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ወደምተርፍበት መንፈሳዊ መረዳት እና ጥንካሬ ውስጥ እንድንገባ ይፈልጋል....ሁልግዜ መንፈሳዊ ህፃንነት(being spiritual babies) ሆነን በመቅረታችን ሰማይ ደስተኛ አይደለም፤ ይልቁንም ማደጋችን በነገር ሁሉ ሊገለጥ ይገባዋል.....ስጋዊነትን ከመካከላችን ነቅሰን ማስወገድ አለብን....ወደ እግዚአብሔር ፍፁም ሙላት ማደግ ይሁንልን!!

1ኛ ጢሞቴዎስ 4
¹⁵ ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር።
¹⁶ ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
670 viewsYonatan Worku, 13:29
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-08 02:30:26 እናትህንና አባትህን አክብር!!
(Honor your father and mother)

እውነት ለመናገር ይሄ ሃሳብ ሰንደይ እስኩል ላይ ለሚማሩ ህፃናትና ታዳጊዎች እንጂ እንደ እኛ የጎለመሱትን እስከቅርብ ግዜ ድረስ የሚመለከት አይመስለኝም ነበር ....አሁንም መንቃት መቻል ግን ቀላል አይደለም!!

“እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ።” ዘዳግም 5፥16

መፅሃፍ ቅዱስን ሳነብ አልበዛም ወይ እንዴ ብዬ እንድልና ጥያቄ እንኪፈጠርብኝ ያደረሰኝ ጥቅስ ቢኖር እናትንና አባትን ብሎም ታላላቆችን የማክበር እውነታ ነው....እግዚአብሔር ግን ይህንን ጉዳይ እንዴት አፅንዖት ሊሰጠው ቻለ???

ከላይ በለጠፍኩላችሁ ጥቅስ ላይ ብቻ እንኳን ብንመለከት እናትንና አባትን ማክበር ሁለት ትልልቅና አስደናቂ በረከቶችን ያጎናፅፋል:-

1. ዕድሜህ እንዲረዝም
2. በዘመንህ መልካም እንዲሆንልህ

ለምሳሌ በጣም የፀሎት ሰው ሆነን ነገር ግን ታላላቆቻችንን የማክበር ዝንባሌ ከሌለን ከዕድሜ ርዝማኔ በረከት ጋር እንተላለፋለን፤ ህይወታችንም በመልካምነትና በበረከት ሳይሆን በትግልና በስቃይ የተሞላ ይሆንብናል.....ሁልግዜ ማወቅ ያለብን እውነት ቢኖር እውነት እንደማይተካካ ነው....ልክ ሽንኩርት ቲማቲምን ቅቤ ደግሞ ጨውን እንደማይተካው ሁሉ ቀላል የሚመስሉ መንፈሳዊ መርሆዎችን መሳት ይሄ ነው የማይባል መከራ ሊያስከትልብን ይችላል!

በስጋ የወለዱንን ወላጆቻችንን ብቻም ሳይሆን በዕድሜ፣ በዕውቀት፣ በስልጣን  ከእኛ የሚቀድሙትን ማክበርና የሚገባቸውን ክብር መስጠት መንፈሳዊነት ነው...ሁለት ጥቅሶችን ላንሣ(አንድ ከብሉይ ኪዳን አንድ ከአዲስ ኪዳን):-

“በሽበታሙ ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”ዘሌዋውያን 19፥32

1ኛ ጢሞቴዎስ 5
¹-² ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፥ እርሱን ግን እንደ አባት፥ ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፥ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፥ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው።
³ በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር።

ምናልባት እኮ ወላጆቻችንም ሆነ ታላላቆቻችን ብለን የምንላቸው በአንዳንድ ነገር(በአካዳሚክ ዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም,,) እንበልጣቸው ይሆናል ሆኖም ግን በተቀመጡበት ቦታ(position) ይበልጡናል.....ወደድንም ጠላንም ወደዚህ ምድር ቀድመው የመጡበትን እውነታ ልንክደው አንችልም ስለዚህ ልናከብራቸው ይገባል.....ይሄ ብቻ አይደለም ባህሪያቸውም የሚመች ባይሆን እንኳን መንፈሳዊ ስርዓት ስለሆነ መገዛት(submission) አማራጭ የለውም....በመጨረሻም አክብሮታችንን ለመግለጥ አንድንድ ስጦታዎችን መስጠት ጥሩ ዕድልና አጋጣሚ ነው.....ተባርካችኃል!!

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
1.3K viewsYonatan Worku, 23:30
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-05 03:59:23 ወደድንም ጠላንም እውነቱ ይህ ነው፤ እንሸሽገውም ዘንድ አይቻለንም

በህግ ለመፅደቅ ማሰብ የኢየሱስን ሞት ከንቱ ማድረግ ነው

“የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።”ገላትያ 2፥21

ያለ ህግ እንዲሁ በነፃ የፀደቅሁበትን የእግዚአብሔርን ፀጋ አልጥልም....ህግን በመጠበቅ ለመፅደቅ መጣጣር/ መታገል ከፀጋ መጉደል ብቻ ሳይሆን መውደቅም ጭምር ነው!!

“በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።”ገላትያ 5፥4

እግዚአብሔር ሰዎች በፀጋ የሚፀድቁበትን መንገድ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያሰናዳው በህግ በኩል ቢሆን ማንም እንደማይፀድቅ ስለሚያውቅ ነው!!

“ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው።”ገላትያ 3፥11

አንዳንዶች ከይሁዳ ወርደው እንደሙሴ ስርዐት ካልተገረዛችሁ አትድኑም በማለት በፀጋ ከዳኑበት ወደ ህግና ትዕዛዛት በመጠበቅ መዳን ወደሚል አስተምሮ ሊመልሷቸው ሲሞክሩ(ሐዋ 15:1)..ጴጥሮስ ተነስቶ የመለሰላቸው መልስ ያስገርማል.....እንዲህ አለ:-ይሄ በህግ በኩል የመፅደቅ ጉዳይ እንኳን ለአዳዲስ ደቀመዛሙርት ይቅርና እኛና አባቶቻችንም እንኳን ልንሸከመው ያልቻልነው ቀንበር ነበር....እዩትማ ቃሉን:-

ሐዋርያት 15
¹⁰ እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ?
¹¹ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን።

የህግ ፍፃሜ የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን ማመን ብቻውን ለመፅደቅ ይበቃል.....ከዛ ውጪ ያለ አስተምሮ የስጋና የአጋንንት ነው!!

“የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።”ሮሜ 10፥4

ለምትሰሙኝ ሁሉ ቅዱሱ መፅሃፍ የሚለውን እናገራለሁ.....እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ሥራ በኩል ሰርቶ የጨረሰልን እኛን ከዘላለም ፍርድ አድኖ ለማፅደቅ ያለምንም የእኛ መዋጮ(አስተዋፅዖ) ከበቂ በላይ ነው!!ሃሌሉያ

ኤፌሶን 2
⁸ ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤
⁹ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።
1ኛ ቆሮንቶስ 1
²⁹ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ።
³⁰-³¹ ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።
#SHARE #SHARE #SHARE
@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
https://t.me/+I4DSx0eJ2iI2MDg0
130 viewsYonatan Worku, edited  00:59
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-04 11:33:07 አንተ ቅዱስ ነህ ስራህ ትክክል፤
አንተ ጻዲቅ ነህ ስራህ ትክክል፤
ጉልበቴ ብቻ ሳይሆን፤
ልቤም ሚገዛልህ፤
ምላሴ ብቻ ሳይሆን፤
ህይወቴም ያክብርህ፤
አንተ ታይ እኔ አልታይ በህይወቴ ላይ፤
አንተ ስትታይ ነው ክብር ያለው ድል ያለው።

ቦሌ አማኑኤል ሽብሸባ ኳየር
@yedestaye_elilta

https://t.me/+I4DSx0eJ2iI2MDg0
53 viewsYonatan Worku, edited  08:33
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-04 11:27:33 ሁልግዜ ስለሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ!!

“ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ።”ኤፌሶን 5፥20

እግዚአብሔር አምላካችንን መቼ መቼ ላመስግነው ወይም በእንዴት አይነት ሁኔታ ውስጥ ስሆን ላመስግነው ተብሎ አይጠየቅም.....እርሱ ሁልግዜ ስለሁሉ የሚመሰገን አምላክ ነው፤ በቀን 24 ሰዐታት፣ በሳምንት 7ት ቀናት፣ በወር 30 ቀናት፣ በአመት 365 ቀናት እንዲሁም ለዘላለም ይመሰገናል....ከተፈጠሩ ጀምሮ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑት እልፍ አዕላፋት መላዕክት ዙፋኑን ከብበዋል....እርሱ እየነበረ የነበረ ሲሆን ለመንግስቱ ፍፃሜ ለአገዛዙም መጨረሻ የለውም......በፈቃዱ ፍጥረታት ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር ካለመታየት ወደመታየት መጥተዋል......የሚወዳደረውና የሚስተካከለው አንዳች አልተገኘም፤ አይገኝምም......አልፋና ኦሜጋ፣ ፊተኛና ኃለኛ መጀመሪያና መጨረሻ እርሱ ብቻ ነው.....ለቁጣ የዘገየ ለምህረት ደግሞ የቸኮለ ደግና ርህሩህ የሆነ እንደ እርሱ ያለ የለም......ፍርዱ አይጓደልም፤ በፅድቅ ይፈርዳል.....በስራው አንዳች እንከን የለበትም...ሃሌሉያ!!

ለእግዚአብሔር ክብር ተፈጥረናልና ቅዱስ ስሙን እናክብር.....በምንም ነገር ውስጥ ብናልፍ እግዚአብሔርን እናዳናመሰግን የሚያደርገን አንዳች ምክንያት የለም፤ ሊኖርም አይገባም....ጳውሎስና ሲላስን በእስር ቤት ያመሰገኑትን መመልከት ይቻላል(ሐዋ 16:25).. ሞላ ጎደለ ወይም ሆነ አልሆነ ብለን አስልተን ሳይሆን ስለሚገባው እግዚአብሔርን ሁልግዜ ስለ ሁሉ እናመሰግነዋለን.....የእኛ የምንለው አንዳች ነገር የለንም፤ እኛነታችን እንኳን ሳይቀር የእርሱ የራሱ ነው.....ከተገለጡ የእግዚአብሔር ፈቃዶች መካከል አንደኛው ያለማቋረጥ አምላክን ማወደስ ሲሆን እርሱን ለማመስገን ፈቃዱ ይሆን አይሆን ተብሎ አይጠየቅም.....ዛሬ እፀልያለሁ ይህንን ፅሁፍ የምታነቡ ሁላችሁ የምስጋና መጎናፀፊያ ይወደቅባችሁ፤ ሁልግዜ ስለሁሉ እግዚአብሔርን እናመሰግን ዘንድ!!

“ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።”
1ኛ ተሰሎንቄ 5፥17-18

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
https://t.me/+I4DSx0eJ2iI2MDg0
492 viewsYonatan Worku, edited  08:27
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-02 13:50:01 ፍቅርና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ያላቸው ዝምድና!!

“ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ።”1ኛ ቆሮንቶስ 14፥1

አብዛኞቻችን እንደምናውቀው ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችና አጠቃቀማቸው በዝርዝር በ1ቆሮ 12፣ 13 እና 14 አብራርቶ አስቀምጦልናል.......ምንም እንኳን የፀጋ ስጦታዎችን በተመለከተ አንድ በአንድ እያነሣ ቢያስረዳንም(በነዚህ ሶስት ምዕራፎች) አፅንዖት ሰጥቶ በተደጋጋሚ የሚያነሣው ጉዳይ ቢኖር ግን ስለ ፍቅር ነው(ለምሳሌ 1ቆሮ ምዕራፍ 13 ሙሉውን፣ 1ቆሮ 14:1,,,,,)

ሐዋርያው ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እያስተማረ ቢሆን እንኳን ስለፍቅር ሳያነሣ ግን በፍፁም አያልፍም....ይህ የሆነበት ምክንያት አንደኛ ከፍቅር ውጪ የሚገለጥ የፀጋ ስጦታ ምንም የማይጠቅም ከንቱ በመሆኑና የፀጋ ስጦታዎች በህይወታችን ላይ በኃይል እንዲገለጡ ደግሞ ቁልፉ ፍቅር እንደሆነ ለማሳሰብ ነው!!

1ቆሮ 14:1 ላይ ሲጀምር ፍቅርን ተከታተሉ በማለት ነው....በመቀጠል መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ እንድንፈልግ
ያበረታታናል......ምክንያቱም በውስጣችን ያለው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በኃይል እንዲገለጥ በዋነኝነት ለወንድማችን ያለን ፍቅርና ርህራሄ ወሳኝነት አለው.....ለምሳሌ የፈውስ የፀጋ ስጦታ ቢኖረንና በከፍተኛ ሁኔታ በህመም ለሚሰቃይ ሰው ለመፀለይ ብንቀርብ ውስጣችን ያለውን ፀጋ በኃይል እንዲቀጣጠልና እንዲገለጥ የሚያድርገው ለታማሚው ሰው የምናሳየው ርህራሄና ከዚህ በሽታ እንዲገላገል ያለን ከእውነተኛ የፍቅር ልብ የመነጨ ጥልቅ የሀዘኔታ ስሜት ነው.....ሃሌሉያ....ስቃዩን ሳንረዳና ህመሙ ሳይገባን ለታመመ ሰው የምንፀልየው ፀሎት ብዙ ግዜ ውጤታማ አይሆንም.....የኢየሱስን አገልግሎት ብንመለከት እንኳን ብዙ ሰዎችን ከልዩ ልዩ እሥራቶች ከመፍታቱና ከመፈወሱ አስቀድሞ በልቡ ስላሉበት ጉስቁልናና ስቃይ እንደሚያዝን መፅሃፍ ቅዱስ ይነግረናል:-

ማቴዎስ 9
³⁵ ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር።
³⁶ ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።

በዚህች አጭር የአገልግሎት ዘመኔ የገባኝ እውነት ቢኖር ከፍቅር ውጪ የትኛውም አይነት የፀጋ ስጦታ ምንም የማይጠቅም(ከንቱ) መሆኑንና በፀጋ ስጦታዎች በኃይል ለማደግና በህይወታችን ለመለማመድ ደግሞ የፍቅርና የርህራሄ ሰው መሆን አማራጭ የሌለው እንደሆነ በደንብ ተረድቻለሁ.....ለዚህም ይመስላል ሐዋርያው ስለ ፀጋ ስጦታዎች በዝርዝር ከማስቀመጡ በፊት ፍቅርን ተከታተሉ በማለት የሚጀምረው!!.....በእግዚአብሔር አለም ከሁሉም ነገር አስቀድሞ የሚመጣው ፍቅር ነው.....እንደ አገልጋይ ብቻም ሳይሆን ዳግም እንደተወለደ ሰው ፍቅር ከሁሉም በላይ ዋጋ ልንሰጠው የሚገባ እውነት ነው፤ ፍቅር በሌለበት እግዚአብሔር የለምና!!
let love lead!!

ቆላስይስ 3
¹³ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤
¹⁴ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
https://t.me/+I4DSx0eJ2iI2MDg0
818 viewsYonatan Worku, 10:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-01 11:14:47 ሰይጣን አንዲከራያችሁ አትፍቀዱለት!!

ማንም ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ ካመነ በኃላ የመንፈስ ቅዱስ ቋሚ መኖሪያ መሆኑ ይታወቃል.....በነገራችን ላይ መንፈስ ቅዱስ በአዲስ ኪዳን ወደ እኛ የሚመጣው ልክ በብሉይ ኪዳን እንደነበረው ሊጎበኘንና ሊሄድ ሳይሆን በውስጣችን ሊኖር ነው(Not for visitation but habitation).....ሃሌሉያ ...ሆኖም ግን ሰይጣን በውስጣቸው ባይኖር እንኳን ለተወሰነም ግዜ ቢሆን የሚከራያቸው "አማኞች" እንዳሉ እሙን ነው ......ሁላችንም የምናውቀውን ምሳሌ ከመፅሃፍ ቅዱስ እንመልከት:-

ማቴዎስ 16
²² ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ፦ አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ።
²³ እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው

አስተውሉ ሰይጣን አንደበቱን ለግዜውም ቢሆን የተከራየው ሰው ሌላ ሳይሆን የኢየሱስ የቅርብ የሆነ ደቀመዝሙር እርሱም ጴጥሮስ ነበር....ትንሽ ከፍ ብላችሁ ብታነቡት እኮ ኢየሱስ አንተ ብፁዕ ነህ ብሎታል:-

“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።”ማቴዎስ 16፥17

ብፁዕ ነህ ከዛ አንተ ሰይጣን ....ጉራማይሌ...ለማመን በሚከብድ ሁኔታ በአንድ ምዕራፍ ብቻ መንፈስ ቅዱስንም ሰይጣንንም ጴጥሮስ አስተናግዷል....ሌላው አስቆሮቶ ይሁዳንም መመልከት እንችላለን....ከኢየሱስ እግር ስር ቁጭ ብሎ ድምፁን እየሰማ ወደ ሶስት አመት ገደማ ቢኖርም ሰይጣንም እየመጣ ሃሳቡን እንዲያስገባበት ልቡ ክፍት ነበር....ይህም የውድቀቱ ብቻም ሳይሆን የጥፋቱም ምክንያት ሲሆንበት እንመለከታለን:-

“እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥”ዮሐንስ 13፥2

ዲያቢሎስ ወደ ሰዎች ህይወት ለሰከንድም እንኳን ቢሆን እግሩን የሚያስገባበት አጋጣሚ ካገኘ የሚያደርሰው ጥፋት ይሄ ነው ተብሎ የሚብራራ አይደለም.....ስለዚህ የቤታችንን ቅጥር አጥብቀን እንጠብቅ.....ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የማይቆጣጠረውና የማይገዛው የአካል ብልት ሊኖረን አይገባም፤ እጆቻችን፣ እግሮችን፣ ዐይኖቻችን፣ ጆሮዎቻችን፣ አንደበታችን፣ ሃሳባችን,,,ሁሉ በበጉ ደም ሊዋጁ ይገባል.....የማይነካ ነገር አለመንካት፣ መታየት የማይገባውን አለማየት፣ መስማት ከሌለብንም ነገር መራቅ አማራጭ የለውም......በፍፁም ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ በህይወታችን ውስጥ እንግዳ የሆነ ነገር መኖር የለበትም....በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አለበት?? ወይም ምን ችግር አለው?? የሚባል ነገር አይሰራም፤ ሞትስ ቢኖርበት .....ክርስቶስን ለመምሰል ራስህን አስለምድ እንደሚል ዘወትር ወደዚህ እውነት ለማደግ ራዳችንን ልናዘጋጅ ይገባል...እስቲ ሰይጣን ለሰከንድም ቢሆን አይከራየኝም ብላችሁ አውጁ....ተባርካችኃል!!!
https://t.me/+I4DSx0eJ2iI2MDg0

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
907 viewsYonatan Worku, 08:14
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-30 11:48:58 እባብ እንዲገባ ትንሽዬ ቀዳዳ ይበቃዋል!!

ይህንን የማካፍላችሁ ከመፅሃፍት ከቃረምኩት ብቻ ሳይሆን በህይወቴ ፈትኜና ተፈትኜበት ካሳለፍኩት ነው፤ ስለዚህ በቀላሉ የማየው ጉዳይ አይደለም......በነገራችን ላይ ትልቁ ትምህርት ቤት የህይወት ትምህርት ቤት እንደሆነ በጠንካራው አምናለው.....እባብ ወደ አንድ ግቢ ወይም ቤት ለመግባት እንደ አብዛኛው የዱር ወይም የቤት እንስሳት ትልቅ ፉካ(space) አይፈልግም......ይልቁንም እንዴት እንደገባ ለማመን እንኳን እስከሚያቅት ድረስ ቀጭንን መንገድ ይጠቀማል....ከገባ በኃላ ግን ይሄ ነው ተብሎ የማይባል(ምናልባትም እስከሞት የሚደርስ) አደጋና ምስቅልቅሎሽ ያደርሳል....በተመሳሳይ ሁኔታ ሰይጣን ወደ ሰዎች የግል፣ የቤተሰብ፣ የቤ/ክን፣ የሃገር እና የመሳሰሉት ስፍራዎች መግባት ሲፈልግ የሚጠቀመው በጣም ሰፊ ቀዳዳ አይደለም.....ይልቁንም የንፋስ መግቢያ ታክል ካገኘ ይበቃዋል.....ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ አጥብቀን ልንጠነቀቅ ይገባናል:-

“በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤”1ኛ ጴጥሮስ 5፥8

ተወዳጆች ሆይ ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት እያወራሁት ያለሁት ሃሳብ ከህይወት የተቀዳ እንጂ ከንባብ ብቻ አይደለም.....እንደ ቀላል ቆጥሬውና ችግር የለውም ባልኩት ቀዳዳ ጠላት ገብቶ ህይወቴን ሲያመሰቃቅለው አይቼ አውቃለሁ....ከዛ ዝም እልና:-ቆይ ግን እንዴትና መቼ ገባ ብዬ እጠይቃለሁ.....አብዛኛውን ግዜ ህይወታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉት ትልልቅ ነገሮች እንጂ ትንንሽ ነገሮች አይደሉም ብለን ስለምንገምት ለጥቃቅን ገዳዮች እምብዛም ትኩረት አንሰጥም፤ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ግን እዚህ ግቡ የማይባሉ ጉዳዮች የሰዎችን ህይወት በእጅጉ አደጋ ላይ ሲጥሉ ይስተዋላል....የሻይ ማንቆርቆርያን የሚደፍኑት የሻይ ቅጠል ድቃቂዎች ናቸው እንዲሁም የውኃ ምንጮች የሚደፈኑት ከትልልቅ ድንጋዮች ይልቅ በአነስተኛ ኮረቶችና ቆሻሻዎች ነው፤ ስለዚህ ቀላል ግምት የምንሰጣቸው ነገሮችን እንደውም አብዝተን መጠንቀቅ አለብን.....አንዳንድ ልጆች ከፍተኛ ደረጃ የማስተርቤሽንና የፓርኖግራፊ ሱስ ውስጥ የገቡት እኮ አንድ ግዜ ባዩት ፊልም ወይም ሶሻል ሚድያ ላይ ባዩት ምስል ሊሆን ይችላል....ተወዳጆች ሆይ ቅጥሮቻችሁን ጠብቁ፤ ዘንድሮ ንፋስ እንኳን ማስገባት የለብንም......ፀሎት አታቋርጡ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያላችሁን ህብረት በጥንቃቄ ተንከባከቡ፣ ለዲያቢያቢሎስ ዕድል ፋንታ አትስጡት.....ቅጥርን የሚያፈርስ እባብ ትነድፈዋለኝ እንደሚል ከምንም አስቀድመን መንፈሳዊ ልብሳችንን ልንታጠቅ ይገባናል፤ የመዳን ራስ ቁር፣ የመንፈስ ሰይፍ፣ የእምነት ጋሻ፣ የእውነት ቀበቶ፣ የፅድቅ ጥሩር፣ እንዲሁም የወንጌል ጫማ!!....በዚህ መረዳት ብንመላለስ እናተርፋለን፤ በህይወት ዘመናችንም የሚቋቋመን አይኖርም....ፀጋ ይብዛላችሁ!!!!!

“ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።”ዮሐንስ 10፥10

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
532 viewsYonatan Worku, edited  08:48
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-29 17:32:09 ቅባታችሁን ጠብቁ!!

እግዚአብሔር አብ ስለ ሰው ልጆች ሁሉ መዳን ወደዚህች ምድር በላከው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስናምን ከቅዱሱ ቅባትም በዚያው ቅፅበት ተቀብለናል(ተቀብተናል)፤ ወልድን መቀበል ማለት አብንም መንፈስ ቅዱስንም እንደመቀበል ነውና....ሆኖም ግን መንፈስ ቅዱስን ዕለት ዕለት እንድንሞላ ታዝዘናል.....ጥቂት ጥቅሶችን ላስቀምጥ:-

“እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።”
1ኛ ዮሐንስ 2፥20
2ኛ ቆሮ 1
²¹ በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥
²² ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው።

በዚህ ፅሁፌ ለሁለት አይነት ሰዎች መናገር እወዳለሁ....የመጀመሪያው በጌታ ኢየሱስ ላላመናችሁ ሁሉ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብታችሁ እንድትታተሙ አብ ወደ አለም በላከው ማመን አማራጭ የለውም.....በልጁ አምናችሁ ዳግም ለተወለዳችሁ ግን እንዲህ ማለት እወዳለሁ በውስጣችሁ ያለውን ቅባት ጠብቁት!!.....በጠበቃችሁትና በተንከባከባችሁት እንዲሁም ትኩረት በሰጣችሁት መጠን በህይወታችሁ ላይ የሚገለጠው ክብር ስለሚጨምር ለብዙዎች በረከትና መፅናናት መሆን ትጀምራላችሁ.....አንዳንድ ግዜ ግን ለሽሚዞቻችንና ለልብሶቻችን ለጫማዎቻችንና ለለፀጉራችን የምንጠነቀቀው ያህል እንኳ ውስጣችን ላለው መንፈስ ቅዱስ ቦታ አንሰጠውም፤ ይህም በምንሰጣቸው የግዜ ብዛት ማየት ይቻላል......በነገራችን ላይ በጣም የምንወደውን ነገር ለማወቅ ከፈለግን ብዙ ግዜያችንን የሚወስደው ምንድነው ብቻ ብሎ መጠየቅ ይበቃል......ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም አይደል የሚለው የአገሬ ሰው!!.....ለምሳሌ መንፈስ ቅዱስን በጣም እናፍቀዋለሁ(እወደዋለሁ) ብለን እያወራን ግዜ ግን የማንሰጠው ከሆነ እውነት ለመናገር የምንወደው መስሎን እንጂ አንወደውም.....በውስጣችን ላለው የእግዚአብሔር መንፈስ ከምንም በላይ ትኩረትን በመስጠት ልንወደው፣ ልንሰማው እንዲሁም ልንታዘዘው ይገባናል፤ ምክንያቱም እርሱ እውነት ስለሆነ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናልና ነው....ሃሌሉያ.....ሁሉን አዋቂና ሁሉን ቻይ የሆነው ጌታ በልባችን ላይ እያለ መንከራተትና መቅበዝበዝ አያስፈልግም.....ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋል ይስጠን!!!

“እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።”
1ኛ ዮሐንስ 2፥27

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
811 viewsYonatan Worku, 14:32
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-28 13:01:23 በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም እንድትችሉ ተቀደሱ!!

“ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ እስራኤል ሆይ፥ እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ተቀደሱ።”
ኢያሱ 7፥13

በዚህች ምድር ላይ እስካለን ድረስ ሁላችንም የምንፈተንበት ዋነኛ ጉዳይ ቢኖር ቅድስና ይባላል......በወደቀ አለም ውስጥ ይህንን አይነት የወደቀ ስጋ ለብሶ መኖር በራሱ ንፅህናችንን ለሚያስጥሉ ተግዳሮቶች እንድንጋለጥ ያደርገናል፤ በዚያ ላይ ደግሞ የሰይጣን ተንኮሎችና ማታለሎች አሉ......ቅድስና የእግዚአብሔር ባህሪይ ሲሆን የእግዚአብሔር ልጆች እንዲካፈሉት ተጠርተዋል(ታዘዋል):-

“ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።”1ኛ ጴጥሮስ 1፥15-16

“እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤”1ኛ ጴጥሮስ 2፥9

ክፉው ዲያቢሎስ ወደ ሰዎች ህይወት ሲመጣ እንደመግቢያ በር የሚጠቀመው ኃጢያትን ነው.....ለዚህ አዳምና ሔዋንን እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል.....የኃጢያት ልምምድ ያለበት ስፍራ ሁሉ ላይ ለጠላት የወደደውን ያደርግ ዘንድ ፈቃድ ይሰጠዋል፤ በቅድስና ውስጥ ግን መንፈስ ቅዱስ የበላይ ሆኖ ይሠራል....ሃሌሉያ.....ኃጢያቱን ያልተናዘዘና በልቡ ልዞ የሚዞር ሰው በሰይጣን ፊት ቆሞ ሥራውን ማፍረስ አይችልም፤ ይሄ እኮ ማለት ልክ ሳንባ ይዞ ድመትን ለማባረር እንደመሞከር ነው....በፍፁም አይታሰብም........ከጨለማ ሥራ ጋር እየተባበርን መልሰን ልንቃወመው መሞከር ድንጋይ ላይ ውኃ እንደማፍሰስ ይቆጠራል፤ ምንም የሚሆን ነገር የለም.....በጠላቶቻችን ፊት በስልጣንና በኃይል መቆምና መቃወም የምንችለው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ታጥበን ስንነፃ ብቻ ነው፤ የተቀደሰ ነገርን ጨለማ አይቋቋመውም.....እንዲህ እፀልያለሁ:-በኢየሱስ ደም ሀለንተናችን የተቀደሰ ይሁን....ወዳጆቼ ሆይ ለሽንፈታችን ምክንያት እንዳይሆንብን ከተሰወረና ከተገለጠ ኃጢያት እንራቅ.....ከአካን ታሪክ የምንማረው ይህንን እውነት ነው.....የማይገባውን ነገር በማድረጉ ለእስራኤል ሁሉ የሽንፈት ምክንያት ሆነ.....በህይወታችን በስውር የምናሳድገው የኃጢያት ልምምድ አይኑር፤ ጠርገን ከቤታችን እናስወግደው......አሊያ ነገ እባብ ሆኖ ተመልሶ ይነድፈናል፤ የውርደታችንም ምክንያት ይሆናል......ቅድስናን እንደ ልብስ መልበስ ይሁንልን!!!

“ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።”ዕብራውያን 12፥14

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
941 viewsYonatan Worku, edited  10:01
ክፈት / አስተያየት ይስጡ