2023-02-08 06:35:06
+ እኔንም አስበኝ +
ዮሴፍ በበደል ላይ በደል የበዛበት ሰው ነው:: ሆድ ብሶታል:: ከሀገሩ የወጣው ፈልጎ ሳይሆን የገዛ ወንድሞቹ ሸጠውት ነበር:: ከመሸጡ በላይ በሥጋ ወንድሞቹ መጠላቱ ልቡን አቁስሎታል:: ዐሥር ወንድሞቹ ጨክነው ተስማምተው መሸጣቸውን ማሰብ ደግሞ በጣም ከባድ ነበር::
ባይተዋሩ ዮሴፍ እንደተከፋ ወደ ግብፅ ሲወርድ እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር አብሮ ተሸጠ እንጂ ብቻውን አልተወውም:: በመከፋቱ አብሮት ተከፋ:: ስለኀዘኑም አብሮት አዘነ::
ዮሴፍ ጲጥፋራ በተባለ ሰው ቤት ባሪያ ሆነ:: በአባቱ ተወዳጅ ሆኖ ላደገው ቅምጥሉ ዮሴፍ በሰው ቤት ባሪያ መሆን እጅግ ከባድ ነበር::
ሆኖም በሰው ቤት ባሪያ በሆነ ጊዜ ግን የጌቶች ጌታ የሆነው እግዚአብሔር አብሮት ነበረ:: በጌታው ፊት ሞገስ ሠጥቶት ስለነበር የቤቱ አዛዥ ናዛዥ ሆኖ ተሾመ::
እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ከሆነ ባሪያ ሆነህ ብትሸጥም ባለ ሥልጣን ትሆናለህ::
እረፍት አልባው ዮሴፍ በተሾመበት ቤት ብዙም ሳይቆይ ግን የጌታው ሚስት ለዝሙት አስቸገረችው:: እግዚአብሔር ን ፈርቶ አሻፈረኝ ሲላት ራስዋ ገርፋ ራስዋ ጮኻ እስር ቤት ጣለችው::
መከረኛው ዮሴፍ እስር ቤት ወረደ:: የታሰሩ ሁሉ ወንጀለኞች አይደሉም:: የአንዳንዶችን ኃጢአት ለመሸፈን የሚታሰሩ ንጹሐን ብዙ ናቸው::
ዮሴፍ ያለ በደሉ ሲታሰርም ብቻውን አልሆነም::
እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር አብሮ ታሰረ:: በበደል ላይ በደል ደርሶበት በገባበት ወኅኒ ቤት "እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሠጠው" ዘፍ. 39:21
እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ከሆነ እስር ቤት ውስጥም ትሾማለህ:: ዮሴፍ የወኅኒው ባለ ሥልጣን ሆነ::
ከዚህ በኋላ ዮሴፍ በወኅኒው ለሁለት ሰዎች ሕልም ይፈታላቸው ጀመር:: የአንዱ ሕልም ፍቺ "ተሰቅለህ ትሞታለህ" የሚል ሲሆን የሌላኛው ሕልም ፍቺ ደግሞ "በፈርኦን ፊት ዳግመኛ ትሾማለህ" የሚል ነበር::
ወደ ፈርኦን ቤተ መንግሥት ተሹሞ የሚሔደውን ሰው ዮሴፍ እንዲህ አለው :-
"ነገር ግን በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን አስበኝ ምሕረትንም አድርግልኝ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ:: እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና፤ ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም።" ዘፍ. 40:14
ዮሴፍ "እኔንም አስበኝ ምሕረት አድርግልኝ" ብሎ የተማጸነው የፈርኦን ጠጅ አሳላፊ ግን "ዮሴፍን አላሰበውም፥ ረሳው እንጂ" ዘፍ. 40:23
ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለሁለት ዓመታት በእስር ቆየ እንጂ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም::
ባሪያ ሆኖ ሲሸጥ አብሮት የተሸጠው እግዚአብሔር
እስር ቤት ሲገባ አብሮት የታሰረው እግዚአብሔር
አሁን ግን ዮሴፍን ዝም አለው::
ለምን?
ዮሴፍ "እኔንም አስበኝ ምሕረት አድርግልኝ" ብሎ የለመነው የጠጅ አሳላፊውን ነበር:: በግፍ ከሀገሩ እንደወጣ ያለ በደሉ እንደታሰረ ያስረዳው ለፈርኦን ቤት ሹመኛ ነበር:: ስለዚህ እግዚአብሔር "ዮሴፍ ሆይ ጠጅ አሳላፊውን አስበኝ አልክን? በል እሱ ያስብህ" ብሎ ተወው::
በሕይወትህ ሰውን አደራ ያልክ ቀን እግዚአብሔር ይተውሃል:: "አውጣኝ" ያልከው ሰውን ከሆነ ፈጣሪ የሰውን ነገር እንድታይ ዝም ይልሃል::
ሁላችንም አደራ አስበኝ ብለን የተማመንንባቸው ጠጅ አሳላፊዎች አይጠፉም:: እንደ ዮሴፍ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሰው አለኝ ብለን ተስፋ የጣልንባቸው ፣ ዘመድ አለኝ ብለን የሙጥኝ ያልናቸው ሰዎች አይጠፉም:: "በአንድ ስልክ ልጨርሰው እችላለሁ እኮ" ብለን የተመካንባቸው ሰዎች አናጣም::
ወዳጄ እመነኝ ሰው አደራ በላ መሆኑ አይቀርም:: ቃል የገባልህ ሰው ወደ ሹመቱ ሲገባ አያስታውስህም::
ሥጋ ለባሹን አደራ ብለህ ከፈጣሪህ አትጣላ::
ሰውን በቤተ መንግሥት አስበኝ ከማለት ፈጣሪን በመንግሥትህ አስበኝ ማለት ይሻላል::
"በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል" መዝ. 118:8
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 6 2015 ዓ.ም.
ዲላ ኢትዮጵያ
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
5.4K views03:35