2023-02-04 12:44:56
መዝሙረ ዳዊት 45
1. አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥
ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።
ከክፉ ነገር የምንዋጋበት ኃይላችን ብንሸሽም የምንጠጋበት ጋሻችን እግዚአብሔር ብቻ ነው:: በመጣብን ታላቅ መከራም ከእርሱ በቀር ረዳት የለንም::
2፤ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥
ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።
እግዚአብሔርን ረዳታችን መጠጊያችን ኃይላችን ብለን አምነናልና ምድር የተባሉ ሰዎች በቁጣ ቢነሡብን እንደተራራ የገዘፉ ሰዎችም ወደ ዙሪያችን ቢመጡ አንፈራም::
አንድም ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም
እንደ ተራራ ያከበርናቸው ሰዎች ክብራቸውን ትተው ባሕር ወደ ተባለች ወደዓለም ውስጥ ጭልጥ ብለው ቢገቡና ራሳቸውን ቢያዋርዱ አንፈራም
እንደ ተራራ የገዘፈ የእምነት ጽናት ያላቸው ሰዎች ቢክዱ በባሕር ክህደት ልብ ቢወሰዱ አምላካችን ኃይላችን መጠጊያችን ነውና አንፈራም::
ተራሮች አባቶች ከእምነት ቢናወጹ
ወደ ባሕር ልብ ውስጥ ሸፍተው ቢሔዱ ቀድሞም መጠጊያችን አምላካችን ነውና አንፈራም::
3፤ ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥
ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ።
ጉልበተኞች በቁጣ ተነሡ መጡ መጡ ሲባል ሰምተን ነበር:: ኃያላን ሁሉ ከእግዚአብሔር ኃይል የተነሣ ፈራርሰዋል::
በየዘመናቱ ብዙዎች በቁጣ ተነሥተውብን ነበረ:: የሚያምንን ሰው ዓይኑን አያሳየኝ ብለው ጮኹ ተናወጡም:: ሆኖም ልባቸው እንደ ተራራ ያበጠ ሁሉ ኃይላችን መጠጊያችን ረዳታችን በሆነው በእግዚአብሔር ተናወጡ::
4: የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።
መከራ እንደወንዝ ቢፈስስባት የእግዚአብሔር ከተማ ቤተ ክርስቲያን አዝና ተከፍታ አታውቅም::
የመከራ ፈሳሾች ቤተ ክርስቲያንን ደስ ያሰኙአታል::
ልጆችዋን የሚያጠነክርላት ወደ ቤቱ የሚመልስላት
በንስሓ የሚያጸዳላት በሰማዕትነት አክሊል የሚያከብርላት ነውና የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ቤተ ክርስቲያንን ደስ ያሰኛሉ::
እንደ ወንዝ ከሰማይ ወደ ምድር የሚወርዱ መላእክትም ቤተ ክርስቲያን በጥበቃቸው ደስ ያሰኙአታል::
ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያው ቤተ ክርስቲያንን ለየ:: በመከራዋ ደስ የምትሰኝ ስለ ቁስልዋ የምትዘምርና ሐሴት የምታደርግ ቤቱን ከዚህ ዓለም ክፋት ሁሉ ለየ::
5፤ እግዚአብሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም፥
እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳታል።
የምትናወጽ የምትበጠበጥ ይመስላል እንጂ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በመካከልዋ ነውና አትናወጥም::
"ጥበቃዬን አንሥቻለሁ" የማይል አምላካችን እግዚአብሔር አምላክዋ ነውና አትናወጥም:: በእሳት ሠረገላ ዙሪያዋን የሚከብባት በማይተኛ አምላክ የምትጠበቅ ናትና አትናወጥም::
6፤ አሕዛብ ተናወጡ መንግሥታትም ተመለሱ፤
እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች።
ቤተ ክርስቲያንን የናቁ ሁሉ ከክብራቸው ተዋረዱ
በቁጣ የተነሡባት ሁሉ ወደ ኋላቸው ተመልሰዋል::
ዝም ያለ የሚመስለው አምላክ ስለ ቤተ ክርስቲያን እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች።
7፤ የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤
የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።
በምድር ካሉ ሠራዊት ሁሉ የሚበልጡ መላእክት ጌታቸው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው::
ብንሸሽም መጠጊያችን እሱ ነው::
8፤ የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ።
እግዚአብሔር በሰማይ ብቻ ያለ ይመስላችሁ እንደሆነ በምድርም የሚሠራውን ድንቅ ነገር ታዩ ዘንድ ኑ::
9፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነት ይሽራል፤
ቀስትን ይሰብራል፥ ጦርንም ይቈርጣል፥
በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።
የምንነደፍበትን ቀስት ሰብሮ የምንወጋበትን ጦር ቆርጦ ከጋሻ ጋር ያቃጥላል:: ጦርነትም ይሻራል:: ኃይላችን እርሱ ነውና ጦር አንሻም:: ጋሻችንም እርሱ ነውና::
10፤ ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤
በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል :- ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤
በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥
በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።
11፤ የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤
የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥር 27 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
1.7K views09:44