Get Mystery Box with random crypto!

አለመቀበልን መቀበል Written by: Getachew - Promising | ቀለማት

አለመቀበልን መቀበል

Written by: Getachew - Promising Psychologist at AAU

ክፍል-2
....መሆንህን ስትቀበለው ደግሞ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሰው ነህ። እየህ እስር የብረት ወይም የአጥር አሊያም የገመድ አይደለም። በራሳችን አስተሳሰብ እና እምነት ነው ከውስጣችን የታሰርነው" ዝም ብዬ በትኩረት ሆኘ እያደመጥኳት ነበር። ቀጥላም

“የሰው ልጅ በብዙ ምክንያቶች በከባባድ ስሜቶች ውስጥ ያልፋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ራስን ካለመቀበል የሚመጡ የበታችነት ስሜቶች አሉ። እነዚህ ስሜቶች በጣም ገዳይ ናቸው። እንዳልኩህ በሌላ ጊዜ ደግሞ እውነትን ሽሽት ወጥተን የቆምንበት የእንቧይ ካብ ሲናድ የምንገባበት እናጣለን። መቆሚያ የለ መቀመጫ ሁሉንም እናጣለን። መቼም ሰውን እንዳይወድቅ ደግፎ የያዘው የጀርባ አጥንቱ ብቻ አይደለም። እንደዛ ብቻ ቢሆን አከርካሪው ምንም ሳይሆንበት ግን ራሱን ማጥፋት የሚፈልግ፣ ህይወት የሰለቸው፣ በሁለት እግሩ መቆም አቅቶት የሚንገዳገድ ብዙ ሽህ ሰው ዓለም ባልኖራት ነበር። ስለዚህ አካላዊ ስጋችን ራሱን ችሎ መቆምና መራመድ እንዲችል ሃይል የሚሰጠው ነገር ያስፈልገዋል። ልክ መኪና ለመንቀሳቀስ፣ አግልግሎትም ለመስጠት ነዳጅ እንደሚያስፈልገው"


“ወደ አነሳነው ሃሳብ ስመጣልህ.... ቆይ እንዳውም አንድ ምሳሌ እናንሳ.... ሁሉም ሰው ማህበረሰቡ ወይም የፋሽን ኢንዱስትሪው ያወጣውን የቁንጅና መስፈርት አሟልቶ አይገኝም። መስፈርቱ ምንም ይሁን ግን ቆንጅና ባለበት ሁሉ ፉንጋነትም አለ። ቁንጅና በሚወደስበት ፋንጋነትን አዕምኖ መቀበል ስነ ልቦናዊ ህመም አለው። ይሄም ‘ውበት ውስጣዊ ነው' የሚለውን ጥቅስ ሳይገባን ራሳችንን ለመከላከል ከመጥቀስ ይጀምራል። ውበት ውስጣዊ ስላልሆነ አይደለም ችግሩ፤ እኛ የወሰድንበት አውድ የተንሻፈፈ ሲሆን ነው። ግን የሚያተርፈን ጥቅስ መጥቀሱ ሳይሆን እውነታው ነው- The Truth!" እዚህ ደረጃ ግን በቀላሉ አይደረስም"

“ሌላኛው ነገር ደግሞ የሰው ልጅ በባህሪው ፍርሃት አለበት። ውድቀትን፣ ሀዘንን፣ መገፋትን፣ አለመፈለግን፣ ማጣትን፣ አዲስ ነገር መሞከርን ብዙ ነገር ይፈራል። ፍርሃት ደግሞ ራስን ከመጠርጠር የሚመጣ ነው። ያ ፍርሃት ራስህን እንዳትቀበል ያደርግሃል። ይሄኔ ነው አለመቀበልህን መቀበል የሚኖርብህ። የመጨረሻው ግብ ጌታቸው ብቻውን መቆም፣ ማሰብ ሲችል፤ የራሱን ልዩ'ነት(uniqueness) ሲያውቅና ያን ልዩ'ነት ስጋ አልብሶ መግለጥ መቻል ነው። እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ አይሆንም። ራስን መጠርጠር፣ የሆነውን አምኖ ለመቀበል መቸገር... ብዙ ነገር ሊከብደን ይችላል። እዚያ ለመድረስ በመንገዳችን የምናገኘው አንዱ ፌርማታ ነው እንግዲህ አለመቀበልን መቀበል። በሰዓቱ የገባህን እውነት መቀበል እንደከበደህ ማወቅ ማለት ነው። እስከ መጨረሻው ግን አይደለም። እንዳልኩህ መቀበል እስከምትችል ድረስ ነው" ብላኝ ስታበቃ....ሳልፈልግ ብዙ አስወራኸኝ ብላኝ ወደ ዶርም ለመሄድ ከተቀመጥንበት የስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ስታድዬም ተነሳች። ስታወራበት የነበረው እርጋታ እና በራስ መተማመን በየትኛው እድሜዋ ይሄን ሁሉ ነገር አስተዋለች ያስብላል። ይሄን ሁሉ ነገር ቁጭ ብለን ስናወራ አይኖቿ ወደ ውጭ አልነበረም የሚመለከቱት። ወደ ውስጥም አይመስለኝም። የሃሳቡ ድር ላይ የቆሙ ይመስለኛል።

ትንሽ በግራችን ተጉዘን ቻው ስንባባል “መች ነበር ነኒ ነኒን እንድትሆን መንገዱ ላይ ይሄ ፌርማታ እንዳለ ያወቅሽው? ማለቴ አለመቀበልሽን መቀበል እንዳለብሽ ያወቅሽው ወይም የነቃሽው?"ብዬ የምርም ማወቅ ፈልጌ ጥያቄ ወረወርኩላት።

“ምነው ነገ ምጽዓት ነው አልክሳ፤ እንገናኝ የለ' ዴ! ነገ ከክላስ መልስ የምርም ማወቅ ከፈልግህ እናወራለን ግን ያን ማወቁ አይደለም አንተን የሚጠቅምህ። በሃሳቡ አጮልቀህ እራስህን እንድታዬው እንጅ በእኔ እንድትደመም አይደለም የምፈልገው። ይሄን ታውቃለህ።"

“ነገ ምጽዓት አለመሆኑን በምን አውቃለሁ። የመዳን ቀን ዛሬ ነው..." ተሳስቀን ድጋሜ ቻው ተባብለን ተለያዬን።

ከመለያየታችን ገና “አለመቀበልህን ተቀበለው!" ብሎ አዕምሮዬ ተቀበለኝ።

ለማት | ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ መድመቂያ ቀለም አለው!

Join us 
@qelemaat@qelemaat