2022-08-21 10:32:11
_#ግእዝ #ክፍል ፷፩_ሙሻዘር ከክፍል 60 የቀጠለ
#ዘመድ #ዝርዝር
ዘመድ ዝርዝር የሚባለው በየራሱ የሚዘረዘረው ነው። ለምሳሌ አምላክ ሞቶ ለአዳም ሲል በይኔሁ/ሎቱ ይወጣሉ ትርጉሙ ስለእርሱ/ለእርሱ ለአዳም ስለ አዳም አምላክ ሞተ ማለት ነው።
-
ቦቱ ሲወጣ:-አምላክ ተሰቅሎ ለመስቀል ይላል ትርጉሙ በእርሱ በመስቀል አምላክ ተሰቀለ ማለት ነው።
-
እምኔሁ ሲወጣ:-ነጋዲ ወጽኦ ለቤት ከእርሱ ከቤቱ ነጋዲ ወጣ ይላል።
-
ምስሌሆሙ፣ከማሆሙ ሲወጡ:- አምላክ ተሰቅሎሙ ለፈያት ይላል ትርጉሙ እንደነርሱ ከእነርሱ ጋራ አምላክ ተሰቀለ ማለት ነው።
-
ኀቤሃ፣እስከኔሃ ሲወጡ:- ገብርኤል ተፈነዋ ለማርያም ይላል ትርጉሙ እስከ እርሷ ወደእርሷ ወደማርያም እስከ ማርያም ገብርኤል ተላከ ማለት ነው።
።
።
#ባዕድ #ቅጽል
አገባቡ ዝርዝሩ ለባለቤት አንቀጹ ለተሳቢ ሲሆን ባዕድ ቅጽል ይባላል። አንድና ብዙ፣ ሴትና ወንድ፣ ሩቅና ቅርብ ሳያናግር ያናገረ ይመስላል። አንቀጽን፣ ተሳቢን እና አገባብን ይዘረዝራል።
-
አንቀጽ ሲዘረዝር:-ማርያም እንተ አክበሩ ሥላሴ አበው ይላል ትርጉሙ ሥላሴ አባቶች ያከበሯት ማርያም ማለት ነው። ብእሲ ዘአክበረት ብእሲት ይላል ትርጉሙ ሴት ያከበረችው ሰው ማለት ነው። መላእክት እለፈጠርከ አንተ ወልድ ይላል ትርጉሙ አንተ ወልድ የፈጠርካቸው መላእክት ማለት ነው።
-
የተሳቢ ዝርዝር:- ማርያም ዘአክበሩ አበዊሃ ይላል ትርጉሙ አባቶቿ ያከበሯት ማርያም ማለት ነው። መላእክት እለ ፈጠርከ አንተ እግዚኦሙ ይላል ትርጉሙ አንተ ጌታቸው የፈጠርካቸው መላእክት ማለት ነው።
-
የአገባብ ዝርዝር:- አበው እለ ከብረት ማርያም ይላል።ትርጉሙ ማርያም የከበረችላቸው አባቶች ማለት ነው። መላእክት እንተ ተፈጥሩ ወልድ ይላል ትርጉሙ መላእክት የተፈጠሩለት ወልድ ማለት ነው። ብእሲ ዘተፈጥረት ብእሲት ይላል። ሴት የተፈጠረችለት ሰው (ወንድ) ማለት ነው።
።
እነዚህ በግልጸ ዘ ሲነገሩ ነው። ብቻ በሳድስ ቅጽል ሲነገሩ ደግሞ የሚከተለውን ይመስላሉ።
-
አንቀጽ ሲዘረዝር:-ማርያም ወይን ትክልተ ሥላሴ ገባእት ፈረየት ፍሬ ይላል ትርጉሙ ሥላሴ ምንደኞች የተከሏት/የተከላችኋት/የተከልናት ማርያም ወይን አፈራች ይላል።ወይም ሥላሴ ምንደኞች የተከሉሽ ማርያም ወይን አፈራሽ ይላል።ወይም ሥላሴ ምንደኞች የተከልንሽ ማርያም ወይን አፈራሽ ይላል። ሥላሴ ምንደኞች የተከሉኝ/የተከላችሁኝ ማርያም ወይን ፍሬን አፈራሁ ይላል።
-
አገባብ ሲዘረዝር:-ድንግል ንግሥት ወልድ ይላል።ትርጉሙ ወልድ የነገሠላት ድንግል/ ወልድ የነገሥኩላት ድንግል/ ወልድ የነገሠልሽ ድንግል/ ወልድ የነገሠልኝ ድንግል/ ወልድ የነገሥክልኝ ድንግል/ ወልድ የነገሥኩልሽ ድንግል/ ወልድ የነገሥክላት ድንግል ይላል።
-
ተሳቢ ሲዘረዝር:-ጴጥሮስ ምሁረ አርድእት ወንጌለ ይላል ትርጉሙ ተማሪዎቹ ወንጌልን የተማሩ ጴጥሮስ ይላል።
-
የተደራጊ አንቀጽ ከአድራጊ ከአስደራጊ ተናቦ በአድራጊ በአስደራጊ አመል ይፈታል። ለምሳሌ አምላክ ተሰቃሌ ይሁዳ ሲል ትርጉሙ ይሁዳ የሰቀለው አምላክ ይሆናል። አምላክ ተሰቃሌ ይሁዳ አይሁደ ሲል ይሁዳ አይሁድን ያሰቀለው አምላክ ተብሎ ይተረጎማል።
-
የአድራጊ አንቀጽ ከአስደራጊ ተናቦ በአስደራጊ አመል ይፈታል። አምላክ ሰቃሌ ይሁዳ አይሁደ ይላል ትርጉሙ ይሁዳ አይሁድን ያሰቀለው አምላክ ማለት ነው።
-
የተደራራጊ አንቀጽ ከአደራራጊ ተናቦ በአደራራጊ አመል ይፈታል ምሳሌ አምላክ ተሰቃሌ ይሁዳ ምስለ አይሁድ ይላል።ትርጉሙ ይሁዳ ከአይሁድ ጋር ያሰቃቀለው አምላክ ማለት ነው።
።
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።
4.5K views07:32