2022-05-30 12:19:24
መጎልመስ በጥሬ ቃል ፍቺው ማደግ፣ መሻሻል፣ ጥሩ ለውጥ ማምጣት ተብሎ ይተረጎማል፡፡ በሃይማኖት መጎልመስ በሃይማኖት ከመቆም ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡
በዲያቢሎስ ላይ ከነቃህ በኋላ ትዋጋው ዘንድ እንዲቻልህ በቀደመቺው መንገድ ላይ ትቆማለህ፡፡
በዚህ ጊዜ ውጊያው ሲጀመር፥ ውጊያው በባሕሪዩ ከግዝፈት ወደ ርቅቀት እየሄደ የሚጓዝ ስለሆነ ወደ ሃይማኖት ጥልቅ እውቀቶች እየገባህ ትመጣለህ፡፡ በሃይማኖት መጎሎመስ የምንለው ይሄን የመንፈሳዊ እይታ ማደግና መስፋት ነው፡፡
ክፉ መናፍስትን መዋጋት በሃይማኖት እንድንጎለምስ ያደርገናል፡፡ ከላይኛው አንቀጽ እንደተጻፈው የመጋደሉ ጦርነት ከግዝፈት ወደ ርቅቀት እየጠለቀ የሚሄድ በመሆኑ፤ ውጊያው በግዝፈት አካል ላይ በሚታዩት መንፈሳዊ ክንውኖች፥ ማለትም በስግደት፣ በጸሎት፣ በጾም፣.. በኩል አድርጎ ወደ በውስጥ አካል ላይ ወደሚታዩት መንፈሳዊ ፍሬያት እንደ ፍቅር፣ ትሕትና፣ ደግነት፣ ይቅር ባይነት፣ ለጋስነት፣.. ጋር በመድረስ፥ በቀዳሚነት በእግዚአብሔር ታስቦ ወደ ተፈጠረው ንጹሕ አዳማዊነት ስውነታችንን እያሳደገው ይመጣል፡፡
በቀደሙት ክፍሎች ላይ እንደተወሳው በክፉው መንፈስ ውስጥ ምንም አይነት የእግዚአብሔር ነገር ባለመኖሩ፥ ይህንን ተቃዋሚ የምንዋጋው በእግዚአብሔር ነገራት በመታገዝ ነው፡፡ የአምልኮተ እግዚአብሔር የዘወትር ልምምዶች ውጊያውን እንድንጀምር ሲያደርጉ፥ እየተዋጋን ስንቀጥል፥ በየዕለቱ በውጊያው ምክንያትነት የምናገኛቸው ትምህርቶች፣ ተጨባጭ ተሞክሮዎችና የተፈተኑ ልምዶች፥ ትናንት ከነበርንበት ሃይማኖታዊ ደረጃ ከፍ ብለን እንድንወጣ የሚያግዙ ለውጦች ይሆኑናል፡፡ በቀላል ምሳሌ፥ ትዕግስት ያልነበረን ታጋሽነትን ገንዘብ እንድናደርግ፣ ግዴለሽነት የተጠናወተን አስተዋይነትን እንድናከብር፣ ንዴት የሚፈታተነን እርጋታን እንድንማር፣ ተስፋ መቁረጥ የከበበን ተስፋ እንዲሰማን ውጊያው በራሱ ያስተምረናል፡፡
ጳውሎስ ጎልምሱ ብሎ አላበቃም፡፡ ጠንክሩ ሲል ደግሞ ሦስተኛውን ቃል ጽፎአል፡፡ ርእሳችን መናፍስትን መዋጋት እንዴት ለሃይማኖታችን ይጠቅመናል የሚል ነውና፤ የሐዋሪያውን መልእክት ለጀመርነው ርእሳችን ማስተንተንኛ አድርገን እንቀጥል፡፡
ዲያቢሎስን መዋጋት በሃይማኖት እንድንቆምና እንድንጎለምስ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት እንድንጠነክርም ያደርጋል፡፡
ክፉ መንፈስ ክፋቱን ወደ ሰው ልጆች ለማጋራት ሲንቀሳቀስ ዕረፍትን አያርፋትም፡፡ እየተሸነፈም እያሸነፈም ግብሩን ለመፈጸም እንቅልፍ የሌለው ባላንጣ ነው፡፡ ተንኮል ከማሰብ አይደክምም፣ ሐሰትን ከመናገር አይሰለችም፣ ጥፋትን ከማድረስ አይቆጠብምም፣ ችግርን ከመፍጠር አይለዝብም፡፡ የሚመጠሉትን አጋጣሚዎች በሚገባ ለሚፈልገው ዓላማና ውጤት ለማድረስ ጥቁር ልቦናው አይዘናጋም ነው፡፡ ሰይጣን ሥራ ፈትቶ አያውቅም!
ስለዚህ፥
ይሄን በክፋት ለክፋት የጸና ጠላት ለመጣል በጽድቅ ለጽድቅ መጽናት ደግሞ የምእመናን ፋንታ ነው፡፡ እያንዳንዷን ሰኮንድ ለተልዕኮው ማስፈጸሚያነት የሚጠቀምባት ዲያቢሎስ በሰፊ ርቀት አልፎ በመቅደም ፍላጎቱን እንዳያሳካብን፥ በእያንዳንዱ ዘወትራችን ላይ መንፈሳዊ ልካችንን ጠብቀንና አስጠብቀን መሄድ አማራጭ የሌለው ግዴታችን ነው፡፡
ትናንት የሰገድከው ስግደት ዛሬም መቀጠል አለበት፡፡ ዛሬ ያሳየኸው መልካምነት ነገም ሊገለጥ ይገባዋል፡፡ ነገ ያቀድከው የመቀደስ ቀን ከዚያም በኋላ ሊለይህ አይገባም፡፡ ጠዋት የበላነው ቁርስ የማታ ራት እንደማይሆነን፥ ክርስትናም አሁናዊ መዳንን ትልቁ ጉዳዩ አድርጎ በመንቀሳቀሱ፥ በአሁኖቻችን ላይ ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ ነገሮች ሁሉ አሁኑኑ እንድናደርግ ጥብቅ ማሳሰቢያ ያስተላልፋል፡፡ አሁኖችን ሁሉ በአሁንነታቸው አክብሮ አሁን መደረግ የሚገባውን እንድናደርግ የሚያደርገው ደግሞ፥ አሁንም ድረስ ቀጥሎ ያለው የዲያብሎስ ፈተና ነው፡፡
መናፍስት ሃይማኖትን ጠንክረው መታገላቸው በሃይማኖታችን እንድንጠነክር ያግዘናል፡፡ የማይቋረጥ አሳችነታቸው የማይተኛ ጥንቅቁነት እንዲኖረን ያበረታናል፡፡ ትናንት የጀመሩትን ሴራ ዛሬም መሸረባቸው፥ ትናንት የተጀመረው ስግደት እንዳይቋረጥ ያስገድደናል፡፡ ቅድም የተጠነሰሱት ተንኮል በኋላም መቀጠሉ፥ ዓለምን በማይሟጠጡ ትዕግስቶች እንድንታገሳት ያስተምረናል፡፡ በእውነትም መናፍስትን መዋጋት በሃይማኖት ያሳድገናል፡፡ ርእሳችንን በይሁዳ ምክር እንዝጋው፦
"ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።"
(ይሁ. 1፥3)
ይቀጥላል
ተሞክሮ መላካችሁን ቀጥሉ ☞ @bemaledaa_neku_bot
9.1K viewsedited 09:19