2022-09-06 16:49:10
እነሆ ከማርቆስ ቤት ደጃፍ ቆመናል፡፡
ከትንሣኤው ቀጥሎ ዕርገቱ ይመጣል፡፡ በዕረገቱ ከአባት ዘንድ እንደወረደው መልሶ ወደ አባቱ ይወጣል፡፡ ከአብ ቀኝ ሆኖም ዝም አይልም፡፡ ሁሉን የሚያውቅ ሁሉን የሚገለጥ አጽናኝ ይልክልናል፡፡
(ዮሐ.16፥7) እስከዛም ድረስ በሰላም ቤት ቆዩ ሲል አሳስቦን ነበረ፡፡
(ሉቃ. 24፥49) እነሆ በሰላም ውስጥ ነን /ሰላም ለእናንተ ይሁን/፡፡
ሰው ቤተ መቅደስ ነው፡፡
(1ኛ ቆሮ. ምዕ 3) ቤተ መቅደስም ሲሆን ከመቅደሱ ያለ ቅድስት አለው ማለት ነው፡፡
(ሕዝ. ምዕ 41) ወደዚህ ወደ ራሱ ቅድስት የደረሰ በዋናው ቅዱስ ይሳብ ዘንድ አለው፡፡
(1ኛ ጴጥ. 1፥15) በአንቀጸ መጽሐፍ አገላለጥ፡ በበዓለ ኀምሳ በ120ው ቤተሰብ ላይ ከወረደው ወይን ጠጅ ለመጠጣት መንፈሳዊ ማንነት ያስፈልጋል፡፡
(ሐዋ. ምዕ 2) ማንነቱ በእምነት ያለ እውነት፥ በእውነትም የሚገለጽ ቅንነት ነው፡፡ ራእየ ዮሐንስ፡ ይህንን ማንነት ሊውጥ አፉን ከፍቶ ስለሚመጣ ቀይ ዘንዶ የሚለን ይኖራል፦
"ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ..ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ፡፡ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ..በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ..ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።"
ወንዱ ልጅ ወደ እግዚአብሔር ሲነጠቅ በአንጻሩ ዘንዶው እስከ ወዳጆቹ ወደ ታች ተጥሏል፡፡ የተጣለውም ወደ ምድር ነው፤ ወደ ሥጋ!
እንግዲህ በሥጋ ለሥጋ ብቻ የሚኖሩት የወጡ ሲመስል እየወረዱ ናቸው፡፡ ቁልቁለቱን ተያይዘውታል፡፡ የሰማዩ እውነት ሽቅብ በወጣበት ልክ እነርሱም ወደ ሐሰታቸው ጥግ "እየወጡ" ነው፡፡ ነገሩ፡ ክፋትም በመጨረሻ ብቃቱ ወደ መገለጽ ይሄዳል እንደማለት ነው፡፡ ተፈቅዶለታልና ተዉት፤ ክፉ የሚችለውን ያህል ይክፋ
(ራእ. 22፥11)፤ ..
ወሳኙ ይሄ ነውና እንድገመው፡፡ ሰውነት ቤተመቅደስነት ነው፡፡ የዚህ ቤተመቅደስ ውጪያዊ ቅጥር ሥጋ ነው፡፡ መድሀኒቱ የሚታየውን ቤተ መቅደስ (ከሥጋ የተወለደውን ሥጋ) አፍርሱት ስለማለቱ ወንጌል ያስታውሰናል፡፡
(ዮሐ. 2፥19) በሥጋ ዕውቀትና ሕግ ወደ ረቂቁ አማናዊ ሥርዓት አይደረስም፡፡ ምክንያቱም ከላይ የተጠቀሰው ዘንዶ በልጅነቱ እባብ ሳለ ነድፎ የመረዘው የሥጋን ፈቃድ ነው፡፡
(ሮሜ. 7፥18) ይሄ ፈቃድ ካስገኘው ፈቃድ ወጥቶ ከሚያጠፋው ጋር በመተባበር፥ ከውስጠኛው ቅጥር ያለቺውን የአምላክ እፍታ ሸፍኗል፡፡ ስለዚህ መጋረጃነቱ ሊገፈፍ (ሊፈርስ) ይገባዋል፡፡
(ቆላ. 2፥11) ይሄም መገለጥ በመስቀል ተከናወነ፡፡ እነሆ ነፍስም
"አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ" በሚል የኛን ባሕርይ በለበሰ ታላቅ ጸሎት ነጻ ወጣች፡፡
(ሉቃ. 23፥46) አሜንታዎች ሆይ፥ በሉ ስለዚህች ታላቅ ጸሎት እጅ ንሡ!
እናንተ፡ ጸሎቲቱን አሜን የምትሏት አማኞች ስትኖሩ፡ ደግሞም ውጪያዊ ቅጥራችሁን ታፈርሱም ዘንድ እንግዲያስ ያስፈልጋችኋል፡፡ አፍርሱና የነፍስን አርነት አውጁ፡፡ ለዚህ ዓለም ሥጋዊ ሥርዓት ምውታን ሁኑ፡፡ የዘንዶው ትልቁ መናገሻ የሥጋ ጉድለት (ድክመት) ነው፡፡ ለሚታየው መሞት እንደሚወራው ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ለዚህም ነው መድኃኒቱ "ባለሸክሞች ሆይ፥ እስቲ ወደ እኔ ኑ" የሚለን፡፡ በእርሱ ከተሆነ እንደርሱው መሞት ይቻላል፡፡ የሞቱም ቁልፍ የተዘጉ ማኅተሞችን ተራ በተራ ይከፍታል፡፡ ሞቱን በሚመስል ሞት እየሞትን የምንፈታው፣ የምንተረትረው የየራሳችን ጥቅል ተቀምጦልናል፡፡ ጥቅሎቹንም ፈትቶ የማንበቡ ሂደት ወደ ውስጠኛው ቅጥር እያስገባ ከመቅደሱ አስኳል ያደርሳል፡፡ ውስጠኛይቱ ቅጥር ነፍስ ናት፡፡ ነፍስም ከሰማይ የሆነች ሰማያዊ ናት፡፡ ስለ ሰማይ ደግሞ ከላይ ያጣቀስነው የራእዩ መጽሐፍ እንደገና እንዲህ ይላል፦
"ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።"
ክፉው ብቻ ሳይሆን፡ እኛም ትንሽ እንደቀረ አውቀን ጠብቁ ካለው ቦታ ደስ ይበላችሁን ይዘን በደስታ ቆመናል፡፡ ስሙ በቃላችን ከፍ ከፍ ላለለት እርሱ በእውነትና በመንፈስ ሰግደናል፡፡
(ሉቃ. 24፥52) መጠበቂያ ቦታውም ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረውን የሕይወት ቃል ጸንቶ መጠበቅ (መታዘዝ) ነው፡፡ ብንወደውስ የሚለውን ሰምተናል፡፡ እንደሰማን ሊያሳየን ትእዛዙ ተቀጥሮአል፤ አሁን እዚያ ነን፤ በማርቆስ ቤት ነን፤ በኢትዮጵያ!
@bemaleda_neku
2.0K viewsedited 13:49