2023-06-18 13:48:02
ነገ ሰኞ June 19/ ሰኔ 12 ወይም ማክሰኞ የዙል-ሒጃ ወር ብሎ ይጀምራል። አላህ ካላቃቸው እና ካከበራቸው አራት ወራቶች መካከል የዙልሒጃ ወር አንዱ ነው።
ከቀናቶች ሁሉ ብልጫ ያላቸው አስር ቀናቶችም ያሉት በዚሁ በተከበረው የዙልሒጃ ወር ውስጥ ነው። በዚህ የዙል-ሒጃ ወር ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ከዱንያ ቀናቶች ሁሉ በላጭ ናቸው።
በእነዚህ ቀናቶች የሚሰራ መልካም ስራ ከሌሎቹ ቀናቶች ከሚሰሩ መልካም ስራዎች በእጥፍ ድርብ ይበልጣል። መልካም ሥራ ከዙል-ሒጃ አሥርቱ ቀናት በልጦ አላህ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነበት ቀናት የለም።
ለዛሬ ስለ ዙል–ሒጃ አሥርቱ ቀናትና በውስጡ መሰራት ስለሚገባቸው መልካም ስራዎች እናኛለን፡-
ሁሌም ቢሆን ስለ ዲናችን ወቅቱን የጠበቀ ትኩረት ሊኖረን ይገባል። ረመዳን ሲመጣ ስለረመዳን፣ በሐጅ ወቅት ስለሐጅ ወዘተ ብናተኩርና ብንማማር በዚያ ጉዳይ የበለጠ እንድንጠቀም ያደርገናል።
እነዚህ ቀናቶች ከዱንያ ቀናት ሁሉ በላጭ ናቸው፣ ረሱላችን (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- "ከዱንያ ቀናቶች ሁሉ በላጩ (የዙል-ሒጃ) አሥሩ ቀናት ናቸው”። ( ሶሒሕ አል-ጃሚዑ ሰጊር 1133)
በእነዚህ ቀናቶች የሚሰራ መልካም ስራ ከሌሎቹ ቀናቶች ከሚሰሩ መልካም ስራዎች በእጥፍ ድርብ ይበልጣል ለዚህም ረሱል (ﷺ) በእነዚህ ቀናቶች የሚሰሩ መልካም ስራዎች አላህ ዘንድ በሌሎች ቀናቶች ከሚሰሩ ስራዎች የበለጠ ተወዳጅ እንደሆነ እንድህ ሲሉ ተናግረዋል፡-
ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ነቢዩ (ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ማለታቸውን አስተላልፈዋል፡-
«አላህ ዘንድ መልካም ስራ ተወዳጅ የሆነበት ከእነዚህ አስር ቀናቶች የበለጠ ማንም ቀን የለም። ሶሐቦች አንቱ የአላህ መልእክተኛ ሆይ በአላህ መንገድ መታገል (ጅሃድ እንኳ) ቢሆን አሉ፣ ረሱልም (ﷺ)፡-
«በነፍሱም በገንዘቡም ጅሃድ ወጥቱ ከእርሱ በምንም ያልተመለሰ ሰው ሲቀር በአላህ መንገድ ላይ መታገል (ጅሃድ) እንኳ ቢሆን (በእነዚህ አስር ቀናቶች ከሚሰራ መልካም ስራ አይበልጥም)» አሉ። (ቡኻሪ (2/457) እና ሌሎችም ዘግበውታል)
በነዚህ በተከበሩ ቀናቶች ወንጀልን መራቅ አለብን፣ ኢብኑ ረጀብ እንድህ ይላሉ:-
«ወንጀልን ተጠንቀቁ እርሷ በሚታዘንባቸው አጋጣሜዎች መሀርታን ትከለክላለች» «ወንጀል (አላህን ማመፅ ከአላህ እዝነት) የመራቅ እና የመባረር ሰበብ ስለሆነች ተጠንቀቁ» (ለጧኢፉል መዓሪፍ (254)
በእነዚህ ቀናቶች ውስጥ ሁሉም መልካም ስራ ይወደዳል ስለዚህ ከእነዚህ መልካም ስራዎች የተገራልንን በመስራት የብዙ አጅር ባለቤት ለመሆን እንጣር። ይህ በእኛ ላይ የተዋለለን የአላህ ትልቅ ኒዕማ እንደሆነ ማወቅ እዚህ ትልቅ ኒዕማ ላይ ጤና እና እድሜ ሰጥቶን በሰላም ከደረስን ይህን ኒዕማ ሳናባክን ሌሎችን በሞት ወይ በበሽታ እንዳለፋቸው እኛንም የሚያልፍብን ቀን ሳይመጣ የተሰጠን እድል ሳያልፍ በአግባቡ እንጠቀም
በእነዚህ ቀናት ከሚሰሩ መልካም ስራዎች መካከል፡-
ሐጅና ዑምራህ፡-
ሐጅ ማድረግ በነዚህ ቀናት ውስጥ ከሚፈጸሙ መልካም ስራዎች መካከል ሐጅ ማድረግ ይገኝበታል፤ በነዚህ አስር ቀናት አቅሙ ለቻለ ሰው የሐጅ ዒባዳ ላይ ተገኝቶ በተገቢው መልኩ ከፈጸመው በአላህ ፍቃድ ክፍያው ጀነት ነው
"ዑምራህ ቀጣዩ አመት ዑምራ እስኪመጣ ድረስ (በመሃል ለተፈጸሙ ጥቃቅን ኃጢአት) ማስተሰረያ ነው፣ ትክክለኛ ሐጅ ደግሞ ከጀነት ውጪ ክፍያ የለውም”። (ቡኻሪና ሙስሊም)
ጾም፡-
የፈለገ ሙሉውን ዘጠኝ ቀን፣ ካልሆነም የቻለውን ያክል መጾም ይችላል
"መልካም ስራ ከዙል-ሒጃ አስርቱ ቀናት በልጦ አላህ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነበት ቀናት የለም፡፡" በዚህ ሐዲሥ መሠረት ጾም "መልካም ሥራ" የተባለው ሐዲሥ ውስጥ ስለሚካተት በጾሙ የቻለውን ያክል መበርታት
በዙል-ሒጃ ወር 9ኛው ቀን፣ የዐረፋ ቀን ነው፣ አቢ ቀታዳህ እንዳሉት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡-
"የዐረፋ ቀን ጾም የሁለት ዐመት (ያለፈውንና የሚመጣውን) ኃጢአት ያስምራል" (ከቡኻሪ በስተቀር ሁሉም የዘገበው)
አላህን ማውሳት፡-
ዚክር ማብዛት: አልሐምዱሊላ ተክቢር (አሏሁ አክበር) ተሕሊል (ላኢላሀ ኢለላህ) ተስቢሕ (ሱብሓነላህ) እና ቁርኣን መቅራትን ማብዛት። ኢባዳዉን ለማስታወስና የአላህን ስም ከፍ ለማድረግ በተለያዩ አጋጣሚዎች ድምጽን ከፍ አድርጎ እነዚህን ዚክሮች ማድረግ ይወደዳል
ዐብደላህ ኢብኑ ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ባስተላለፉት ሐዲሥ ላይ ነቢዩ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ ብለዋል፡-
"በነዚህ ቀናት ውስጥ ተህሊል (ላ ኢላሀ ኢልለሏህ)፤ ተክቢር (አላሁ አክበር)፤ ተሕሚድ (አል-ሐምዱ ሊላህ) ማለትን አብዙ" (አህመድ 7/224)
ዐብዱላህ ኢብኑ ኡመር እና አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁም) ወደ ገበያ በመውጣት በተክቢራ ሲያሞቁት ሰዎቹም እነሱን ተከትለው ተክቢራ ይሉ ነበር (ኢርዋዑል-ገሊል: አልባኒይ 651)
በእነዚህ ቀናት እኔን አስታውሱባቸው ብለዋል አላህ፡-
۞ "ለነሱ የሆኑ ጥቅሞችን ይጣዱ ዘንድ፣ በታወቁ ቀኖችም ውስጥ ከማለዳ እንሰሳዎች በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ፣ (ይመጡሃል)፤ ከርሷም ብሉ፤ ችግረኛ ድኻንም አብሉ።" ۞ ( ሱረቱል-ሐጅ 28)
"የታወቁ ቀኖች" የተባሉት እነዚሁ አሥርቱ ቀናት እንደሆኑ ሙፈሲሮች ያስረዳሉ፡፡ ታዲያ አላህን በማንኛውም ጊዜ ማውሳትና ማወደስ ከመቻሉ ጋር በነዚህ ቀኖች አወድሱት ብሎ ቀኖቹን ለይቶ መጥቀሱ የተለየ ደረጃና ክብር እንዳላቸው ይጠቁማል
ተውበት ማብዛት፡-
۞ "…ምእምናኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ (በመመለስ) ተጸጸቱ።" ۞ ( ሱረቱል አሕዛብ 31)
መልካም ሥራዎችን ማብዛት፡-
በኢስላም የመልካም ሥራ በሮች ብዙ ናቸው፡፡ ተቆጥረው አይዘለቁም፡፡ ከኛ የሚጠበቀው ስራው ላይ ተሳታፊ መሆን ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምረን እሰከ ሩቅ ሰው ድረስ አቅማችን የቻለውን ያህል በመርዳት ወደ አላህ እንቃረብ።
ኡዱሕያ፡-
በነዚህ አስር ቀናት ከተወደዱ ተግባሮች መካከል ኡድሂያን በማረድ ወደ አላህ መቃረብ ነው። ኡድሂያን ለማረድ ያቀደ ሰው የዙልሂጃ ወር ከገባ ጥፍሩንና ጸጉሩን መቁረጥ የለበትም።
የኡድሑይያህ የእርድ ቀናት ከዒዱ ቀን ሶላት መጠናቀቅ ጀምሮ (የውሙ–ነሕር 10ኛው ቀን ማለት ነው) እስከ አያሙ–ተሽሪቅ የመጨረሻው ቀን (11፣ 12 እና 13ኛው ቀን ፀሀይ መግባት ድረስ) የሚቆይ ይሆናል
በዒባዳህ መጠናከር፡-
ነፍል (ትርፍ ግዴታ ያልሆኑ) ዒባዳዎችን ማብዛት ለምሳሌ ሱና ሶላቶችን ማብዛት፤ ቁርኣንን ማንበብና ማዳመጥ
ከሐራም መቆጠብ፡-
ከላይ የተጠቀሱት መልካም ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የአላህን ተውፊቅ ያላገኘ ሰው ቢያንስ ከወንጀል ይታቀብ። እሱም ትልቅ ተውፊቅ ነውና
በነዚህ ውድ ቀናቶች ከተጠቀሱት ውጪ ያሉትንም መልካም ስራዎች በሙሉ መስራት ምንዳው ላቅ ያለ ነው። ከመልካም ፈገግታ ጀምሮ በኸይር ስራ ሚዛን ላይ ሊያመዝንልንና ሊጠቅመን የሚችልን ነገር ከመተግበር ወደ ኋላ አንበል።
http://t.me/khalidzemen
1.9K views10:48