2023-07-29 07:09:59
ከሱብሒ ሰላት በፊት ቀደም ብዬ ካይሮ ኤርፖርት ደረስኩ ይሉናል የታሪካችን ተራኪ ሸይኽ ሙሐመድ ሳዊ። ሰዓቱ ለሊት ስለነበር የመስጂድ ኢማም ወደሆነው ወዳጄ ዘንድ ደወልኩ።
"ገና አሁን መግባቴ ነውና መስጂድ መጥቼ እስከ ንጋት አብሬህ እቆይ ዘንድ የመስጂዱን በር ክፍት ተውልኝ" አልኩት።
ሻንጣዬን ሸክፌ በዝግታ እየተራመድኩ መስጂዱ በራፍ ላይ ደረስኩ። መብራቶቹ በርተዋል። አንድ ሰው ሚህራቡ አቅራቢያ ሱጁድ ተደፍቶ አላህን ያናግራል።
"ጌታ ሆይ ከዚህ በላይ መታገስ አቃተኝ አልቻልኩም ደከመኝ ከአንተ በቀር ማንም የለኝ ወዴት ልሂድ ወደማንስ ልጠጋ አረ ተው ጌትዬ!..." እያለ እነዚህን ቃላት ይደግማል።
ሰውነትን የሚያንቀጠቅጥ አስደንጋጭ ዱዓ!!
ዕንባን የቀላቀለ አስቸኳይ መልስን የሚሻ ልመና!!
ከነፍሴ ጋር አወጋሁ በአላህ እምላለሁ ይህ ለቅሶ ኃጢአት ከሠራ ሰው የሚመነጭ አይደለም ችግር ያቆረፈደው መከራና ሐዘን የከበበው ሰው ልመና ነው እያልኩ ባለሁበት ቆምኩ። እስኪጨርስ ጠብቄ ወደ ሰውየው ተጠጋሁ። ሲያየኝ ዝም አለ።
"ወንድሜ!" አልኩት "ምን ነካህ? ምን አገኘህ?!" በማለት ጠየቅኩት።
ከረዥም ዝምታና ውትወታ በኋላ፡-
"በአላህ እምላለሁ ምን እንደምል አላውቅም ነገር ግን ባለቤቴ ነገ ጠዋት ኦፕራሲዮን ታደርጋለች። ለቀዶ ጥገናው የሚያስፈልገኝ 15,400 ፓውንድ ነው። ስባሪ ሳንቲም ስለሌለኝ ጌታዬ እንዲያበድረኝ እየጠየቅኩት ነው" አለኝ።
"የምረዳህ ገንዘብ ባይኖረኝም አላህ የተደገፈበትን እንዲሁ የማይተው መሐሪ ጌታ ነውና አብሽር" ብዬው ዊትሬን ሰግጄ ተኛሁ።
ጎህ ቀዶ ሙአዚኑ ለፈጅር ሰላት ቀሰቀሰኝ። ሱብሒን ባንተ መስገድ እንፈልጋለንና ተቀደም አለኝ። ሰግደን እንዳበቃን ከሦስተኛው ሰፍ ረጅም ካፖርት የለበሰ ሰው እኔ ወዳለሁበት አቅጣጫ ተጠጋ። ሞቅ ባለ ሰላምታ ፈገግታን እየቸረኝ እንዴት ነህ? አለኝ።
ፕሮግራምህንና ትምህርቶችህን እከታተላለሁ ከመስጂዱ ፊት ለፊት የሚገኝን አፓርታማ የገዛሁት ከጥቂት ጊዜ በፊት ነው። አንተን ለማየትና ሰላም ለማለት በመታደሌ አልሐምዱሊላህ" አለኝ።
"እንኳን ደህና መጣህ አላህ ይባርክህ" አልኩት ሰላምታውን እየመለስኩ።
ተመቻችቶ እየተቀመጠ ንግግሩን ቀጠለ:-
"ጌታዬ ወሰን በሌለው ፀጋው አክብሮኛል፤ የፕላስቲክ ፋብሪካ ባለቤት ነኝ። ሁለተኛውን ቅርንጫፍም በቅርቡ ከፍቻለሁ። ምስጋና ለአላህ ይገባውና ዘካውን ሳሰላ 15400 ፓውንድ ... "
ንግግሩን ሳይጨርስ በለቅሶዬ አቋረጥኩት። መላ አካሌ በድንጋጤ ተንቀጠቀጠ። ከሱ በቀር ሌላ አምላክ በሌለው ጌታ እምላለሁ ይህ ሰው የጠራው የገንዘብ መጠንና ያ ከሱብሂ በፊት ያገኘሁት ወንድም ቸግሮት የፈለገው የብር መጠን አንድ ነበር። ያን ሰው በአይኔ ፈለግኩት
"ምን ነካህ ሸይኽ?" አለኝ በሁኔታዬ ግራ እየተጋባ
"ትንሽ ታገሥ" አልኩት።
ሰውየውን አየሁት። ወደ እኛ እንዲመጣ በምልክት ጠራሁት። ከፊታችን ተቀመጠ። አይኖቹ በለቅሶ ብዛት አሞጭሙጨዋል። እስኪ ሐጃህን በድጋሜ ንገረኝ አልኩት።
"ሚስቴ ዛሬ ጠዋት ኦፕራሲዮን እንደምታደርግ፣ ገንዘብ እንደሌለኝ ነግሬሀለው" አለኝ
"ቀዶ ጥገናው ስንት ብር ያስፈልገዋል" አልኩት።
"15400 ፓውንድ"
ነጋዴው በተክቢራ መስጂዱን እየናጠ ምርር ብሎ አለቀሰ! ወደ ደረቱ አስጠግቶ እያቀፈው እንዲህ አለ፡-
"በአላህ እምላለሁ ባለቤቴ ይህንን የአላህ ሀቅ ለሚገባው ባለሐቅ ወስደህ ስጥ እያለች ጠዋት ማታ ትወተውተኛለች። ሐቢብቲ መቶ መቶ እየቆነጠርኩ መስጠት አልሻም። የቂያማ ቀን አላህ ከጭንቅ ይገላግለኝ ዘንድ ሙሉ ገንዘቡን ለተቸገረ አንድ ሰው ሰጥቼ ከጭንቀቱ ገላግዬ ለደስታው ሰበብ መሆን እፈልጋለሁ እላታለሁ"
ገንዘቡን በሙሉ አመጣና ለሰውየው ሰጠ።
እየሆነ ያለውን አላመነም። ገንዘቡን ሲቀበል እኔንም ነጋዴውንም ትቶ ገንዘቡን በእቅፉ እንደያዘ ሱጁድ ወረደና እንዲህ አለ:-
"ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ እንደምትወደኝም አውቃለሁ"
ዩሒቡሁም ወዩሂቡነህ ይሉሀል ይህ ነው።
ችክ ብሎ በሲድቅ አላህን የለመነና የተቸገረን ሰው ከጭንቅ ለመፈረጅ በኢኽላስ የታተረ ሁለትዮሽ ዱዓ ሲገጥም የሚሆነው እንዲህ ነው። እንደዚያም ተፈፀመ።
ታሪኩ አልቋል የዓለማቱ ጌታ ስጦታዎች ግን አያበቁም.......
ሸይኽ ሙሐመድ ሳዊ ገጠመኛቸውን ከተናገሩበት የድምፅ ቅጂ የተተረጎመ።
Mahi Mahisho
@Dania_Islamic || ዳኒያ ኢስላማዊ ቻናል
17.9K views04:09