2023-05-05 08:11:06
የአርበኞች ድል ቀን መታሰቢያ በዓል
አርበኝነት በኢትዮጵያ ታሪክ በደማቅ ቀለም የተጻፈው ከ1928 ዓ/ም በኋላ ነበር፡፡ በዘመኑ ጣሊያን በ1888ዓ/ም በዳግማዊ ምኒልክ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር በዓድዋ ያደረሰባትን መራር ሽንፈት ለመበቀል 40 ዓመታትን ስትዘጋጅ ከርማ ለመላው የጥቁር ሕዝብ እንደ ነጻነት ምልክት ተደርጋ የምትታየውን ኢትዮጵያን ወረረች፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብም በአንድነት የጣሊያንን ወረራ ለመከላከል ጨርቄን ማቄን ሳይል ተነሳ፡፡ በሰሜን እና በምስራቅ በተካሄዱ ጦርነቶች ግን ኢትዮጵያዊያን እንደ ዓድዋው ድል አልቀናቸውም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በተሳተፉበት የማይጨው ጦርነትም ድል አልተገኘም፡፡
ያም ሆኖ ኢትዮጵያዊያን በመድፍ እና በአውሮፕላን መርዝ በታገዘው የጣሊያን ጦር ተሸነፍነ ብለው ተስፋ አልቆረጡም፤ እጅም አልሰጡም፡፡ የሀይማኖት አባቶች “እንኳን ሕዝቡ የኢትዮጵያ ምድር ለባዕድ እንዳይገዛ” አውግዘው ውድ መሰዋዕትነት ከፈሉ፡፡ ቆራጦችም የአርበኝነት ትግል ለማካሄድ ዱር ቤቴ አሉ፡፡
በዚህም እንደ እጃቸው መዳፍ ጠንቅቀው የሚያውቁትን የአገራቸውን መልክዓ-ምድር መመኪያ አድርገው ጣሊያንን ይፋለሙ ጀመር፡፡ ከመኳንንቱ እና ከመሳፍንቱ በተጨማሪ ብዙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የአርበኝነት ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡
በበጌምድርና አካባቢው ራስ ውብነህ ተሰማና ቢትውደድ አዳነ፤ በጎጃም ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ በላይ ዘለቀ(አባ ኮስትር)፣ ደጃዝማች ኃይለየሱስ ፍላቴ እና ራስ ኃይሉ በለው፤ በሸዋ ራስ አበበ አረጋይ፣ መስፍን ስለሺ ፀሐይ ዕንቁሥላሴ፤ የበሼ ቤተሰቦች ደጃች ተሾመና አበበ ሽንቁጥ፤ በወሎ እነ ኃይሉ ከበደ፣ ወሰን ኃይሉ እና በሌሎች የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ አርበኞች ሕዝቡን በማስተባበር ጣሊያንን ለአምስት ዓመት የረገጣት የኢትዮጵያ ምድር ረመጥ እንድትሆንበት አደረጉ፡፡
ከአምስት ዓመት ተጋድሎ በኋላም ጣሊያን ድጋሜ የሽንፈትን ጽዋ ተጎነጨ፡፡ አርበኞች በዱር በገደሉ፣ የውስጥ አርበኞች በከተማ እና ንጉሠ ነገሥቱ በውጭ ባካሄዱት የዲፕሎማሲ ትግል ወድቃ የነበረችው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተነሳች፡፡ ሚያዚያ 27/1933 ዓ/ም ድጋሜ በኢትዮጵያ ሰማይ በነጻነት ለመውለብለብ በቃች፡፡ ኢትዮጵያም ድጋሜ በነጻነት ደምቃ ታየች፡፡
ይህ የአርበኞች ድል መታሰቢያ በዓልም ሁሌም ሚያዚያ 27 ይከበራል፡፡ ዘንድሮም የአርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በመጭው አርብ ለ82ኛ ጊዜ በድምቀት የሚከበር ይሆናል፡፡
ጃንሆይና ሚያዚያ 27 ቀን ያደረጉት ንግግር
አሁን በመጨረሻው ለናንተ ለህዝቤ የማስታውቃችሁ ዛሬ የሁላችን የደስታ ቀን መሆኑን ነው።ዛሬ ጠላታችንን ድል የመታንበት ቀን ነው።ስለዚህ በሙሉ ልባችን ደስ ይበለን ስንል ደስታችን በክርስቶስ መንፈስ እንጂ በሌላ አይሁን።
ለክፉ ክፉ አትመልሱ። ጠላት እንደ ወትሮው ልማድ እስከዚህ መጨረሻ ሰዓት ድረስ እንደሰራው ያለ የጭካኔና የግፍ ስራ አትስሩ።ጠላታችን መውቀሻ በሚሆነው ነገር የኢትዮጵያን መልካም ስም እንዳታሳድፉ ተጠንቀቁ።
ጠላቶቻችን በእጃቸው ያለውን መሳሪያ እንዲያስረክቡና በመጡበት መንገድ ተመልሰው እንዲሔዱ እናደርጋለን።
**ይህ ቃል ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሚያዚያ 27/1933 በድል አድራጊነት ወደ መናገሻ ከተማቸው ሲገቡ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው።አፄ ሚንሊክ መቀሌ ላይ በጣይቱ መላ የማረኳቸውን በቅሎ ሰተው እንደሸኙት ሁሉ አፄ ኃይለስላሴም በዚህች ቀን ህዝባቸው ከበቀል ተግባር እንዲታቀብ አውጀው ነበር።ይህ አዋጅ ባይታወጅና ምድሪቱም የደግ ህዝቦች ምድር ባትሆን ከተሰራብን ግፍ አንፃር ኢትዮጵያ በነበሩት ጣሊያኖች ላይ ስንት ነገር በደረሰ ነበር።
ኢትዮዽያ የአስተዋይ ነገስታት እና የጨዋ ህዝብ ምድር።ክብር በደምና አጥንታቸው ዋጋ ነፃነትን ላወረሱን አባቶች።መልካም የአርበኞች ቀን ።
"ማንበብ ፋሽን ነው።"
Join us @noahbookdelivery
1.2K viewsኖኀ መፅሐፍ, 05:11