2023-05-03 15:09:19
ኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን በመስጠት ከአለም ሀገራት የምትበልጪው 30ውን ብቻ ነው ተባለች፡፡
ዛሬ ይፋ በተደረገውና ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ወይንም ሪፖርተርስ ዊዝ ሀውት ቦርደር በየዓመቱ ይፋ በሚያደርገው የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት የአገራት ደረጃ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 114ኛ ወደ 130ኛ አሽቆልቁላለች፡፡አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ በይዘቱ ለመገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች የተሻለ ነፃነትን የሚሰጥ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረጉ ግን ፈተና እየገጠመው ነው ተብሏል፡፡
የቅድመ ክስ እስርና ሌላውም በአዋጁ የተከለከለ ቢሆንም ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ተብሏል፡፡በአሁኑ ሰዓት ቢያንስ 8 የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረዋል ተብለው በእስር ላይ ስለመሆናቸውም ተነግሯል፡፡የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ አማካኝነት ሜይ 3 ወይንም ሚያዚያ 25 ቀን የአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ተብሎ ይታሰባል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት እለቱን በማስመልከት ዛሬ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ባሰናዳው ዝግጅት ላይ የፕሬስ ነፃነትን የተመለከቱ በርከት ያሉ ሀሳቦች ተነስቷል፡፡የዘንድሮ የፕሬስ ነፃነት ቀን በአለም ዙሪያ በጦርነትና የሕዝብ መፈናቀል ሰበብ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ስጋት ላይ በወደቀበት ጊዜ የሚከበር ነው ተብሏል፡፡በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰቱ ጉልህ የሰብአዊ መብት ችግሮች በፀጥታ ሀይል እየተፈፀመ ያለ ፍርድ እስር ህገ-ወጥና የዘፈቀደ አፈናን በተመለከተ እንደ ሰብአዊ መብት ባሉ ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶችን መነሻ በማድረግ በዚህ ቀን በደንብ መነጋገር ይገባል ተብሏል፡፡
አዲሱ መገናኛ ብዙሃን አዋጅ በተመለከተ ሀሳብ ያነሱት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ አዲሱ አዋጅ ይዞ የመጣው ጠቀሜታ ብዙ ቢሆንም የዛን ያክል አዋጁን ተፈፃሚ ለማድረግ ችግር እየገጠመ ነው ብለዋል፡፡ሚዛናዊና እውነተኛ ዘገባ፣ የጋዜጠኛው ከስጋት ነፃ ሆኖ ስራውን መስራትና የህዝቡን እውነተኛ መረጃ የማግኘት መብትን በተመለከተ ሁሉንም አቻችሎ የመሄድ አስፈላጊነትን አንስተው በማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
ዛሬም የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ አደጋ ውስጥ ስለመሆኑ ማብራሪያ ያቀረቡት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ናቸው፡፡መሻሻል አሳይቶ የነበረው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መልሶ አደጋ ውስጥ ገብቷል ብለዋል፡፡አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ በርከት ያሉ ሊጠቀሱ የሚችሉ በጎ ጎኖች ቢኖሩትም አሁንም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን አልቻለም ብለዋል፡፡
አዋጁ የቅድመ ክስ እስርን የሚከለክል ቢሆንም አሁንም በቀጥታ ክስ ከማቅረብ ይልቅ የቅድመ ክስ እስር ተደጋግሞ እየታየ ነው ብለዋል፡፡በአሁኑ ሰዓትም በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረዋል የተባሉ ቢያንስ 8 የሚዲያ ሰራተኞች በስር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ዶ/ር ዳንኤል የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን የማንሳቱን ያክል መገናኛ ብዙሃኑ ያለባቸውን ግዴታ አብሮ ማንሳት ተገቢ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
የሚዲያ ነፃነት ገደብ የሌለው መብት አለመሆኑ ማወቅና መብትን ከግዴታ ጋር አቻችሎ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡በፕሬስ ነፃነት ቀኑ ላይ ጋዜጠኞች መረጃ ለማግኘት እየገጠማቸው ስላለው ችግርና ሌሎች ሀሳቦች ተነስቷል፡፡ፍርሃትና ምን ይገጥመኝ ይሆን በሚል ስጋት ውስጥ ሆኖ መስራት የመገናኛ ብዙሃኑ እና የጋዜጠኞቹ ፈተና ነው ተብሏል፡፡
የአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት አማካኝነት ሁሌም ሚያዚያ 25 ቀን እንዲከበር የተወሰነው ከ31 ዓመት በፊት በናሚቢያ ዊንዶ ኦክ የተካሄደውን ጉባኤ ተከትሎ ነው፡፡የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት እለቱን የተመከተውን ጉባኤ ከዩኔስኮ ካርድ ከተባለ ተቋምና ከሌሎችም ጋር በመሆን ያሰናዳው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ዛሬ ይፋ በተደረገው የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት የአለም አገራት ደረጃ ኢትዮጵያ ከ180 አገራት 130ኛ ደረጃ መያዟን ይፋ ተደርጓል፡፡
[Sheger FM]
@esatchannal
4.1K viewsedited 12:09