2023-07-06 14:43:14
#አልኬሚስቱ
---
በመካከለኛው ዘመን የተነሱ ብረትን አቅልጦ (አንጥሮ) በማጣራት ወደ ወርቅ ለመቀየር ለተጉ የግኝት ባለቤቶች የተሰጠ ስያሜ ነበር፤ አልኬሚስት። ከቅዠት የተወሰደው መገለጣቸው ከመወገዝ አላዳናቸውም ነበር፤ የሚረዳቸውም አልነበረም።
አልኬሚ ብረትን ወደ ወርቅ ከመቀየር የሚልቅ ሐሳብ አለው። አልኬሚ የልውጠት (transformation) ጥበብ ነው። የነበረውን ማንነት ወደ ላቀው ምንነቱ የማሻጋገር ጥበብ ነው። ሂደቱ የነገሮችን ምንነት በመረዳትና በከፍተኛ ደረጃ በማጣራት የምንነታቸውን የላቀ ልዕልና እንዲወርሱ የማድረግ ጥበብ ነው።
ሰዎች የተሰጣቸውን ተፈጥሯዊ ዕምቅ ኃይልና ድንቅን የማድረግ ጥበብ መጎናጸፍ የሚችሉት ልቡናቸውን በማጥራት ልምምድ ውሰጥ ሲያልፉና ከተሰጣቸው ታላቅ ማንነት ጋር ሲተዋወቁ መሆኑን ካርል የንግን ጨምሮ አንጋፋዎቹ የሥነልቡና ባለሙያዎች ያትታሉ፡፡
በየዘመኑ ይህን ልምምድ ከውነው በመገለጥ ውስጥ የሚኖሩ አልኬሚስቶች በምድራችን እንደሚከሰቱ ይሰማኛል፤ ልብ ስል።
ለአለፉት ሃያ ዓመታት በምድራችን የተከሰተ አልኬሚስት ነበር፤ ኤሊያስ መልካ! ስምን «መልአክ ያወጣዋል» እንዲሉ፣ «መልክኣ ጥበብ» ብንለውስ!? እርግጥ «መልካ» በአማርኛም በኦሮምኛም (ምናልባት በጉራግኛም) ተቀራራቢ ትርጉም አለው፤ መንጋው (ብዙ እንስሳት) ውኃ የሚጠጡበትና ለመሻገርም ምቹ የሆነ የአንድ ወንዝ ወይም ጅረት አካል ነው። ኤልያስ ከአልኬሚስትነት አልፎ፣ ስሙ እንደሚነግረን፣ ብዙዎችን የጥበብ ሰዎች በጥበቡ ሲያማክል (ማዕከል ሲሆን) የጥበብ ታዳምያንንም ጥበብ ሲያስጎነጭ፣ ጥበብንም ከዘመን ወደዘመን ሲያሸጋግር የኖረ ግለሰብ ሳይሆን ጀማ (ብዙኃን ሊሰኝ የሚችል) ነበረ። ለዚህ ነው ከመልካነት መገኘትን መልአክ ነው ያዘዘው ያልነው።
በዚህ ዘመን የሚወጡ የጥበብ ሥራዎች፣ በተለይም የሙዚቃ ጥበባት አብዛኞቹ ጠዋት ተዘፍነው እረፋዱ ላይ የሚረግፉ የማለዳ ጤዛ ሆነው አስተውለናል። ዘመን ተሻግረው በጥበብ ክፍታችንን የሚሞሉ፣ ውበታችንን የሚገልጹ፣ ሰናይነታችንን የሚያንጸባርቁ፣ ዕኩይነታችንን በድፍረት የሚኮንኑ የሙዚቃ ውጤቶች ጥቂቶች ናቸው። እነዚህን ዓይነት ዘመን ተሸጋሪ የጥበብ ፍሬዎች ለማፍራት ከተለመደውና ከድግግሞሹ ማምለጥ ሊስፈልግ ይችላል፡፡
የውስጣቸውን መገለጥ አጋርተውን አዲስ መንገድ የሚሠሩልን የጥበብ ሰዎች "ለጥበብና ለሕዝብ የሚወግነውን ብቻ ልሥራ" ብለው፣ የውስጥ ስሜታቸውንና አመለካከታቸውን ለወገን በመሰዋት (social desirability) የሚጸኑት ከራሳቸው ጋር መተናነቅ ካልፈሩ (fear of knowing the self) ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በተለየ መልኩ የሚያስብ ሻል ያለ የግል ምልከታ ያለው ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል።
አለበለዚያ ማኅበረሰቡ እንደሚፈልገውና እንደገበያው ሁኔታ ያተኮሩ "እጅ እጅ" የሚሉ (monotony) ሐሳቦችን ብቻ ለማመንዠክ እንገደዳለን። ይህ ብቻም አይደለም፤ ዘፋኞች ለማኅበረሰብና ለራስ ጥቅም ፍላጎት ሲገዙ፣ በውስጣቸው የማይቀበሉትን ሐሳብ የለበጣ ሲዘምሩትም ይታያል።
ከተለመደው ነገር ለመውጣትና ውስጥን አዳምጦ ውስጥን በማስዋብ (As within So without/ "እንደ ልቦናችን ደጃችን " እንዲሉ ጥንታዊ አልኬሚስቶች) ዓለምን ማስዋብ እንደሚቻል የሚያሳዩን ጥቂቶች ናቸው። የዚህ ዓይነት የላቀ ሰብእና ለመጎናጸፍ በሚደረጉ ጥረቶች መሐል ሌሎችን አብሮ የማነጽ ኢላማ የተሳካላት ድንቅ ነፍስ የኤልያስ መልካ ናት።
ለቁጥር የሚያዳግቱ ባለተሰጥኦ ነፍሶችን የላቀው ማንነታቸውን እንዲጎናጽፉ ያስቻላቸው፣ ወደ ወርቅነት ያሸጋገራቸው አልኬሚስት ኤሊያስ መልካ ነው። የተሰጠው ¹ ELIXIR OF LIFE በጸጋው ላይ ሲያርፍ ዘላለማዊነት ይናኝበታል። ይህ የዘመን ክስተት ለጆሮ ብቻ ሳይሆን፣ ለፍሳችን ንጽሕና ሲጠበብ የኖረ ጠቢብ ነው።
ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ጎሳዬ ተስፍዬ፣ኢዮብ መኮነን፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ታደለ ሮባ፣ ትግስት በቀለ፣ አብነት አጎናፍር፣ ገረመው አሰፍ፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ይርዳው ጤናው፣ ጌቴ አንለይ፣ ጆኒ ራጋ፣ ኃይሌ ሩት፣ ጌዲዮን ዳኔል፣ እንዳለ አድምቄ፣ ቤሪና፣ ዳን አድማሱና ሌሎች በኤሊያስ መልካ የጥበብ እጆች ተገርተው ዳግም የተፈጠሩ ድምጻውያን ናቸው፡፡
ኤሌያስ በጥበብ ውስጥ ነጻነቱን አስከብሮ ከተሰለቸው ልማድ በማፈንገጥ፣ ያበረከታቸው የሙዚቃ ሥራዎች ማኅበረሰቡን የሚያንጹና ተስፋንም የሚሰንቁ እንጂ፣ ዝሙትና ውርዴ ሐሳብን የሚለፍፉ አልነበሩም፡፡ የኤሊያስ ፈጠራዎች የዚህ ዓይነት ፣ራዎችን ይጠየፋሉ። ለዚህ ዋቢ አንዲሆን፣ በኢዮብ መኮነን፣ በዘሪቱ ከበደና በጌቴ አንለይ ላይ ያሰረጸውን የግጥም ጨብጥ ልብ ይሏል፡፡
ኤሊያስ ትቶን እስኬደበት ጊዜ ድረስ፣ ሙዚቃን በክብር ሲራቀቅበት ቆይቷል፡፡ የተሰጠውን መክሊት ተጠቅሞ አሻራውን በማኖር፣ ስሙንና ሥራዎቹን ዘላለም አጽድቆ፤ ተከታዮቹን ደግሞ በልባቸው ብርሃን ፈንጥቆ ተሻግሯል፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት አለ፡፡ ከዚህም ተተኪዎቹና አዲሱ ትውልድ ሊወርሳቸው ከተገባቸው ወርቃማ መርሖች መካከል ቀጣዮቹን (በኮመንት ሳጥኑ ውስጥ የሚገኙትን) በጥሞና እንድናጤናቸው የአልኬሚስቱ ኤሊያስ ሕይወት ሹክ የሚለን ይመስለኛል፡፡…
Surafel Ayele
822 views11:43