2023-04-09 23:27:00
በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከአማራ ልዩ ኃይል ጋር በተያያዘ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን በሚመለከት በተከታታይ አቋሙን ግልጽ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም የአማራ ክልልን ለከፍተኛ አለመረጋጋት እና የጸጥታ መድፈረስ ያጋለጠው ፣ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው እና አደገኛ የሆነው የገዥው ፓርቲ ውሳኔ እስኪቀለበስ ድረስ እና ተገቢው መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ ድርጅታችን አብን አስፈላጊውን ጥረት እና ትግል እንደሚያደረግ ማሳወቁ ይታወቃል፡፡ ድርጅታችን አብን ሁኔታውን በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለ ሲሆን ፣ ገዥው ፓርቲ እና የፌዴራሉ መንግስት ስህተቱን ከማረም እና መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ ከጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመረ ችግሩን እያወሳሳበ እና ክልሉን ለከፍተኛ አለመረጋጋት እና የጸጥታ መደፍረስ እየዳረገው ይገኛል፡፡ በዛሬው እለትም በበርካት የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን ፣ በተለያዩ አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለው ውለዋል፡፡ በተለይም በራያ ቆቦ ከተማ ውስጥና በዙሪያው በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ተኩስ ሲደረግ የዋለ ሲሆን ይህ በከተሞች ውስጥና አቅራቢያ የሚደረግ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን።
ዛሬ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) “ከጊዚያዊ መፍትሄ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም” በሚል በስማቸው ባወጡት መግለጫ ፣ “ዘላቂ መፍትሄ” ብለው የሰየሙትን የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔ “ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ እንደሚደረግ እና የህግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወሰድ” በመግለጽ ፓርቲያቸው ያሳለፈው ውሳኔ በአማራ ክልል ለፈጠረው አለመረጋጋት እና የጸጥታ መድፈረስ ኃላፊነት ሳይወስዱ ቀርተዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ ለማድረግ ተገቢው ዝግጅት እንደተደረገበት ፣ የልዩ ኃይል አመራሮች እና አባላት እንደ ተወያዩበት ፣ የልዩ ኃይል አባላት ወደ መረጡት ተቋም (የሀገር መከላከያ ሠራዊት ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወይም የክልል ፖሊስ) ለመቀላቀል ምርጫ እንደተሰጣቸው እና ውሳኔው በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ሁሉንም የልዩ ኃይል ፖሊሶችን የሚመለከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን የማስፈጸሚያ እቅድ ነው የተባለው ሰነድ እንኳ በፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ደረጃ ውይይት የተደረገበት ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በፌዴራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት መሆኑ ሲታይ ፣ ለአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት “ትጥቃችሁን ፍቱ” ከሚል ትዕዛዝ በቀር እንኳን ምርጫ መረጃ እንኳን የሰጣቸው አካል እንደሌለ የሚታወቅ መሆኑ እና ከአማራ ክልል በስተቀር በየትኛውም ክልል ልዩ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታትም ሆነ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት “ወደ ተለያዩ ተቋማት የማስገባት” እንቅስቃሴ የሌለ መሆኑ ሲታይ ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወጡት መግለጫ እውነትነት የሌለው መሆኑን እና በድርጅታች አብን የቀደመ ግምገማ መሰረት የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማፍረስ የተላለፈው ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ የማይሆን እና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት እና መበተን መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተሩ በመግለጫቸው “የልዩ ሃይል አደረጃጀት አስፈላጊ አይደለም ማለት ፣ የልዩ ሃይል አባላት አያስፈልጉም ማለት አይደለም” ቢሉም ፣ በተግባር የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በሚመለከት ያሳለፉት ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄዱበት ያለው መንገድ የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ የሀገር አንድነትን እና ኅልውና ለማስከበር የከፈለውን መስዋዕትነት እና ግዙፍ አስተዋጽኦ የካደ ፣ በግዳጅ ላይ እና በካምፕ ውስጥ የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላትን የዕለት ስንቅ ፣ ሎጂስቲክ እና ደሞዝ ነፍጎ ለርሃብ እና ለእንግልት እንዲዳረጉ ያደረገ ፍጹም ክብረ ነክ ተግባር ሲሆን ፣ እንኳንስ ለቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮ የማዘጋጀት ፍላጎት አይደለም ዝቅተኛውን የግበረ-ገብ እና ጨዋነት መመዘኛ የማያሟላ ፣ ልዩ ኃይሉን ተስፋ በማስቆረጥ እና በማበሳጨት ለመበተን እና ክልሉን የቀውስ እና የትርምስ ቀጠና የማድረግ ተልዕኮ ያለው ውሳኔ ሁኖ አግኝተንዋል፡፡
ይህም የክልሉ መንግስት የሚቆጣጠረውን እና የሚመራውን ኃይል በመበተን ፣ በእዝ የማይመራ እና መንግስት የማይቆጣጠረውን ኃይል ለመፍጠር እና ክልሉን ወደ ቀውስ እና ትርምስ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ሆኖ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለሆነም የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ እና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳለፉትን ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄዱበት ያለ ፍጹም አደገኛ ከሆነ መንገድ እንዲቆጠቡ እና ቆም ብለው እንዲያስቡ እያሳሰብን ፣ ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን የሚከተሉትን ጥሪዎች በድጋሜ ያስተላልፋል:-
1. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔያቸውን በይፋ እንዲሰርዙ ፣ ውሳኔው ስለመሰረዙ በአደባባይ እንዲገልጹ እና የአማራ ልዩ ኃይል አባላት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ካምፓቻቸው እና ወደ ግዳጅ ቦታቸው እንዲመለሱ በይፋ ጥሪ እንዲያደርጉ፤
2. በፌዴራል መንግስቱ ውሳኔ እና ትዕዛዝ ከስራ ውጭ የሆኑት የአማራ ልዩ ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ፣ የብርጌድ እና የክፍለ ጦር አዛዦች ወደ ኃላፊነታቸው እና ምድብ ቦታቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ፤
3. የክልሉ መንግስት ለልዩ ኃይሉ አስፈላጊ የሆኑ የስንቅ እና ሎጂስቲክ እንዲያቀርብ እና ደሞዝ እንዲከፍል፤
4. በካምፕ እና በግዳጅ ቦታችሁ ላይ የምትገኙ ውድ የአማራ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ሠራዊቱ እንዲበተን የሚደረጉ ጥረቶችን እና የፕሮፖጋንዳ ጥቃቶችን በመቋቋም በተለመደው ሥነ-ምግባር ፣ ዲስፕሊን እና ጨዋነት የሠራዊቱን የእዝ ሰንሰለት አክብራችሁ እና ጠብቃችሁ ከህዝባችሁ ጎን እንድትቆሙ፤
5. ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እና አመራሮች በሙሉ በግፍ እየተጠቃ ካለው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ከአማራ ሕዝብ ጎን እንድትቆሙ እና ለግጭት ከሚጋብዙ ማናቸውም ሁኔታዎች እንድትቆጠቡ፤
6. የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የዞን እና የወረዳ አመራሮች በሙሉ በዚህ ፈታኝ ወቅት ከልዩ ኃይል ፖሊስ ሰራዊት እና ከሕዝባችሁ ጎን እንድትቆሙ፤
7. የአማራ ሕዝብ በየአካባቢው ላሉት የልዩ ኃይል አባላት አስፈላጊውን ስንቅ እና ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ድርጅታችን አብን ጥሪውን ያቀርባል።
አብን ጉዳዩን በቅርበትና በንቃት እየተከታተለው መሆኑን እየገለፀ መንግስት ውሳኔውን እስኪቀለብስ እና ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ ተከታታይ ሰላማዊ ትግል የሚያደርግ መሆኑን ያሳውቃል። ድርጅታችን አብን መላው የአማራ ሕዝብ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከሀገር ወዳዱ የአማራ ልዩ ኃይል ጎን እንድትቆሙ የከበረ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ
ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም
ቻናላችንን በመቀላቀል
ዓለም-አቀፋዊ እና አገር-አቀፍ መረጃዎችን በቴሌግራም ገፃችን ይከታተሉ።
https://t.me/wektawi1mereja
2.2K views20:27