2023-04-28 19:41:38
ዓርብ ምሽት! ሚያዝያ 20/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች
1፤ የፓርላማው አባላት ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንደማያቀርብና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደማያከብር ጠቅሰው ተችተዋል። የፓርላማ አባላቱ ትችቱን ያቀረቡት፣ ፌደራል ፖሊስ ሕገወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የሰው ዝውውርና ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን እየመረመረ መኾኑን ትናንት ለሕግና ፍትህ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ነው። ፌደራል ፖሊስ ግን፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን ማክበር ለፖሊስ "ቀይ መስመር" መኾኑን ገልጦ ትችቱን ያስተባበለ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቶችም በጉዳዩ ላይ ያቀረቡት ቅሬታ እንደሌለ ተናግሯል። ፌደራል ፖሊስ በተለይ በቁጥጥር ስር የዋሉ ጋዜጠኞች ከውጭ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደደረግላቸውና "በስውር መዋቅር ተደራጅተው" እንደሚንቀሳቀሱ ለፓርላማ አባላቱ አብራርቷል።
2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ልዩነቶቻቸውን በመግባባት ለመፍታትና ለሱዳን መረጋጋት ማስፈን በሚችሉበት ኹኔታ ዙሪያ ከኹለቱም ጋር በስልክ መወያየታቸውን ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። በኹለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ከኹለት ሳምንት በፊት ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ ዐቢይ ከጀኔራል ቡርሃንና ጀኔራል ደጋሎ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በስልክ መነጋገራቸውን ሲገልጹ የዛሬው የመጀመሪያቸው ነው።
3፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭት ከምትታመሰው ሱዳን የሚመነጩ የጸጥታና ሰብዓዊ ቀውስ ስጋቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጋቡ የሚከላከልና መፍትሄ የሚሰጥ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸውን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ግብረ ኃይሉ፣ ዜጎቻቸውን በአስቸኳይ ከሱዳን ለማስወጣት የአየር ክልልና አውሮፕላን ማረፊያ ፍቃድ ለሚጠይቁ አገራት ምላሽ የሚሰጥ፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ስደተኞችና የውጭ ዜጎች አቀባበልና ሽኝት የሚያደርግ ጭምር መኾኑን መለስ መናገራቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል። መለስ ስንት ኢትዮጵያዊያን ከሱዳን ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል ተብሏል።
4፤ የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም መንግሥት በኦሮሚያ፣ ሱማሌና ደቡብ ክልሎች ድርቅና ጎርፍ ላስከተለው ጉዳት ዳተኛና ከሚጠበቀው ደረጃ በታች የኾነ ምላሽ ሰጥቷል ሲል በክልሎቹ ያደረገውን የቁጥጥር ሪፖርት ትናንት ለጋዜጠኞች ባብራራበት ወቅት ተችቷል። ተቋሙ፣ በክልሎች የምግብ ዕርዳታ ክምችት አለመኖሩና ፍትሃዊ የዕርዳታ ሥርጭት አለመስፈኑ አንድ ከጠቀሳቸው ችግሮች መካከል ይገኙበታል። በድርቁ ሳቢያ ከቦረና ዞን ከ59 ሺህ በላይ ተጎጂዎች በ20 መጠለያዎች እንደሚገኙ የገለጠው ተቋሙ፣ በዞኑ ድርቁ ከ1 ሚሊዮን 300 በላይ የቁም እንስሳትን መግደሉን ገልጧል። ከደቡብ ኦሞ ዞን ኹለት ወረዳዎች 64 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንና ከሱማሌ ክልል ዳዋ ዞን ደሞ ከአራት ወረዳዎች ከ16 ሺህ 300 በላይ ተፈናቃዮች በአራት መጠለያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቅሷል።
5፤ ታንዛኒያ 206 ዜጎቿን በኢትዮጵያዋ የጠረፍ ከተማ መተማ በኩል በተሽከርካሪ ከሱዳን ማስወጣቷን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በመተማ በኩል ከሱዳን ወጥተው በቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ አገራቸው ከተመለሱት ታንዛኒያዊያን መካከል፣ በሱዳን የአገሪቱ አምባሳደር ሲሊማ ሐጂ እና የጉዞ ሰነድ የሌላቸው የአገሪቱ ዜጎች እንደሚገኙበት ዘገባዎቹ አመልክተዋል። በመተማ በኩል ከሱዳን የወጡት አብዛኛዎቹ ታንዛኒያዊያን በሱዳን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ናቸው ተብሏል። ስመ ጥሩ በኾኑት የሱዳን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ አፍሪካዊያን ተማሪዎች እንደሚማሩ ይታወቃል።
6፤ ኹለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ከትናንት እኩለ ሌሊት ጀምሮ በድጋሚ ያራዘሙትን የ72 ሰዓታት ተኩስ አቁም ሳያከብሩ እንደቀሩ የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ካርቱም ዛሬም በከባድ መሳሪያ ተኩስ ስትናጥ እንደዋለች ዘገባዎቹ አመልክተዋል። በምዕራብ ዳርፉር ግዛት በኹለቱ ወገኖች መካከል የቀጠለው ግጭት ደሞ፣ የጎሳ ግጭት መቀስቀሱን ተመድ ገልጧል።
7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ1517 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ2347 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ5557 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ8468 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ8647 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ0620 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
2.9K views16:41