2023-07-01 20:17:00
ግዜው 1860 ነው። ሬት በትለር 35 አመት ሞልቶታል። የእርስ በእርስ ጦርነቱ ሊጀምር ነው። ሁለቱም ወገኖች የጦርነት ድቤ እየደለቁ ነው። ደቡባውያኑ ሰፋፊ የጥጥ እርሻ ያላቸው ሃብታሞች ናቸው። እርሻው የሚለማው በባሮች ጉልበት ነው። ሰሜናውያኑ በበኩላቸው ባርነትን አጥፍተው ህገወጥ አድርገውታል። በምትኩ ትላልቅ ኢንደስትሪዎችን ተክለዋል።
አብርሃም ሊንከን ለፕሬዚዳንት ሲወዳደር ከተመረጠ ባርነትን ከመላው አሜሪካ እንደሚያጠፋ ቃል ገባ። ምርጫውን ሲያሸንፍ የገባውን ቃልኪዳን ለመጠበቅ ስራውን ጀመረ። አንድ ሃገር በሁለት የተለያየ ስርአት መተዳደር እንደሌለባቸው አወጀ። ይኼኔ ሁለቱም ወገኖች ተቆጡ።
ደቡባውያኑ ያላቸው አንድ ነገር ሰፋፊ እርሻ ነው። ባርነት ከተወገደ እርሻቸውን ማን ያለማላቸዋል? በባሮች ትከሻ ቀለል ያለ ኑሮ የሚኖሩ ህዝቦች ነበሩ። የባርነት ስርአትን ማፍረስ ያንን የተንደላቀቀ ህይወት መሰናበት ነው።
ሬት በትለር ግን እንደ ሌሎቹ ደቡባዊውን አይደለም። የኮንፌዴሬሲው ባንዲራ ሲውለበለብ ሰውነቱን አይወረውም። ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር አይነሽጠውም። እንዲያውም ሬት እንዲህ ይላል፦
"ሃገር ስትበለጽግ አብሮ ሃብታም መሆን ይቻላል። በተቃራኒው አለም ወደ ውድቀት ስትንደረደር የበለጠ እጥፍ ሃብታም መሆን ይቻላል።"
በዚህ ፍልስፍና እየተመራ ሬት በሙሉ ሃይሉ ወደ ኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ ይገባል። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የማይሸጠው ቁሳቁስ አልነበረም—ከሽቶ እስከ መሀረብ፣ ከመጠጥ እስከ ልብስ። ሬት በትለር መላው ሃገር ወደ አመድነት ቢቀየር ግድ የሚሰጠው ሰው አይደለም። ለሱ ዋጋ ያላቸው ነገሮች የንግድ ስራውና ትርፉ ብቻ ናቸው።
ጦርነቱ ሲገባደድ ሬት ሚሊየነር ሆኗል። ይህ ሃብት በብዙሃን ደም የተገኘ ነው። ሬት በተደጋጋሚ የሚጠቀማት አንድ ሃረግ አለች፦
"እንደ እውነቱ ከሆነ ውዴ ምንም ግድ አይሰጠኝም።"
አዎ ሬት ግድ አይሰጠውም። ሃገሪቷ በእሳት ብትነድ ግድ አይሰጠውም፤ ሚሊየኖች ቢሞቱ ግድ አይሰጠውም፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ቀውስ ቢሰፍን ግድ አይሰጠውም። ለሬት ግድ የሚሰጠው አንድ ነገር ብቻ ነው—ገንዘብ፣ እጅግ ብዙ ገንዘብ። ገንዘብ የሚያስገኝለት ከሆነ ለመስዋዕትነት የማያቀርበው ነገር የለም። አለማችን ወደ ሲኦል የምትንደረደረው በነዚህ አይነት ሰዎች ምክንያት ነው።
¤¤¤
ነገም ሌላ ቀን ነው ውስጥ በጣም የምወዳት ገጸባህሪይ ሜላኒ ሃሚልተን ነች። ልቧ ትልቅ ነው— ያለ ምንም ተቀጥላ ምክንያት ሁሉንም እኩል ትወዳለች። አምስት ደቂቃ አብሯት ያሳለፈ ሁሉ ይወዳታል። ነፍሷ ምትሃታዊ ባህሪ አለው። ሰዎች ለራሳቸው እንኳን የማይታያቸውን ጥሩነት በማየት ዘወትር ታስደንቀኛለች።
ሰዎች ላይ አትፈርድም። ሁሉንም እንዳሉ ትቀበላቸዋለች ጨካኝና መጥፎ እንኳን ቢሆኑ። ልቧ ግዙፍ ስለሆነ ለሁሉም የሚበቃ ቦታ አላት።
ደቃቃ ብትሆንም ደፋር ናት—ፍርሃት የሚባል ነገር አልፈጠረባትም። ትልቅ ነፍሷ ትንሹ ሰውነቷን ሸፍኖታል። በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና እንኳን አትፈራም። እንደዚያ አምርራ የምትጠላት ስካርሌት እንኳን በሃቀኛነቷ ታከብራታለች። በአረብኛ እንዲህ የሚል አባባል አለ፦
"ለልበ ንጹህ፣ ሁሉም ንጹህ ነው"
.
እኔ ደግሞ በልብወለድም ይሁን በእውነታ ከሜላኒ የበለጠ ንጹህ አልገጠመኝም።
¤¤¤
እስካርሌት ከአሽሌይ ድብን ያለ ፍቅር ይዟታል። ከሱ ጋር ለመሆን የማትፈነቅለው ድንጋይ፣ የማታደርገው ነገር የለም። እሱ ግን እስካርሌትን ትቶ የምትመስለውን፣ የሚመስላትን ሜላኒን አገባ። ይኼኔ እስካርሌት አረረች ፤ ቆሽቷ ደበነ።
እስካርሌት ለሶስት ግዜ ያህል አግብታለች—ግን አንዱም ለፍቅር አልነበረም። ሌላ ድብቅ አላማ ነበራት—ቁሳዊም ሆነ ሌላ።
በመጨረሻ ሜላኒ በወሊድ ሞተች። አሁን ህይወቷን ሙሉ ስታሳድደው የኖረችው አሽሌይ ነጻ ሆነ። ነገር ግን ለሱ የነበራት ስሜት ሁሉ ተኖ ማለቁ ገረማት።
አሁን የሚወዳትን ሬት መውደድ ጀመረች። ነገር ግን ረፍዶ ነበር። እሷ ለአሽሌይ የነበራት ስሜት እንደሞተ ሁሉ፤ ሬት ለሷ የነበረው ስሜት ሞቷል። የምትወደውን አሽሌይን ስታሳድድ የሚወዳትን ሬትን አጣች። እስካርሌት ግራ የሚያጋባ የህይወት እንቆቅልሽ ሲገጥማት ዘወትር እንደዚህ ትላለች፦
"ይሄን ዛሬ አላስበውም። ነገም ሌላ ቀን ነው!"
¤¤¤
በማያልቅ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ለምንኖረው እኛ ይሄ መጽሐፍ ትልቅ መልእክት አለው። ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ አለመማራችንን ነው ይባላል። እንኳን ከአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ከራሳችንም ታሪክ አልተማርንም። በናፍቆት የሚጠበቅ የኦሎምፒክ ውድድር ይመሰል በየ10 አመቱ ጦርነት እንገጥማለን።
Tewodros Shewangizaw
1.3K views17:17