2022-09-24 15:37:13
--------የፈጣሪ ትእዛዝ ክፍል ፲------
ከአስሩ ትእዛዛት የመጨረሻው ሌላውን ሰው እንደ ራስ መውደድ ነው። ለራሳችን የምናስበውን መልካም ሐሳብ ለሌሎችም መመኘት፣ ለእኛ ሊደረግልን የምንፈልገውን ለሌላውም እንዲደረግ መፈለግና ማድረግ ናቸው። በእኛ ሊሆንብን የማንፈልገውን በሌላውም እንዳይሆን መመኘት ነው። ባልንጀራውን እንደራሱ የሚወድ ሰው በሰዎች ደስታ ይደሰታል በሰዎች ኀዘን ደግሞ ያዝናል። ለሁሉም ሰው መልካም አሳቢ ነው። የማንንም መጥፋት አይፈልግም። አንድ ሰው አጥፍቶ ቢገኝ እንኳ ለንሥሓ እንዲያበቃው ይመኛል እንጂ ጥላቻ የለበትም። ይህንን ሕግ የሚፈጽም ሰው ዘረኝነትን አያውቀውም። ሰው ዘረኛ የሚሆነው ባልንጀራውን እንደራሱ አለመውደድ ሲጀምር ነው። ኦርቶዶክሳዊው ሕይወት ግልጽና ውብ ነው። ሰው ከኦርቶዶክሳዊው ሕይወት እየራቀ ሲሄድ እየከፋ ይሄዳል። አንድ ሰው ጥሩ ነው የሚባለው ኦርቶዶክሳዊ ሲሆን ነው። ኦርቶዶክሳዊነት እውነትን ከጥበብ፣ ፍቅርን ከፍትሕ፣ ትሕትናን ከሙሉ ሰብእና ጋር አጣምሮ የያዘ ማንነት ነው። ኦርቶዶክሳዊው ሕይወት ራስ ወዳድነት የለበትም። አንዱ ለሁሉ ያስባል። ሁሉም ለአንዱ ያስባል። የኦርቶዶክሳዊነት ማዕከሉ ክርስቶስ ነው።
።
ዘሌ. ፲፱፣፲፰ "አትበቀልም፥ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ"።
።
አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይገባል።
968 views12:37