2023-05-04 19:51:57
መጓዝ የሚመስል አቋቋም ቆመን ይሆን
Written by: Getachew. M
“ሲጀመር የሌለህን ነገር ምን እንዳይሆን ብለህ ነው የምጠብቀው? ከማንስ ነው የምጠብቀው?" መልሳ ለጥያቄየ ጥያቄ አነሳችልኝ። “አንዳንዴ እራሳችንን ለመከላከል ብለን ማንም ከጀርባ መጥቶ ሳይጥለን በራሳችን ጥላ የምንወድቅበት ጊዜ አለ!" አለችኝ።
“እኔ አሁን በዚህ ሰዓት፣ በዚች ቅጽበት የምፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው ነኒ፤....... ሰላም! የት ጋር እንዳለሁ፣ የት ደርሸ እንደቆምኩ፣ የቱ ጋር እንደጠመምኩ ማወቅ ነው የምፈልገው። ልክ አዲስ አበባን ሙሉ ገጽታዋን በቴሌስኮፕ ለማዬት እንጦጦ እንደ ሚወጣው የኔንም ፍርስራሽ ገጽታ ለማዬት የሆነ ከፍታ ላይ መውጣት ብችል ብዬ ነው የምመኘው" አሁን ግን አዲስ አበባ(እኔ) ውስጥ ካለ አንዱ ፍርስራሽ ሰፈር(አሁን ላይ እኔ) ውስጥ ነኝ እና አዲስ አበባን(እኔን) እያየኋት አይደለም። አንዳንዴ ራሳችንን ከራሳችን ወጥተን ከፍ ብለን ማዬት ብንችል እናውቀው ይሆን? እላለሁ።" ቀጠል አድርጌ “መረጃ የሚሰጠኝ ሰው አይደለም ደግሞ የምፈልገው፤... መንገድ የሚያሳየኝ፣ ከዚህ ጨለማ እጀን ይዞ የሚያወጣኝን አካል ነው የምፈልገው።" አልኳት ጠንከር ብዬ።
“አንተ ሰዎችን አይተህ እንዲሁ በማየት ብቻ ማንነታቸውን፣ ያሳለፉትን ህይወት፣ አሁን ላይ ምን እያሰቡ ምን እየተሰማቸው እንደሆነ ማወቅ ትችላለህ? መገመት አላልኩም።"
“አልችልም!" መለስኩላት። የምርም አልችልም።
“ስለዚህ ራስህን ልታውቀው ከፈለግህ እንጦጦ ወጥተህ ሳይሆን እዚህ 6 ኪሎ ግቢ (አሁን ላይ እኔ) ውስጥ ሆነህ ብትፈልገው ነው የተሻለ ልታውቀው የምትችለው። ስለዚህ ልክ ነው። ውስጥ መግባት እንፈራለን ግን ልክ ነው ብዬ አምናለሁ" አለችኝ።
“እዚህ ሆኘ መፈለጌ እኔን ጨርሶ ለማወቅ ባይበቃስ?" ጠየኳት።
“በመጀመሪያ ጨርሶ ማወቅ እንዴት ያለ ነው? ይሁን እንኳን ብንል ጨርሶ ማወቁን በምን ያውቃል ሰው? ጨርሶ ማወቅ ሚባል ነገር የለም። እዚህ ጋ ጨርሶ ስለማወቅ አይደለም ቁም ነገሩ። የተሻለ ስለማወቅ ነው።
አዲስ አበባ ኮ አስራ አንድ ክፍለ ከተሞች ነው ያሏት። ስድስት ኪሎ ቁጭ ብሎ አዲስ አበባን አውቃታለሁ ማለት የለም። እንደምታዬው (በእጇ ከድንጋይ ወደ ተሰራው የአንበሳ ቅርጽ እየጠቆመችኝ) ስድስት ኪሎ ስትሆን አንበሳ ግቢን ታውቃለህ፤ አራት ኪሎ ወረድ ብትል ደግሞ ፒኮክን ታያለህ (የሹፈት ሳቋን እየሳቀች)። “ምን ልልህ ነው እንጦጦ ላይ ሆኖ ማዬት አይደለም ቁም ነገሩ። ይሄን ከውጭ የመጣ እንግዳም ያደርገዋል። እዛ ሆኖ ስላያት ከተማዋን ያውቃታል ማለት አይደለም። ማወቅ ከፈለገ ከተማው ውስጥ መግባትና መኖር አለበት።" ምናምን ብላ ልታስረዳኝ ሞከረች።
“አሁን የምትይው ኮ ይገባኛል። እኔ የምለው ነው እማይገባሽ ነኒ። አሁን አዲስ አበባ ምናምን ብሎ ምሳሌ ማምጣት ምን ሚሉት ነው" ከልቤ ነበር ይሄን ያልኳት። (ሰው የፈለገ ሊረዳችሁ ቢሞክር የማይረዳላችሁ የሆነ ክፍል አለ።) (አንድ የልቡን ያጣ ሰው ግን ምን አግኝቶ ይደሰታል? አንዳንዴ ከቤት ወጥቶ የማያውቅን ሰው መንገድ አሳየን ብላችሁ አትጠይቁት። ጭሱን ከጠላችሁት እናንተ ራሳችሁ ከኩሽናው ውጡ።)
“ልክ ነህ።" አለችኝ ራሷን እየወዘወዘች።
“ከቅድሙ አሁን የተረዳችኝ መሰለኝ።"
“ለምን ለአሉታዊ ሃሳቦች የቀረብክ ይመስልሃል? አስበኸው ታውቃለህ?" ጠየቀችኝ።
“እናንተም ታዝዛችሁ ከሆነ ታስታውሻለሽ... ‘ኢለመንተሪ' እያለን የሳይንስ አስተማሪያችን የሆነ እጽዋት አብቅሉና የፀሀይ ብርሃን በሌለበት ቦታ አስቀምጡት ተብለን የሰራነው experiment ነበር... ያ እጽዋት ከበቀለ በኋላ እንደምንም የፀሀይ ብርሃን ወዳለበት አቅጣጫ ተጣሞ ያድጋል፤ አሊያ ይሞታል። ለምን ተጣመመ አይባልም...ከመጣመም ውጭ ያለው አማራጭ መሞት ነዋ። የሰው ልጅ ህይወት ላይም ተመሳሳይ ነገር አለ። ሰው ትናንት ያላገኘውን ብርሃን ነገ ለማየት፣ በልጅነት የጎበጠ እድገቱን ለማቅናት ሁልጊዜ ምርጫ ላይኖረው ይችላል። አየሽ ብርሃን ለማግኘትም ተጣሞ ማደግ አለ። ምናልባት ይሄ ይሆናል ምክንያቴ አልኳት።
“ጌችዬ አንተ ኮ ተስፋ ያለህ ልጅ ነህ። ተመልከተው እስኪ ዙሪያህን... ያንተ መኖር ብቻ የሚያስደስታቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ደግሞ ለመዳን ስትነሳ ቁስልህን ለማድረቅ አትሞክር፤ ዝም ብለህ ሽረቱን ኑረው። መልቀቅ ያቃተህ ብዙ ነገር እንዳለ ይሰማኛል። እስኪ ትተህ እየው ደሞ።" ማለት ስላለባት ሳይሆን የምርም እኔን ተረድታ ለመርዳት እየሞከረች ነበር። ደስ አለኝ።
“እሽ... አንችን ይዤ አያቅተኝ ይሆናል!" አልኳት። (እንደ ሰው ሰው ያስፈልገናል።)
“ብሉይ ታሪኬን ሳልጥል ወደ አዱሱ ፍስሃ የምሸጋገርበትን ኪዳን የሚጠቁመኝ ሰው ያስፈልገኛል....."
“Promise!" አለችኝ ቀድማ ፈቃድኝነቷን በፈገግታ እየገለጸችልኝ።
“አመሰግናለሁ ነኒ!" አልኳት። ተለያይተን ብሉይ ጥያቄየን እያወጣሁ እያወረድኩ ሳለሁ በመሃል... መጀመሪያ ላይ “ለውጥ ትፈራለህ ልበል?....። ንግግሮችህ መሃል መቆም ይታየኛል... በትናንት መታሰር። ለውጥም አልመለከትም። ራስህን ሌሎች ውስጥ እየፈለከው ነበር እንዴ ይሄን ሁሉ ጊዜ? ሰዎች ስላንተ የሚያስቡት ሙሉ ውሸት ነው። አንተ ያቆምከውን ጣኦት ነው ብዙ ጊዜ የሚያውቁት።" ያለችኝ አዕሞሮዬ ላይ ጫር አለብኝ። አሁን ጣፉ ተለኩሷል!
ለማት | ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ መድመቂያ ቀለም አለው!
Join us @qelemaat | @qelemaat
4.0K viewsGech, edited 16:51