2023-06-04 16:05:41
የሰው ወርቅ አያደምቅ!
(የማይደበዝዙ ምክንያታዊ ሂሶች)
ከዓመታት በፊት በአንድ ኮሌጅ የምሽት ፕሮግራም አንድ የዓለማቀፍ ህግ ኮርስ እሰጥ ነበር፡፡ ከተማሪዎቹ መሐል ህግን የማወቅ ፍላጎት ያደረባቸው በተለያዩ ፕሮፌሽኖች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ይገኙ ነበር፡፡ እና ይህ በሌላ ሙያ ፒኤችዲ ያለው ዶክተር.. እኔ ክፍል እየገባ ይማራል፡፡
ዶክተሩ ተማሪ በጣም ደስ የሚሉ የመጠቁ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን በነጻነት ይሰጣል፡፡ ያልገባውን ማንኛውንም ነገር አያልፍም፡፡ ያልተስመማባቸው ነገሮች ካሉም አያሳልፍም፡፡ በጣም እወደዋለሁ፡፡
.. በየሙያችን የያዝነውን ይዘን ወደሌላ የትምህርት መስክ ስንቀላቀል.. ሰፋ ያለ አድማስ ይዘን ነው የምንቀላቀለው፡፡ ብዙ insight እና አቅም ይሰጣል፡፡ አንዳንዴ በምዕራቡ የአንግሎ-ሳክሰኑ ዓለም ህግ ለመማር መጀመሪያ በሌላ ሙያ ዲግሪህን መያዝ ለምን እንደቅድመ ሁኔታ እንደተቀመጠ... ሳስብ.. ይሄ ሰው ትዝ ይለኛል፡፡ በእርግጥም ያ ልማድ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው እንደዚህ ሰው ያሉ ጥቂት የማይባሉ ክሪቲካል ሰዎችን እያየሁ በቂ ምስክር ሆነውኛል፡፡
ታዲያ የተለያዩ ሙያዎችንና ልምዶችን ይዘው ወደመጡ ተማሪዎች ስገባ... (በተለይ በምሽት ፕሮግራሞች ላይ) ተማሪዎችን ለማሳወቅ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ተማሪም ሆኜ ነው፡፡ እና ጓደኞቹን እንደሚያገኝም ሰው ሆኜ፡፡ ብዙ ነገር ለራሴም ይዤ ለመውጣት ነው የምገባው፡፡
አሁን የወጣለት ፖለቲከኛ የሆነው የቀድሞው የሎውስኩል ሲኒየሬ ፀጋዬ ረጋሳ (አሁን ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ)፣ በአንድ ወቅት በህግ ት/ቤት የተማሪዎች መፅሔት ላይ ያሳተማት ደስ የምትል አርቲክል ትዝ ትለኛለች፡- ‹‹ዴሲዶ ዴሰመስ - እየተማሩ ማስተማር›› የምትል ነበረች፡፡ በመምህርነት ባሳለፈው ልምዱ ካስተማረው እኩል ከተማሪዎቹ ብዙ ነገሮችን እንደተማረ በማስመልከት የጻፈው ነው፡፡ ከጥንት ላቲን ጀምሮ የነበረ ልማድ፡፡ ‹‹ዴሲዶ ዴሲመስ››፡፡ እያስተማሩ መማር፡፡ ጥሩ አድርጎ ነበር የፃፈው፡፡
ታዲያ እኔም ‹‹ዴሲሞ ዴሲመስ›› ሆነና... ስለ ዓለማቀፍ ህግ ምንጮች.. (ከየት ከየት ተለቅሞ ነው የመጣው የዓለም ህግ?)... የሚለውን እንደወትሮዬ በተቻለኝ መጠን መሳጭና ሰፋ ያለ አድርጌ ለተማሪዎች አቀረብኩ፡፡ ሶስት አካባቢ ክላሶች የፈጀብኝ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ዶክተር ተማሪ ያለወትሮው ያለምንም ጥያቄና አስተያየት ሁሉንም እስክጨርስ ኖት እየያዘ ሲያዳምጥ ቆየና በመጨረሻ ግን ‹‹አሁን ወደሌላ ርዕሰጉዳይ እንሸጋገራለን›› ስል... ንዴቱን መቆጣጠር አቃተው! እና እንዲህ አለኝ... በጣም በንዴት ተሞልቶ
‹‹ቆይ እናንተ የዚች ሀገር ምሁሮች... ምንድነው የነካችሁ ነገር?
በጣም ነው የሚገርመኝ! አሁን አንተ የዓለም ሀገሮችና ታሪኮች
ሁሉ እንዴት አሁን ላለው የዓለማቀፍ ህግ ሥርዓት ምን
እንዳበረከቱ... እንዲህ ደስ በሚል ሁኔታ እየተነተንክ
ስታስረዳ ቆይተህ... እንዴት የራስህ ሀገር ኢትዮጵያ
ለዓለማቀፍ ህጉ ያበረከተችውን... አንዲት እንኳ አስተዋፅዖ
ሳትናገር... ሳታጠና.. ሳትፈልግ... ሳታዘጋጅ... አበቃሁ ትላለህ?
‹‹በቃ አለቀ? ኢትዮጵያ አንድም አበርክቶት የላትም
ለዓለምዓቀፍ ህግ? ... ለምን የሌሎችን ከምታነበንቡ
(ከይቅርታ ጋር - እያለኝ እኮ ነው ልክ ልኬን የሚነግረኝ)..
ለምን ጊዜ ወስዳችሁ...
የራሳችንን አጥንታችሁ አታስተምሩንም?!
‹‹ሌሎች ፈረንጆቹ.. ሁሉም.. የራሳቸውን አስተዋፅዖ በመፅሐፍ
አሳትመው እናንተን አስተማሩ... እናንተ ደግሞ የኛን አስተዋፅዖ
አጥንታችሁ ልታስተምሩን ሲገባ... ያንኑ የእነሱን አምጥታችሁ
ትነግሩናላችሁ? ...
‹‹እኛ አስቀድመን ክርስትያንና ሙስሊምን አብረን ያኖርን
ሀገር አይደለንም? የሌሎችን የሐይማኖት ነፃነት የማክበር
ልምድን ለዓለም አላሳየንም እኛ? የውጭ ሀገራት ቆንሲሎችንና
መልዕክተኞችን እየተቀበሉ ጠብቀው፣ አክብረው፣
ተንከባክበው ወደመጡበት የሰደዱ ጥንታዊ ንጉሣን
አልነበሩንም እኛ? ..
‹‹ለዓለማቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ህግ ያበረከትነው ምንም
አስተዋፅዖ የለም? ሴቶች በኛ ሀገር ንግሥት ሆነው አልኖሩም?
ለሴቶች እኩልነት ዓለማቀፍ ህግና አስተሳሰብ እኛ
ያበረከትነው ምንም ነገር የለም?
‹‹በጦርነት ምርኮኞችን የመንከባከብ፣ ቁስለኞችን የማከም
ልማድ በእኛ ዘንድ የለም? የሌሎችን ድንበር የማክበር...
የራሳችንን የማስከበር... ከጥንት ጀምሮ ያቆየነው ልማድ
የለንም እኛ ኢትዮጵያውያን? ከአፍሪካ ብቸኛዋ
በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ውስጥ አባል ሆና ያበረከተችው
አስተዋፅዖ የለም ይቺ ሀገር...?
‹‹እና በቃ ‹‹የዓለማቀፍ ህግ ምንጮች›› ብለህ... የሌሎችን
የአውሮፓዎችን የቱርኮችን የራሺያኖችን የአሜሪካኖችን.. ወዘተ
አስተዋፅዖ ብቻ እነሱ እንዳስተማሩህ ዘርዝረህ... በቃ
ጨርስክ ትምህርቱን እዚህ ላይ? የኛስ አስተዋፅዖ?
‹‹ለምን የኛን አስተዋፅዖ አጥንተህ፣ መርምረህ፣ አታስተምረንም?
አንተና አንተን የመሰሉ ሰዎች ካላጠናችሁት የኛን አበርክቶት...
ማነው የሚያጠናልን? ማን ያጥናልን? በጣም ነው የማዝነው
በኛ ነገር አሣፍ! በተለይ ካንተ ብዙ እጠብቅ ነበረ... !
በጣም ነው የማዝነው››
ብሎኝ ንዴቱ እንደፋመ አበቃ! ልክ እንደ ትልቅ ሌክቸር ነበር የቆጠርኩት በእውነት! አፈርኩ! ዓይኔን ነው የገለጠልኝ፡፡ ብዙ መጻሕፍት ነበሩኝ በዚህ ጉዳይ፡፡ ብዙ አነባለሁ፡፡ ደስ የሚለኝም ርዕሰጉዳይ ነበር፡፡ ግን ለአንድም ቀን... ያገሬስ አስተዋፅዖ ምንድነበር? እስቲ ላጥናው! ላደራጀው! አሳምሬ ልወቀው... እና እንደ አንድ የኮርስ አጋዥ ማቴሪያል... ለሌሎች ላስተምረው... የሚል ሃሳብ በጭራሽ መጥቶብኝ አያውቅ ነበር፡፡
የዶክተሩ ወቀሳ ትክክል ነበር፡፡ በከፍተኛ ተመስጦና በትዕግሥት እስኪጨርስ አዳመጥኩት፡፡ አፈርኩ! አመንኩለት፡፡ ሌሎችም ብዙ አስተያየት ሰጡ፡፡ እና አንድ ኮርስ አድርገህ ራሱ ብታስተምረን በኛ በኩል የፈለገውን እናደርጋለን፣ ለኮሌጁም ማሳወቅ እንችላለን ትብብር ከፈለግክ አሉ፡፡ ሁሉም በየራሱ የተለያየ ሃሳብ አዋጣ፡፡ የሚገርም አካዳሚክ አርበኝነት ነገሠ በዚያች ጠባብ የምድር ክፍል፡፡ እና እያስተማርኩ ተማርኩ፡፡
አሁን ብዙ ዓመቶች ተቆጠሩ፡፡ በየአጋጣሚው የዓለማቀፍ ህግን የተመለከቱ ነገሮች በሰማሁ ቁጥር ያ የዶክተሩና የክፍል ተማሪዎቹ ንግግሮች በሀሳቤ ውልብ ይላሉ፡፡ አደራቸው ጎሸም ያደርገኛል፡፡ በእርግጥ እኔ የዓለማቀፍ ህግ ምሁርም አይደለሁም፡፡ የማውቃትን ታህል ለሌሎች ለማካፈል ጥረት የማደርግ አንድ ተራ ሰው ነበርኩ፡፡
ግን በሀገራችን በዚህ ዘርፍ ብቻ ራሱን ችሎ ያጠኑ፣ የተመራመሩ፣ ብዙ ነገሮችን የዳሰሱ ጥቂት የማይባሉ የዓለማቀፍ ህግ ምሁራን እንዳሉን አውቃለሁ፡፡ በየአካዳሚክ ተቋማቱ ያሉ፡፡ ብዙ አሉን፡፡ ግን ይሄን እኔ በወቀሳ የቀረበልኝ ጥያቄ ቀርቦላቸው ያውቃል ወይ?... ይሄንን ለማድረግስ ተነሳስተው ይሆን ወይ? የተሠሩ ጥናቶችስ ይኖሩ ይሆን ወይ... ? ለዓለም የኛን አስተዋፅዖ ቆጥረው ለክተው በማስረጃ አስደግፈው የሚያስረዱልን? አላውቅም፡፡ ብዙ ርቄያለሁ፡፡ እንኳ በመጻፉ፣ በማንበቡም የለሁበት፡፡
1.9K views13:05