2023-04-27 20:02:04
ሐሙስ ምሽት! ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች
1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በአማራ ክልል የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የኾኑት ግርማ የሺጥላ ዛሬ "በነውጠኛ ጽንፈኞች" መገደላቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። ዐቢይ በዚኹ መልዕክታቸው፣ "በሐሳብ የተለየን ኹሉ በጠመንጃ ለማሳመን መነሳት የጽንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ነው" ብለዋል። ግድያው "አስነዋሪና አሰቃቂ" መኾኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ጽንፈኝነትን በጊዜ ካልተወገደ "ወደመጨራረስ እንደሚወስደን ጉልህ ማሳያ ነው" በማለትም ድርጊቱን አውግዘዋል። ግርማ ዛሬ የተገደሉት በተወለዱበት ሰሜን ሸዋ አካባቢ መኾኑንም ዐቢይ ጨምረው ገልጸዋል።
2፤ የኹሉም ክልላዊ መንግሥታት ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ከንቲባዎችና የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተካተቱበት ልዑካን ቡድን ዛሬ በትግራይ ክልል ጉብኝት ማድረጉን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ልዑካን ቡድኑን የመሩት የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አደም ፋራህ መኾናቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ልዑካን ቡድኑ፣ በውቅሮ ከተማ ሰማያታ የእብነበረድ ፋብሪካና ሸባ የቆዳ ፋብሪካን እንደጎበኘና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ እና ከሌሎች የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ጋር እንደተወያየ ዘገባው አመልክቷል። በጉብኝቱ ወቅት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋሚያ 1 ቢሊዮን ብር እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል ተብሏል።
3፤ ታንዛኒያ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ድርድር አሸማጋዮች ኬንያ እና ኖርዌይ እንደኾኑ ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል። አጀንዳ በመቅረጽ ላይ ያተኮረው የአኹኑ ድርድር ወደፊት ለሚካሄድ ሁሉን ዓቀፍ ድርድር መንደርደሪያ እንደሚኾን የአማጺው ቡድን ቃል አቀባይ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ድርድሩ ወደፊት ከቀጠለ፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ ኅብረት እና ኢጋድ የድርድር ሂደቱ አካል ይኾናሉ መባሉን ዘገባው አመልክቷል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፣ መንግሥት ድርድር እየተካሄደ ስለመኾኑ ያለው ነገር የለም።
4፤ የፌደራሉ እንባ ጠባቂ ተቋም በኦሮሚያ፣ ሱማሌና ደቡብ ክልሎች በድርቅ ሳቢያ "አንድም ሰው እንዳልሞተ" አረጋግጫለሁ ሲል ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መናገሩን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ተቋሙ በድርቁ የሰው ሕይወት እንዳላለፈ አረጋግጫለሁ ያለው፣ በሦስቱ ክልሎች በድርቁ በከፍተኛ ደረጃ በተጎዱ የኦሮሚያው ቦረና፣ የሱማሌው ዳዋ እና የደቡቡ ደቡብ ኦሞ ዞኖች ባለፈው መጋቢት መገባደጃ ያከናወነውን ክትትል መሠረት በማድረግ መኾኑን መግለጡን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ተቋሙ፣ ከሦስቱ ክልሎች በድርቁ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የኦሮሚያው ቦረና ዞን መኾኑን ማረጋገጡን በመግለጫው አመልክቷል ተብሏል።
5፤ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ በቦዲ እና ደሚ ጎሳዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት 11 ሰዎች ተገድለው ስድስት ሰዎች እንደቆሰሉ ዶይቸቨለ ከዓይን እማኞችና ከወረዳው አስተዳደር መስማቱን ጠቅሶ ዘግቧል። የኹለቱ ጎሳዎች ግጭት ወደ ወረዳው መቀመጫ ከተማ ሐና ተዛምቶ ሴቶችና ሕጻናት ጭምር እንደተገደሉ የጠቀሰው ዘገባው፣ የግጭት መነሻ አንድ የወረዳው አመራር ገጠር ውስጥ ለሥራ በመጓዝ ላይ ሳሉ በድንገተኛ ጥቃት ከተገደሉ በኋላ መኾኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።
6፤ ኢጋድ የኢጋድ አሸማጋይ መሪዎች ቡድን አባል የኾኑት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሃንን እና ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎን ለማሸማገል ጥረት መጀመራቸውን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ፕሬዝዳንት ኪር ዛሬ እኩለ ሌሊት የሚያበቃው የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የ72 ሰዓታት ተኩስ አቁም ለተጨማሪ 72 ሰዓታት እንዲራዘምና ኹለቱ ወገኖች ሽምግልና እንዲጀምሩ እያደረጉት ባለው ጥረት የደረሱበትን ደረጃ፣ ትናንት ለድርጅቱ አባል አገራት መሪዎች ማሳወቃቸውንም ኢጋድ ገልጧል።
7፤ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ጁባ ውስጥ ተገናኝተው በዘላቂ ግጭት ማቆም ዙሪያ እንዲነጋገሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል። የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን የፕሬዝዳንት ኪርን ግብዣና የተኩስ አቁም ማራዘም ጥሪ እንደተቀበሉት ዘገባው ጠቅሷል። የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ግን፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ገና ምላሽ አልሰጡም ተብሏል። የተኩስ አቁሙ ቀነ ገደብ ባይጠናቀቅም፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት ዛሬ ካርቱም ውስጥ የባላንጣውን ይዞታዎች በአየር እንደደበደበና በምዕራብ ዳርፉር ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መኾኑን የዘገቡት ደሞ የውጭ ዜና ወኪሎች ናቸው።
8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ1547 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ2347 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ5557 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ8468 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ8647 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ0620 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
4.3K views17:02