2023-04-29 22:26:43
ሠይጣኑን እንዴት ጠብቀኸው ነበር?
(Reframe your expectations! መነፅርህን አሁኑኑ አስተካክል!)
በናዚ ዘመን የሒትለር የቅርብ ሰዎች ከነበሩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሐል ለሂትለር ጦርነቶች የሚያስፈልጉ የሎጂስቲክ አቅርቦቶችን በማስተባበርና ሒትለርን የሚያስደምሙትን ግዙፍ የምህንድስና ግንባታዎች በመንደፍ ያገለገው የሒትለር መሃንዲስ፣ አልበርት ስፒር፣ የናዚ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሞት ሲቀጡ፣ በህይወት እንዲተርፉ ከተፈቀደላቸው እጅግ ጥቂት ዕድለኞች አንዱ ነው።
(በህይወት ተርፎም ከእስር ተለቆ በሠላም በነፃነት ኖሯል። ይህን ተስተካካይ የሌለውንና እስከዛሬም በዋና ምንጭነት ተደጋግሞ ሲጠቀስ የሚኖር የቅርብ ምስክርነቱን የያዘ.. ስለናዚ መንግሥትና ስለመሪው ሒትለርና ሸሪኮቹ ሰብዕና የሚተነትን እጅግ ተደናቂና አስደማሚ መፅሐፍም ሊያሳትም በቅቷል ስፒር።)
በዚህ መፅሐፍ አልበርት ስፒር በቅርብ ስለሚያውቀው ሂትለር ሲናገር ደጋግሞ የሚገረመው በሒትለር የተግባቢነት፣ የሰው አክባሪነትና የቅለት ባህርያት ነው።
ሂትለር "ከተራው ሕዝብ" ጋር ሲሆን እጅግ ቅለት የሚሰማውና ነፃ ሆኖ የሚገኝ ትሁትና ሰው-አክባሪ ሰው እንደሆነ ይናገራል አልበርት ስፒር።
የሒትለርን ነፍስ እጅግ ዘና ብላና ነፃነትን ተቀዳጅታ የምታያት ቀሪው ዓለም በሚያውቀው የሆነ የንግግር መድረክ ላይ ሲወጣ፣ አሊያም በሆነ ቦታ በተዘጋጀለት የክብር ሥፍራ ላይ አልነበረም።
ሒትለር ወደ መድረክ ከመውጣቱ በፊት በአካባቢው ከሚያገኛቸው ሠራተኞችና ባለሙያዎች ጋር እንደ ጓደኛ ሆኖ ማውራት በጣም የሚያስደስተው ሰው ነበር ይለናል ስፒር።
ለበታቾቹ ሠራተኞች ከፍ ያለ አክብሮት ነበረው ሒትለር። ምግብ ቤት ገብቶ ስለቀረበለት ምግብ፣ ወይ ስለ አስተናጋጁ፣ወይ ስለለበሱት ልብስ፣ ወይ ስለመጡበት ሀገር ጠይቆ፣ የሆነ ሰዎቹን የሚያደንቅበትና የሚግባባበት አስተያየቱን ሳይሰጥ አይወጣም ይለናል።
አንዴ የሆነ ምግብ ቤት ገብቶ አስተናጋጁን ሲያዋራው ከኦስትሪያ ነው የመጣሁት ይለዋል። እና ሒትለር እሱም ከኦስትሪያ እንደመጣ ለአስተናጋጁ አውርቶለት፣እንዴት ባንዴ የወንድማማችነት ስሜት በመካከላቸው እንደፈጠረ ያስታውሳል አልበርት ስፒር።
ሂትለር አንዴ፣ ለአንዲት ቀን፣ ከብዙ ዓመት በፊት፣ መንገድ ላይ፣ ወይ የሆነ መሥሪያቤት ውስጥ፣ ወይ በሆነ አውቶቡስ ላይ፣ ያገኘውን ሰው ከነታሪኩ፣ ከነስሙ፣ ከናወሩት ነገር አይረሳም ይለናል ስፒር በመደነቅ።
ሂትለር ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ከወጣ በኋላ ራሱ በሆነ አጋጣሚ እነዚያን ቀድሞ ተራ ኑሮ እየገፋ ያገኛቸውን ሰዎች ሲያገኝ፣ በፍፁም ትህትና ራሱን አቅልሎ የድሮውን ትዝታ ልቅም አድርጎ እያስታወሰ ሲደሰቱ ማየት የሚያረካው ተግባር እንደሆነ ይመሠክራል ስፒር።
ሒትለር በቢሮው የሚሠሩ ሰዎችን ሳይረሳ ስለቤተሰባቸው ጉዳይ ይጠይቃል። ሳይረሳ ስለጓደኞቻቸውና ስለታመሙ ዘመዶቻቸው ሳይቀር ይጠይቃል። ወጣት ሠራተኞቹን "እስከማጣበስ" የደረሰ የወጣትነት፣ የጓደኝነትና የቅንነት ስሜት ለበታቾቹ እንደሚያሳይ ይናገራል።
ሌላ ቀርቶ በልጅነቱ ያከመውን የጥርስ ሃኪም የነበረ ትውልደ-እስራኤላዊ ዶክተሩን አስታውሶ፣ እስራኤሎቹን ማፈስና መግደል ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ከጀርመን እንዲወጣ አድርጎታል። ሊያተርፈው።
(በእርግጥ ይህ የሒትለር ችሮታ ባንድ ሰው ብቻም የተወሰነ አይመስልም። የሀርቫርዱ ብራየን ሪግ በቅርብ ዓመታት አጥንቶ በፃፈው "የሒትለር ጂዊሽ ወታደሮች" መፅሐፍም ላይ ሒትለር ብዙ የእስራኤል ደም ያላቸው ባለኒሻን ወታደሮችን እንደሙሉ የጀርመን ዜጋ እንዲቆጠሩ የፃፋቸው መመሪያዎች ተመልክተዋል።)
(በእርግጥ ሒትለር አስከፊ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ በሚዋኝበት በመጨረሻው ራሱን ሊያጠፋ በወሰነበት ቅፅበቱ ላይ ራሱ፣ ሠራተኞቹን ከፀሐፊዎች እስከ ወጥቤት ሠራተኞቹ ድረስ እየዞረ የሞቀ ሠላምታ አቅርቦና መልካሙን ተመኝቶ እንደተሰናበታቸው በብዙ የህይወት ታሪክ ዝክሮቹ ተዘግቦለት ይገኛል።)
"... he acted in a friendly way to “the little guy”. To his secretaries, to their husbands. He’d play matchmaker for his staff. Inquire about the children of friends. Allow his old Jewish childhood dentist to leave the country unharmed before the Holocaust kicked off…."
ሒትለር በፈለገው ርዕሰጉዳይ ላይ ላቅ ያሉና የበሰሉ ውይይቶችን የማድረግና በርቱዕ አንደበት የማስረዳት ብቃት ቢኖረውም፣ ብዙ ጊዜ ከተራ ሰዎች ጋር ሲሆን የሚሰማው የመንፈስ ቅለት፣ ከተከበሩና በተለይ "የትልቅሰው ዘር" ተብለው ከሚቆጠሩ (በስማቸው ላይ "ቮን" የሚል የክብር መጠሪያ ከተደረበላቸው ሰዎች) ጋር ሲሆን ግን የመዝናናት መንፈሱ በቁጥብነትና በሲሪየስ ሙድ እንደሚቀየር የታዘበውን ፅፏል ስፒር።
የሚገርመው፣ እነዚያም አንቱታ የተቸራቸው ብዙዎቹ ሰዎች የቱንም ያህል ከሒትለር ጋር ለጥቅማቸው ወይም ላገራቸውም ጥቅም አብረው ቢሰለፉ፣ ነገር ግን በግል ቀርቦ ላዋያቸው በሚስጥር ሒትለርን የሚጠሩት "ያ ጭባ ወታደር" እያሉ ነው ሲል ይመሠክራል ስፒር።
ሒትለር የቱንም ያህል በሥልጣንና በኃይል ተምዘግዝጎ ቢወጣ፣ ለእነዚህ ሰዎች ሒትለር ማለት ከሚገባውና መገኘት ከነበረበት የህይወት ሥፍራው አጓጉል አጥር ዘልሎ ባልዋለበት ያለሥፍራውና ያለደረጃው የተገኘ፣ መደዴ ሰው፣ አሊያም ይሉኝታና የጨዋ መገራት ያልጎበኘው ተራ ዓይንያወጣ ወንበዴና ሽፍታ ሆኖ ነበር የሚታያቸው። ተጀምሮ እስኪጨረስ።
ሒትለር በበኩሉ ለምን ከእነዚህ ከበርቴዎች ጋር ሲሆን ከተራው ሕዝብ ጋር ሲሆን የሚሰማውን ዓይነት ቅለትና የሚታይበትን ትህትና እንደማይላበስ ስፒር ሲያስረዳ፣ ምናልባት ሒትለር በጅምሩ ለከበርቴዎቹ ከፍ ያለ ትህትናና አክብሮት ቢኖረውም ለእርሱ የናዚ ዓላማና ለሀገር ጉዳይ ግን የፈለገውንና የጠበቀውን የገንዘብም ሆነ ሌላ እገዛ ለማድረግ ፈቃደኝች ሆነው ስላላገኛቸው፣ ነገሩ ሲደጋገም፣ ለእነዚህ "ጩቆች" ትሁት መሆን አስፈላጊ አይደለም የሚል አቋም ላይ ደርሶ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳል።
የሆነ ሆኖ አልበርት ስፒር እጅግ ተደንቆ እኛን አንባቢዎቹንም የሚያስደንቀን በሒትለር ውስጥ ተዳብለው ስለሚገኙት እጅግ የተራራቁ ሰብዕናዎች ሲናገር ነው።
በአንድ ሥፍራ ፉህረሩን (አዶልፍ ሒትለርን) ሲገልፀው ደስ በሚል ቋንቋ እንዲህ ይለዋል፦
"Hitler is a great and enduring paradox, an enigma — boundless evil in an often surprisingly polite package. A sea of anger and hatred, brewing underneath a surface that could be deceptively charming."
"ሒትለር ራሱን የቻለ አንድ ትልቅና ሳይፈታ ብዙ የሚዘልቅ ምሥጢር ነው። መጨረሻ ሊበጅለት የሚያዳግት ከፍ ያለ እርኩስ መንፈስ፣ እጅግ ትሁት በሆነ መጠቅለያ ውስጥ ተጣምሮ የሚገኝበት ፍጡር ነው። ባህርን የሚያስንቅ ንዴትና ጥላቻን ያቆረ ሰው፣ በሚያስገርም የማደንዘዝ ኃይል፣ እጅግ ማራኪና ውብ በሆነ ተጫዋችና ሩህሩህ ሰብዕና ውስጥ ተጠልሎ ይገኛል። የሒትለር ነገረሥራ ራሱን የቻለ እንቆቅልሽ ነው...።"
1.2K views19:26