2023-05-02 20:28:55
የምስኪኖቹን መንደር በስካቫተር ያፈረሰው ሚሊየነር ።
በደቡባዊ ቻይና ግዛት የምትገኘው የደሳሳዋ ዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎች ፡ ሸቀጣሸቀጥ ጭነው ከሚመጡ አሮጌ ከባድ መኪኖች ውጭ አንድም መኪና ወደመንደራቸው ዘልቆ አይተው አያውቁም ። ዛሬ ግን እጅግ ዘመናዊ ፡ መርሰዲስ መኪና መጥታ ቆማለች ።
እናም ነዋሪዎች ፡ በመኪናዋ እዚህ መገኘት በመገረም ዙሪያውን ከበው በማየት ላይ እያሉ ፡ አንድ በጠባቂዎች የታጀበ እድሜው በሀምሳዎቹ የሚገመት ሰው ከመኪናው ወጣ ። ማንም ደፍሮ ሰላም ሊለው ወይም ሊያናግረው የመጣ ሰው ግን አልነበረም ። እናም ሰውየው መንደሩን ለደቂቃዎች ከተመለከተ በኋላ ተመልሶ ወደመኪናው ገብቶ ሄደ ።
ይህ በሆነ በማግስቱ ወደዛች ደሳሳ መንደር ሌላ መኪና መጣ ። ከመጡት ሰወች ውስጥ የትናንቱ ሰውዬ አልነበረም ። በቁጥር በዛ የሚሉ መሀንዲሶች ነበሩ የመጡት ። በዚህ ጊዜ ነዋሪዎቹ ነገሩ ገባቸው ፡ የትናንቱ ሰው ባለሀብት መሆኑን በሁኔታው አውቀዋል ፡ እናም ይህን መንደር ሊያፈርስ መሀንዲሶች ልኳል ።
................
እነዚህ ነዋሪዎች ፡ ይህም ኑሮ ሆኖ ፡ ደሳሳ ጎጇቸውን የሚያፈርስ ሰው ይመጣል ብለው መቼም አስበው አያውቁም ነበር ። እና ሽማግሌዎች ቀርበው መሀንዲሶቹን አናገሯቸው ። ፍርሀታቸው ልክ ነበር ፡ ትናንት የመጣው ባለሀብት እዚህ መንደር ላይ ሪል ስቴት መገንባት ፈልጓል ፡፡ ለዚህም ከመንግስት ፍቃድ እንዳገኘ ፡ ከሰባ በላይ ለሚሆኑት ለመንደሩ ነዋሪዎችም ካሳ እና መኖሪያ ቤት የሚገነቡበት ገንዘብ እንደሚሰጣቸው እስከዛ ግን በመጠለያ መቆየት እንደሚችሉ ፡ እስከነገ ድረስም እቃቸውን አውጥተው በተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንዲያስቀምጡ ነግረዋቸው ሄዱ ።
ከቀናት በኋላም ፡ ብዛት ያላቸው ግሪደሮች እና የህንጻ ሰራተኞች ትንሿን መንደር አጥለቀለቋት ።
....................
ያለቻቸውን አሮጌ እቃ አውጥተው ከቤታቸው አቅራቢያ በተዘጋጀላቸው መጠለያ ውስጥ የገቡት የዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎች ፡ ቆመው እያዩ ለዘመናት የኖሩባቸው ደሳሳ ጎጆዎች በስካቫተር ፈረሰ ።
.............
ቃል የተገባላቸው ቤት መስሪያ ቦታም ሆነ ካሳ ሳይሰጣቸው ለወራት በመጠለያ እየተረዱ ቆዩ ። ከአመታት በፊት ከነሱ ብዙም በማይርቅ ቦታ የሚገኙ መንደሮች ልክ እንደነሱ በጨካኝ ባለሀብት ተፈናቅለው ፡ መሰደዳቸውን እያሰቡ ፡ እጣ ፈንታቸውን መጠባበቅ ጀመሩ ።
........
ይህ በሆነ በጥቂት ወራት ውስጥም የባለሀብቱ ዘመናዊ ቪላዎች ተገንብተው ተጠናቀቁና ፡ ነዋሪዎቹ በስነስርአቱ ላይ እንዲገኙ ፡ በፕሮግራሙም ላይ ለነሱም ቃል የተገባላቸው ካሳ እንደሚሰጥ ተነገራቸው ። ብዙዎች ነዋሪዎች ግብዣውን ተቃወሙ ።
.......
ትንሿ የዦንኪንግ መንደር ዛሬ በልዩ ሁኔታ ደምቃለች ። ከሰባ በላይ ዘመናዊ መኖሪያዎችን ለመመረቅ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል ። ያቺ የድሆች መንደር ፡ አይታ በማታውቀው ሁኔታ በዘመናዊ መኪኖችና በሀብታሞች ተጥለቅልቃለች ።
የምረቃው ፕሮግራም ተጀመረ ።
ያ ፡ በመጀመሪያ ቀን መርሰዲስ መኪና ይዞ ወደዚህ መንደር የመጣው ባለሀብት ፡ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረኩ ወጣ ።
ክቡራንና ክቡራት የዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎችና ፡ ክቡራን እንግዶች ዛሬ ልዩ የሆነውን ይህን የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት ለመመረቅ ስለተገኛችሁ አመሰግናለሁ ።
እኔ የማየው ዛሬ ሚሊየነር መሆኔን አይደለም ። የኔ ስብእና የኔ የሀብት ምንጭ ይሄ መንደር ነው ።. ... እኔ ..... ትንሽ ልጅ ሆኜ የምታውቁኝ Xiong Shuihua ነኝ ። በርግጥ ከዚህ መንደር ከወጣሁ ብዙ አመታት ተቆጥረዋልና ፡ አላወቃችሁኝም ። እኔ ግን ሁላችሁንም አስታውሳለሁ ።
ለኔና እጅግ ድሆች ለነበርነው ቤተሰቦቼ በየወሩ ቀለብ ይቆርጥልን የነበረው ሚስተር ዣይን ፡ ከልጆቻቸው እኩል ልብስ ይገዙልኝ የነበሩት የሚስ ታዮኒ ቤተሰቦች ፡ ሲርበን የሚያበሉን የዚህ መንደር ነዋሪዎች ሁላችሁንም አስታውሳለሁ ።
የኔ የአሁን ህይወት ላይ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጣችሁ እናንተ ናችሁ ። ለዚህም ነው መንደሩን ለመለወጥ በተሻለ ህይወት እንድትኖሩ ለማሰብ የተገኘሁት ።
እናም እነዚህ ቤቶች የተሰሩት ለናንተ ነው ። ያለምንም ክፍያ በነዚህ ቤቶች ትኖራላችሁ ። ቤቶቹ ንብረቶቻችሁ ናችሁ ። በነጻ የተሰጧችሁ አይደሉም ፡ ከአመታት በፊት ለኔና ለቤተሰቦቼ መልካም ነገር በማድረግ ኢንቨስት አድርጋችሁበታል ።
እያለ እንባ እየተናነቀው ሲናገር የመንደሩ ሰወች በሙሉ በታላቅ ድንጋጤ ውስጥ ሆነው ይሰሙት ነበር ።
ባለሀብቱ ንግግሩን ቀጥሏል ።
እናም ከሀምሳ ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎባቸው የተሰሩት ፡ እነዚህ ቤቶች በፈረሱት ቤቶቻችሁ ቁጥር ልክ የተሰሩ ናቸው ፡ ነገ አዳዲስ የቤት እቃ የጫኑ መኪኖች ይደርሳሉ ። መብራትና ውሀም አትከፍሉም ። መስራት ለምትችሉ የስራ እድል ይዘጋጃል ፡ ለአቅመ ደካሞችና ማብሰል ለማይችሉ ደግሞ ዘመናቸውን ሙሉ የሚፈልጉትን መርጠው የሚመገቡበት መመገቢያ አዳራሽም ተገንብቷል ። የናንተ ውለታ ከዚም በላይ ነው አላቸውና ፡ ከመድረኩ ወረደ ።
............
በሌላ ሀገር ፡ አንድ ግለሰብ ለወገኖቹ ይህን ያህል ያስባል ፡ በኛ ሀገር ደግሞ ፡ የምስኪኖች ቤት ሀላፊነት ሊሰማው በሚገባ በመንግስት አካል ፈርሶ ቤተሰብ ሜዳ ላይ ይበተናል። ልዩነታችን ይህን ያህል ነው።
Wasihune Tesfaye
1.1K views17:28