2023-05-20 20:43:29
ድህረ-ዘመናዊነት (Postmodernism): ማህበረሰባዊ ዕዳ ወይስ ቡራኬ?
(ዮናስ ታደሰ)
ክፍል አራት
2.1 ድህረ-ዘመናዊነት በዘመናዊነት ላይ አምፆ እንዲነሳ ምክንያት የሆነው ፍልስፍናዊ ፕሮብሌም ታሪካዊ ዳራ
በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ቴይሊዝ ባመጣው "ከተረት ወደ ህሊና" መሸጋገሪያ ጭብጥ ምክንያት፤ ግሪክ መሰረቱ ያደረገው የምእራቡ ዓለም ፍልስፍና የሚታወቅበት ዋና መለያ ባህሪው በአመክንዮአዊ-አእምሮ (Reason) ላይ ያለው ፅኑ መተማመን ነው። * (ከስር ያለውን ማስታወሻ ይመልከቱ)
ይሄም ማለት ሰው ስለ ራሱ የሰውነት ተፈጥሮ ምንነት እውቀትን ጨምሮ በዙሪያው ስለአለው የተፈጥሮ ከባቢም ሆነ ስለ ዓለም/ሁለንታ ምስጢራት በአጠቃላይ ለማወቅ ከፈለገ፤ ያለ ማንም ውጪያዊ ወይም መለኮታዊ እገዛ እሱ ራሱ የገዛ አመክንዮአዊ-አእምሮውን ተጠቅሞ አጥንቶ እና ተመራምሮ ሊደርስበት ይችላል የሚል በህሊና (ወይም በአመክንዮአዊ-አእምሮ) ላይ ያልተሸራረፈ ሙሉ መተማመንን መያዝ ማለት ነው።
በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ ግሪክ ላይ የተወለደው ፍልስፍና የህሊና ወይም የአመክንዮአዊ-አእምሮ ውልደት ተደርጎ የሚወሰደው ። ከዚህ የተነሳም ነው መጀመሪያ ላይ የግሪካውያን በኋላ ላይ ደግሞ የምእራቡ ዓለም በአጠቃላይ የተከተለው የሐሳብ ታሪክ ጉዞ ከተረት ወደ ህሊና የተደረገ ጉዞ ተደርጎ የሚወሰደው።
ይህ ከተረት ወደ ህሊና በተደረገ ሽግግር ምክንያት የተጀመረው አመክንዮአዊ-አእምሮ መር የፍልስፍና ጉዞ ግን ገና ከጅምሩ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተግዳሮቶች የተሞላ ውጣ ውረድ የበዛበት መንገድ ሆኖ ነው እየቀጠለ ያለው። ተግዳሮቱ የሚመነጨው በዋናነት ከ እንደነ ሄረክላይተስ አይነት ተጠራጣሪ (skeptic) ፈላስፎች እና የምስራቁ ዓለም ሃይማኖታዊ ወይም ደግሞ ተአምራታዊ (mystical) ተፅእኖ ያለባቸው ፓይታጎረሳውያን አይነት ፈላስፎች ነው።
የነዚህ ሁለት ጎራዎች ማለትም በአመክንዮአውያን ፈላስፎች እና በተአምራታውያን ፈላስፎች መካከል በሚደረግ የሐሳብ ፍልሚያ (በታሪክ እንደታየው ተአምራታውያን የበላይነት በሚያገኙበት ወቅት የሐሳብ ፍልሚያውን ወደ ሐይል/ጉልበት ይቀይሩታል) ነው የፍልስፍና ታሪክ ሂደት እንደዚሁም አጠቃላይ የሰው ልጅ የታሪክ ሂደት አቅጣጫ የሚወሰነው ትላለች አይን ራንድ። ከሶቅራጥስ በኋላ ደግሞ ይህ ፍልሚያ በአሪስቶትላውያን እና በፕሌቶናውያን መካከል የሚደረግ ነው። (The Duel Between Plato and Aristotle in, Objectivism: The Philosophy of Ayn Rand)
አሪስቶትላውያን ማለት በዲበ-አካል (ሜታፊዚክስ) አስተምህሮአቸው <<እውንነት (Reality) በፍፁማዊነት ከኛ ንቃተ-ህሊና ውጭ ፀንቶ የሚኖር ተጨባጭ (objective) ነው ብለው የሚቀበሉ፤ በስነ-እውቀት (ኤፒስተሞሎጂ) አስተምህሮአቸው ደግሞ <<የሰው አእምሮ ይህን እውንነት (Reality) ማወቅ ይችላል>> ብለው የሚቀበሉ ናቸው። ፕሌቶናውያን ማለት ደግሞ በዲበ-አካል (ሜታፊዚክስ) አስተምህሮአቸው <<የእውንነት (Reality) ምስለ-አካል/ቅርፀ-ምስል (perception) ይህ ነው ተብሎ የማይወሰንና ሊታወቅም የማይችል ኢእውን-ምስል (illusion) ነው ብለው የሚቀበሉ፤ በስነ-እውቀት (ኤፒስተሞሎጂ) አስተምህሮአቸው ደግሞ <<የሰው አእምሮ እውንነትን ለማወቅ የማይቻለው አቅመ-ቢስ (impotent) ነው ብለው የሚቀበሉ ናቸው። (የፍልስፍና ትምህርት ቅፅ-፩)
በነዚህ ሁለት ጎራዎች በተደረገው የመጀመሪያው የሐሳብ ፍልሚያ ታድያ በፕሌቶናውያኑ በእነ ፕሎታይነስ (Plotinus) እና ኦግስጢኖስ (Augustine) ስራዎች አማካኝነት ፕሌቶ አሸናፊ ሆነ። በዚህም የጨለማው ዘመን (The Dark Ages) የሚባለውን ተከተለ። የጨለማው ዘመን ቶማስ አኳይነስ አሪስቶትልን ነፍስ ዘርቶ እስኪያስነሳው ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የቆየ ነው። አሪስቶትል በቶማስ አኳይናስ አማካኝነት በአውሮፓ ምድር ከተንሰራፋ በኋላ፤ አውሮፓውያን ለዘመናት ተሰውሮባቸው የቆየውን የአመክንዮአዊ-አእምሮ ምንነት እና ጥቅም ይበራላቸው ጀመር። በዚህም ምክንያት አጠቃላይ የሐሳብ ታሪካቸውን መመርመር ጀመሩ። የጨለማው ዘመንን ተሻግረውም ወደ ኋላ ማማተር ሲጀምሩ ግሪክ ላይ ቀደምት አባቶቻቸው የነበራቸውን በአመክንዮአዊ-አእምሮ ላይ የመተማመን ባህልን ተገነዘቡ። ይሄን በአመክንዮ ላይ የተመሰረተውን የግሪክ ፍልስፍና ባህልን አጣቅሰውም ወደ ህዳሴ ዘመን (Renaissance) አቀኑ። በአመክንዮአዊ-አእምሮ ላይ ያላቸውን መተማመን በረኒ ዴካር (René Descartes)፣ ፍራንሲስ ቤከን (Francis Bacon)፣ እና ጆን ሎክ (John Locke) ስራዎች አማካኝነት እየጎለበተ ሲመጣም ዘመናዊ ፍልስፍና ተወለደ። አመክንዮአዊ-አእምሮ የሚገባትን የክብር ማማ ላይ ስትቀመጥም የአብርሆት ዘመን (The Age of Enlightenment) ተከተለ። (የፍልስፍና ትምህርት ቅፅ-፩)
የዘመናዊነት ፍልስፍና ምንድን ነው?
ዘመናዊ ፍልስፍና እና አብሮሆት ተመጋጋቢ ናቸው። ዘመናዊ ፍልስፍና አብርሆትን ወለደ፤ በአብርሆት ዘመን ደግሞ ዘመናዊ ፍልስፍና ጎልምሶ በባህል፣ በአርት ፣በፖለቲካ፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ የተገለፀበት ነው።
የዘመናዊነትን ጅማሮ ከጊዜና ከቦታ አንፃር መበየን አስቸጋሪ ነው ይባላል። ነገር ግን ፍልስፍናዊ ምልከታቸውን ተፈጥሮአዊነት (Philosophical Naturalism) ላይ ያተኮረ፣ በአመክንዮአዊ-አእምሮ ላይ ባላቸው መተማመን ወይም ፅኑ እምነት፣ እናም በግለሰባዊነት ላይ ባላቸው ልዩ አትኩሮት የተነሳ ቤከን፣ ዴካር፣ እና ሎክ የነበሩበትን ዘመን የዘመናዊነት ሐሳብ የተጠነሰሰበት አድርገን መውሰድ እንችላለን። ዘመናዊነት ያመጣቸውን አዳዲስ እሳቤዎች ለማየት እንዲያስችለን ከቅድመ-ዘመናዊነት ያለውን ንፅፅሮሽ ከብዙ በጥቂቱ እንመልከት:- (Explaining Postmodernism)
- ዘመናውያን አሳቢዎች የተፈጥሮ እውቀትን ለማግኘት በአፅንኦት የሚቀበሉት መንገድ የምስለ-አካል (Perception) እና አመክንዮአዊ-አእምሮ (Reason) መሳሪያዎችን ሲሆን፤ ቅድመ-ዘመናውያን ትውፊትን (tradition)፣ ጭፍን-እምነትን (faith)፣ እና ተአምራታዊነትን (mysticism) ነው እንደ የእውቀት መሣሪያ የሚቀበሉት።
- ዘመናውያን አሳቢዎች የሰውን ራስ-ገዝነት (autonomy) እና የራሱን ፀባይ/ባህሪ (personal character) የማነፅ/የመገንባት ሚና ለመወጣት ያለውን ውስጣዊ አቅም ላይ ሲያተኩሩ፤ ቅድመ-ዘመናውያን ደግሞ ሰው የመሆን ዕዳ በሚሏቸው ባሕርያት ውጭያዊ ረዳት ፈላጊነት (dependence) እና የውርስ ሐጢአተኝነት ወይም ጥንተ-አብሶ (Original Sin) ላይ ነው የሚያተኩሩት።
- ዘመናውያን አሳቢዎች ሰውን በግለሰባዊ ልኬት የሚመዝኑ እና የእሴት ልኬት ሚዛን (standard of value) አድርገው የሚወስዱትም ግለሰብን ሲሆን፤ በቅድመ-ዘመናውያን አሳቢዎች ዘንድ ደግሞ የህልውና ልኬት (unit of survival) ተደርጎ የሚወሰደው ጋርዮሻዊ ስብስቡ/ቡድኑ (The Collective) ነው። በአጠቃላይ ግለሰብን ለማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወይም ለሃይማኖታዊ የስልጣን ተዋረድ የሚያስገዛ ወይም የሚያስገብር ምልከታ ነው ያላቸው።
አሁን የዘመናዊነት ፍልስፍናዊ ፕሮብሌም ምንነትን እንመልከት።
848 views17:43