2023-04-04 08:31:30
ቋንቋ እና ሃይማኖትበሮማውያን ዘመን ላቲን Latin (ሮማይስጢ) ሰውንና እግዚአብሔር ማግባባት የሚችል ብቸኛ ቋንቋ እንደሆነ ስለሚታሰብ ፤ ቃላዊ ሆነ ጽሑፋዊ ውዳሴ አምላክ ከላቲን ቋንቋ ውጪ ቢቀርብ "ባዶ ጩኸት" ነው ተብሎ ይታመን ነበር።
በዓረቡም ዓለምም ቢሆን የእሰልምናው ሥርዓተ አምልኮ፤ 'ሶላቱም' ሆነ ትምህርቱ በዐረብኛ ቋንቋ መቅረቡ መንፈሳዊ ዕሴት እንዳለው ስለሚታመን ቋንቋውን በማይናገሩ ሀገሮች ሳይቀር ሥራ ላይ ሲውል እንመለከታለን።
ይህ አስተሳሰብ በእኛም ሀገር ለብዙ ዘመናት ሰፍኖ መቆየቱ አያጠያይቅም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጸሎቱና ማኅሌቱ፣ ውዳሴውና ቅዳሴው ከግእዝ ቋንቋ ውጪ በሌላ ቋንቋ ቢቀርብ እንደዓለማዊ ጉዳይ የሚቈጠርበት ሁኔታ ነበረ።
ለምሳሌ በድሮ ጊዜ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዳይሰጥበት አንዳንድ አባቶች ይከላከሉ እንደነበር አንድ ትውስታ ነው።
ከዚህም ሌላ በዐሥራ ዘጠኝ ኀምሳዎቹ መጨረሻ (1950's) አካባቢ ባንዳንድ የክፍለ ሀገር ከተሞች በ"ክብረ ተዋሕዶ" ወይም በ"ሃይማኖተ አበው" መዋቅር ሥር የተቋቋሙ ወጣቶች በቤተክርስቲያን ተሰባስበው የአማርኛ መዝሙሮችን መዘመር ሲጀምሩ ጊዜውን የታዘቡ ሰዎች ነበሩ።
ይህን ሁሉ የተነሣው፤
ልሳነ ግእዝ ከሃይማኖት ጋር መተሳሠሩ ያስገኘለት ፋይዳ አለ? ወይስ የለም? የሚለውን ለመመለስ ነው።
ቋንቋ ለሃይማኖት መስፋፋት፣ ሃይማኖት ለቋንቋ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል አለመሆኑን ሁሉም ሰው ይገነዘባል። የግእዝ ቋንቋ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ብሔራዊ ቋንቋነት ሊያድግ የቻለ ከዐራተኛው ምእተ ዓመት (301 - 400) አጋማሽ ጀምሮ ባብዛኛው ጉዳያቸው ሃይማኖታዊ የሆነ ትርጉም ሥራዎች ስለተሠሩበት ነበር።
የሃይማኖትና የቋንቋ ቁርኝት ጥቅምም ድክመትም እንዳለው መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ዐረብኛ ቋንቋ ከሰባተኛው ምእተ ዓመት (601-700) ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ግለቱ ሳይበርድ እምነቱን እያስፋፋ እሱም አብሮ እያደገ ነው። ላቲን እና ግእዝ ግን አልቀናቸውም።
መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝኛ እና በሌሎችም የአውሮፓ ቋንቋዎች መታተምና መሰበክ ሲጀምር ላቲን እየተዳከመ እንደመጣ ሁሉ ፤ የኛው ግእዝም አማርኛ የጽሑፍ ቋንቋና የሃይማኖት መስበኪያ እየሆነ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የላቲን ፈንታ ደርሶበታል። ይቀጥላል...◌◌◌□▢🪻
መሠረተ ፡ ግእዝ🪻▢□◌◌◌
@MesereteGeez ◦ @MesereteGeez
@MGeez24
1.8K viewsedited 05:31