2023-06-11 21:35:43
#Update #ባህርዳር
" ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ልዩነቶቹ ከአማራ እና ትግራይ ሕዝብ በታች ናቸው " - አቶ ጌታቸው ረዳ
" ልዩነቶችን በሕግ፣ በሠላም እና በመነጋገር መፍታት የአማራ ሕዝብ ፍላጎት አለው " - ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
ባህር ዳር የሚገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ልዑካቸው ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ጋር እንዲሁም ከህብረተሰቡ ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በዚህ ውይይት ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ " ዋጋ የማይጠይቅ የሠላም አማራጭ ሳለ በፖለቲከኞች የጠብ ርሃብ ምክንያት በርካታ ጉዳቶች ተከስተዋል " ብለዋል፡፡
" ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ልዩነቶቹ ከአማራ እና ትግራይ ሕዝብ በታች ናቸው " ያሉ ሲሆን " አሁን የጦርነትን ምዕራፍ ዘግተን የሠላም አማራጮችን የምናይበት ጊዜ ነው " ብለዋል፡፡
" የሁከት እና ግርግር አጀንዳዎች የሚታያቸው ይኖራሉ፤ ነገር ግን ለሕዝብ ካሰብን እና ከሠራን ከሠላም ውጭ የተሻለ አማራጭ የለንም " ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፕሬዜዳንት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው ፤ " ልዩነቶች ይኖራሉ ያሉትን ልዩነቶችን ግን በሕግ፣ በሠላም እና በመነጋገር መፍታት የአማራ ሕዝብ ፍላጎት ነው ብለዋል።
" የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ለሠላም አማራጮች ዝግጁ ነው " ሲሉም ተደምጠዋል።
" የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ወደ ቀደመው ሁኔታው መመለስ አለበት፣ ትራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴ መጀመር ይኖርበታል " ያሉት ዶ/ር ይልቃል " ተከባብረን እና ተደማምጠን ልዩነቶቻችን ለመፍታት መሥራት ይጠበቅብናል " ብለዋል።
የፖለቲካ አመራሩ የጀመረውን የሠላም ግንኙነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች በተለይ ደግሞ አዋሳኝ አካባቢ ያሉ የሁለቱም ክልል ሕዝቦች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
@esatchannal
5.4K viewsedited 18:35