2023-05-04 16:19:05
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ
በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ሥነ-ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ከአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ ጋር በመተባበር ለዘርፉ የጉልበት ሠራተኞች በሥራ ሥነምግባር፣ በሙስና ወንጀል የህግ ድንጋጌዎች እና በምርት ጥራትና እንክብካቤ ዙሪያ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከሚያዚያ 24-25/ 2015 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
በዚህ ስልጠና ላይ በመገኘት የሥራ ምንነት፣ የሥራ ሥነ-ምግባር ምንነት፣ የሥራ ሥነ-ምግባርን በመላበስ መስራት ያለው ፋይዳ፣ የሥራ ሥነምግባር መርሆዎች/ባህርያት፣ ሥነምባራዊ/ግብረገባዊ እንከኖች፣ የሥራ ሥነምግባር አለማክበር የሚያስከትለው ጉዳትና ሥነምግባርን ተቋማዊ ለማድረግ የሚያግዙ መንገዶች በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የሰጡት የኮርፖሬት ሥነምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከድር ጀማል ናቸው፡፡
በዚህ ዕለት የተሰጠው ሌላው ስልጠና የወንጀል ህግ ዓላማ፣ በወንጀለኛ ህጉ ላይ የተቀመጡት 23 የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ምንነትና የሚያስከትሉት የቅጣት ዓይነት እንዲሁም የሙስና ወንጀል ድርጊት ምንነትና የቅጣት ዓይነቶች በተመለከተ የህግ ግንዛቤቸው እንዲዳብር ስልጠና የሰጡት የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ባለሙያ አቶ አዲስዓለም አድማሱ ናቸው፡፡
በምርት ጥራትና እንክብካቤ ዙሪያ ስልጠና የሰጡት ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ የምርት ጥራት ቡድን መሪ አቶ ሳለጌታ ሲሆኑ የጉልበት ሠራተኞች ምርቶች ወደ መጋዘን ውስጥ በሚያስገቡበት ወቅት ማድረግ የሚገባቸው የምርት አቀባበል፣,አያያዝ፣ አደራደር አሠራሮች እንዲሁም በምርት ሥርጭትና ብልሽት አወጋገድ ሂደት መከናወን የሚገባቸው የአሠራር ሥርዓቶችን በተመለከተ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በአሠራርና በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመለከተ ከጉልበት ሠራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት በዘርፍ ደረጃ መስተካከል ያለባቸው የአሠራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማስተካከል ዘርፉ ዝግጁ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን የጉልበት ሠራተኞች በበኩላቸው የድርጅቱን ሀብትና ንብረት በአግባቡ በመያዝና በመጠቀም እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል በጋራ እንደሚሰሩ መግባባት ላይ በመድረስ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡ በዚህ ስልጠና ላይ የዘርፉ 58 የጉልበት ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
337 views13:19