2023-05-08 20:08:41
ሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች
1፤ የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በአማራ ክልል ውስጥ ባኹኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው "ወታደራዊ እንቅስቃሴ" እና "የዘፈቀደ እስሮች" አሳሳቢ ኾነዋል ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት የኮሚሽኑ የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ላይ መግለጣቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። በክልሉ እየተወሰደ ካለው የጸጥታ ርምጃ "በእስር ወቅት የሚደርስ ተገቢ ያልኾነ አያያዝ"፣ "በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ጸጥታ ኃይሎች የሚወስዱት ተመጣጣኝ ያልኾነ የኃይል ርምጃ"፣ "በጋዜጠኞች፣ በሚዲያ፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ተቃዋሚ ድምጾች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት" እና "በመንቀሳቀስ መብት ላይ የተጣሉ የዘፈቀደ ገደቦች" ጭምር አሳስቢ እንደኾኑ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። የመንግሥት ርምጃ በሰብዓዊ መብት ላይ ያለው አንድምታ የሚያሰጋ መኾኑንም ዳንኤል ጨምረው ገልጸዋል።
2፤ በአፋር ክልል ገቢ ረሱ ዞን የሐሩካ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ ሃላፊ ኡመር ለማ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ትናንት እንደተገደሉ በክልሉ የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ኡመር በጥይት የተገደሉት፣ ከአዳማ ወደ አዋሽ በሚወስደው መንገድ ላይ በተሽከርካሪ ሲጓዙ በተከፈተባቸው ተኩስ እንደኾነ የገለጠው ፓርቲው፣ የግድያውን ፈጻሚዎች "አሸባሪዎች" በማለት ጠርቷቸዋል። ዶይቸቨለ በበኩሉ፣ ኡመርን ከአንድ ወንድማቸው ጋር በሩምታ ተኩስ ወለንጪቲ ከተማ አካባቢ አካባቢ ልዩ ስሙ አረቦና በሚባል ቦታ የገደሏቸው 30 የሚደርሱ ታጣቂዎች እንደኾነ ከሟቹ ቤተሰቦች መስማቱን ጠቅሶ ዘግቧል። ከጥቂት ቀናት በፊት ታጣቂዎች የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ ግርማ የሺጥላን ሰሜን ሸዋ ውስጥ መገደላቸው ይታወሳል።
3፤ ንግድ ባንክ ከነገ ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በነዳጅ ማደያዎች የ"ሲቢኢ ብር" የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት እንደሚጀምር አስታውቋል። ባንኩ "ቀላልና ፈጣን" ያለውን የ"ሲቢኢ ብር" የሞባይል ስልክ መገበያያ አገልግሎት ዘዴን በአዲስ አበባ ነዳጅ ማደያዎች መስጠት የጀመረው ከሚያዝያ 16 ጀምሮ ነው። የነዳጅ ደንበኞሽ፣ *847# በመደወል ወይም "ነዳጅ" የተሰኘውን ባንኩ ያበለጸገውን መተግበሪያ በሞባይል ስልካቸው ላይ በመጫን ነዳጅ መቅዳት እንደሚችሉ ባንኩ ገልጧል።
4፤ የሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ተወካዮች በሳዑዲ ዓረቢያና አሜሪካ አስተባባሪነት ጅዳ ውስጥ ቅዳሜ'ለት የጀመሩት ንግግር፣ ለቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት እንደሚቀጥል የሳዑዲ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጡን የውጭ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። የንግግሩ ዓላማ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ መተላለፊያ መስመሮችን ለመክፈት የሚያስችል "የአጭር ጊዜ ተኩስ አቁም" ላይ ለመድረስ ብቻ እንደኾነ ተፋላሚዎቹ የገለጡ ሲኾን፣ ሳዑዲና አሜሪካ ግን "ለዘላቂ ተኩስ አቁም" ንግግር እንዲደረግ በመወትወት ላይ እንደኾኑ ሚንስቴሩ ገልጧል ተብሏል። በጅዳው ንግግር እየተሳተፉ ከሚገኙት መካከል፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ይገኙበታል። ውጊያው ግን ዛሬም እንደቀጠለ ነው።
5፤ የሱማሌላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ "የፑንትላንድ ራስ ገዝ መንግሥት ታጣቂዎች የግጭት ማዕከል ከኾነችው ላስ አኖድ ከተማ እስካልወጡ ድረስ ግጭቱ አይቆምም" በማለት ለራስ ገዟ ፓርላማ መናገራቸውን የሐርጌሳ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የሱማሌላንድ ወታደሮች ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ፣ ፑንትላንድ የይገባኛል ጥያቄ በምታነሳባት የላስ አኖድ ከተማና ሱል አውራጃ የጎሳ ሚሊሻዎች ጋር ግጭት ውስጥ ናቸው። ሱማሌላንድ ግን፣ የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት ሠራዊት፣ የፑንትላንድ አስተዳደርና የአልሸባብ ታጣቂዎች ተባብረው እየወጉኝ ነው ትላለች። ፑንትላንድ በበኩሏ፣ ታጣዎቿን ወደ ላስ አኖድ እንዳላስገባሽ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
6፤ የኡጋንዳ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ጫትን ከአደንዛዥ ዕጽ ተርታ የሚፈርጀው ሕግ እንደሻረው የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፍርድ ቤቱ ሕጉን የሰረዘው፣ ፓርላማው ሕጉን ያጸደቀበት ውሳኔ ምልዓተ ጉባዔ ያልተሟላበት ሕጋዊ ያልኾነ ውሳኔ ነው በማለት እንደኾነ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ የአገሪቱ ጫት አምራች ገበሬዎች ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ነው። የኡጋንዳ ፓርላማ ከሰባት ዓመታት በፊት ያጸደቀው ሕግ፣ ጫት ማምረት፣ መሸጥ፣ ማከፋፈልና መጠቀምን የሚከለክል ነበር። በምሥራቅ አፍሪካ ጫት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የመሪነቱን ደረጃ የያዙት፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ናቸው።
7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ1967 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ2806 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 65 ብር ከ0182 ሳንቲም እና መሸጫው 66 ብር ከ3186 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ9090 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ1072 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
#ሼር በማድረግ ተባበሩን
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
4.3K views17:08