2023-04-27 10:34:19
በተወሰኑ ሰዎች/ብሄረሰቦች ዘንድ ከረመዷን ዒድ ማግስት ጀምሮ ለተከታታይ 6 ቀናት የሸዋልን ጾም ይጾሙና ሰባተኛውን ቀን (ሸዋል 8) ሸዋል ዒድ ወይም ትንሹ ዒድ በማለት ዐመት እየጠበቁ ያከብሩታል
የሸዋል/ትንሹ ዒድ የሚባለው መሰረት የለውም እና እንደ-ዒድ አድርገው የሚይዙ ሰዎችን ማስተማርና ማስገንዘብ ይጠበቅብናል፡፡
ሊታወቅ የሚገባው ነገር ከዒዱል ፊጥር ማግስት ጀምሮ በተከታታይ የሸዋልን 6 ቀናት የጾመ ሰው በቀጣዩ ቀን መብላት መጠጣት አይችልም ማለት አይደለም፡፡ ሰውየው ጾሙን እስካጠናቀቀ ድረስ መብላት መጠጣት ይችላል፡፡ ዋናው ነገር በቀኑ ላይ ሲበላም ሆነ ሲጠጣ ቀኑን ዒድ ነው ብሎ እንዳይመለከተውና እንደ-ዒድ አድርጎ እንዳይዘው ነው፡፡
የሸዋል/ትንሹ ዒድ ከሚያከብሩበት ምክንያቶች ውስጥ የተወሰነው ይህን ይመስላል፡-
የዒዱል-ፊጥር ቀን አንድ ቀን ስለሆነና በነጋታው ተመልሰን ወደ ሸዋል ጾም ስለምንገባ ነው፡፡ ስለዚህ ባሉት ተከታታይ 6 ቀናት የሸዋልን ጾም በመጾም ረመዷንንም ሸዋልንም እንጨርስና 7ተኛው ቀን ጀምሮ በደንብ ዒዱን እናከብራለን፡፡ እንበላለን እንጠጣለን፡፡ ጎረቤት፣ ጓደኛ፣ ዘመድ እንጠይቃለን፡፡ ብዙ ቀናቶች አሉንና፡፡
ከዚህ ምክንያት መረዳት እንደሚቻለው ሰዎቹ የዒዱል-ፊጥር ቀን አንድ ቀን ብቻ በመሆኑ በሰፊው ለመብላትና ለመጠጣት፣ ከዘመድ ጋር ለመዘያየር አይበቃም የሚል ነው
እዚህ ጋር ሊታሰብባቸው የተገቡ ጉዳዮችን ቀጥሎ እናኛለን፡-
የሸዋል ስድስት ቀናት ጾም በመጀመሪያዎቹ የሸዋል ቀናቶች ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ሸዋል ሙሉ አንድ ወር 29/30 ነው፡፡ ስለዚህ ከወሩ ውስጥ የሚመቸውን ቀን መርጦ በማከታተልም ሆነ በማፈራረቅ ሸዋልን መጾም ይቻላል፡፡
እናም የደስታውን ቀን ማርዘም የሚፈልግ ከዒዱል-ፊጥር በኋላ ያለውንም ቀን መጠቀም ይቻላል፡፡ በቀሩት ቀናት ደግሞ ሸዋልን መጀመር ይቻላል፡፡
የሆኑ ሰዎች ልክ እንደ መደበኛ ዒድ ቋሚ ልምድ አድርገው ሳይዙ በሆኑ ቀናቶች ላይ ቢሰባሰቡ ይሄ አይጠላም። ነገር ግን ወቅት በዞረ ቁጥር አብሮ የሚዞር ልምድ አድርጎ መያዙ የተጠላ ነው። ሸሪዐን መቀየር እንዲሁም የተደነገገውን ካልተደነገገው ጋር ማመሳሰል አለውና።
ይህ የሸዋል ዒድ ተብሎ በሰዎች የተወሰነው ቀን፣ በዘልማድ ሲተገበር ቆይተዋል፣ አሁንም በአንዳንድ አከባቢዎች በሰፊው ሊከበር ዝግጅት እየተደረገ ነው። ይህም በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ ስድስቱ የሸዋል ቀኖች መጾም ያለባቸው ከዒድ ማግስት ጀምሮ - ማለቅ ያለበት ደግሞ በሸዋል 8 እንደሆነ በሙስሊሙ ዘንድ አምኖ እንዲቀብል ሆነዋል
ይህ ደግሞ ሰዎች ሸዋልን እንዳይጾሙ አንዱ ምክንያት እየሆነ ነው፣ ሰው በረመዳን የደከመውን ሰውነቱን ማሳረፍ፣ መብላት መጠጣት በሚፈልግበት ሰዐት ጾም መጾሙ ከባድ ይሆንበታል፣ ወሩ ሳይወጣ በተለያየ ቀን በማፈራረቅ መጾም እንደሚቻል በዚህ የሸዋል ዒድ ምክንያት ተዘንግተዋል።
የኢስላም ሃይማኖት እንዳስተማረን ከሁለቱ ዒዶች (ዒዱል ፊጥር እና ዒዱል አድሓ) ውጪ፣ ሙስሊሞች ሌላ ዒድ የላቸውም፡፡ የአላህ መልክተኛ ከደነገጉት ውጪ አዲስ ስርአትን መደንገግ በሃይማኖቱ ላይ መጨመር ነው፡፡
የሸዋል መጀመሪያ ቀን ዒዱል ፊጥር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዒድ ደግሞ የመደሰቻ፣ የመብያና የማብያ፣ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት መለዋወጫ ቀን ነው፡፡ ግን በመጀመሪያው ቀን ብቻ ይህን ማድረግ የሚቻለው ያለው ማነው?
የሸዋልን ሁለተኛና ሶስተኛ ቀናትስ መብላትና ማብላት፣ መዘያየር አይቻልም?
ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የነገሩን ዓመታዊ በዓል ሁለት ብቻ ናቸው። እነርሱም ዒዱል ፊጥር እና ዒዱል አድሓ ናቸው
አነሥ ኢብኑ ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ፡-
"የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መዲና ሲገቡ የመዲና ሠዎች የሚደሰቱባቸው ሁለት በዓላት እንዳሏቸው አወቁ። እርሳቸውም እነዚህ ሁለቱ ቀናት ምንድን ናቸው? በማለት ጠየቁ፣ ሰዎችም በጃሂሊያ ጊዜ እንጫወትባቸው የነበሩ በዓላት ናቸው አሏቸው።
የአላህ መልእክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) “አላህ ከእነርሱ የተሻሉ ሁለት ዒዶችን ሠጥቷችኋል እነርሱም፡- ዒዱል ፊጥር እና ዒዱል አድሓን" አሏቸው
(ሡነን አቢ ዳዉድ መጽሐፍ 2, ሐዲስ 745)
አሏህን በብቸኝነት አምልከን፣ የመልእክተኛውን ፈለግ ተከትለን የምንሞት ባሮቹ ያድርገን! አሚን
በሸዋል ዒድ ዙርያ የግንዛቤ እጥረት ስላለ ሼር በማድረግ ለእህትና ወንድሞች እንዲደርሳቸው ያድርጉ
ቴሌግራም t.me/khalidzemen
851 views07:34