2022-11-20 14:55:36
በእንተ ብፁዓን !ክርስትና እንደ ክርስቶስ የመኖር ሕይወት ነው:: የእግዚአብሔር ልጅ ራሱን በሰው ልጅነት በለካበት መሥፈሪያ ሰውነትን መለካት የሐዲስ ኪዳን ክርስትና በቁዔት ነው::
በእውነት ለምናምን፥ አድራሻችን፣ ጥጋችን፣ ፍጻሜያችን ሁሉ ክርስቶስን በመምሰል እርሱን በጸጋ መዋሐድ ነው:: አድራሻችን፣ ጥጋችን ካልን፥ ቃላቱ አንዳች ሊያሳዩ የፈሉት ጉዞ ወይንም ሂደት አለ ማለት ነው:: ይህንን ጉዞ የምንጓዘው ደግሞ በተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሆን እርሱን እንድንመስለው ሲል እኛን የመሰለው ጌታ
"እኔ መንገድ ነኝ" አለ::
(ዮሐ. ፲፬፥፮) የዚህ መንገድ የመጀመሪያ ተጓዦች ሐዋሪያት ነበሩ:: እነርሱም የወጠቡት የወረዱበት፣ የወደቁበት የተነሡበት፣ እንደ በጎች በተኩላ መካከል የተሰማሩበት ይህን መንገድ ከእኛ በኋላ የምትነሡም ክርስቲያኖች ሂዱበት ሲሉ
"እኔ ክርስቶስን እንደምመስል [እናንተም]
እኔን ምሰሉ" በማለት በኑሮአቸው ገልጠው አስተማሩ::
(1ኛ ቆሮ. ፲፩፥፩) እንግዲህ አንድ ስለ ክርስትናው ነገር በእውነት ያለ ሐሰት የሚያስብና ዋጋውንም በሕይወት ማክበር የሚፈልግ አማኝ፥ ይህንን ክርስቶስ የመሠረተውን፣ መሥርቶም የተጓዘውን፣ ተጉዞም እሱ በሄደበት ሌሎችን ያስከተለውን መንገድ እንዴት ላገኘው እችላለው? ሲል ሊጠይቅ ይገባዋል:: ጥያቄውንም አሰምቶ በተናገረ ጊዜ መልስ የምትሆን ቃል እንዲህ ትለዋለች፦ 'ወንጌልን አንብብ፥ ከወንጌልም ማቴዎስን፥ ከማቴዎስም፥ የተራራውን ስብከት - አንቀጸ ብፁዓንን!'
አንቀጸ ብፁዓን እንደ ክርስቶስ የምንኖርበት፥ በምድር የምንራመደው ሰማያዊ ፍኖት ነው:: በሐዲስ ኪዳን የተጻፉ ወንጌላትና መልእክታት ማዕከላዊ ርእሶች፥ በዚህ፥ ክርስቶስ ተራራ ላይ ወጥቶ ደቀመዛሙርቱንና ሕዝቡን ባስተማረው ትምህርት ዙሪያ ያጠነጥናሉ:: የዚህም ምክንያት፥ እነዚህ የተመሰገኑ ቃሎች ትምህርቶች ብቻ ሳይሆኑ ሕግጋትም በመሆናቸው ጭምር ነው:: የሃይማኖት ጠቢባን የኦሪት ሕግ በ(ሲና)ተራራ እንደተሠራች፥ ሐዲሷም ሕግ በተራራ ተመሠረተች ይላሉ:: ስለዚህ አንቀጸ ብፁዓን ክርስትናን የምንከተልበት ጎዳና ብቻ ሳይሆን
ክርስትናን የሚያኖረን ትእዛዝም ነው ማለት ነው::
ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን ያስተማረው
ራሱን ነው:: እርሱ የሚናገራቸው ንጹሕና በጎ ቃላት መንፈስም ሕይወትም ናቸው::
(ዮሐ. ፮፥፷፫) እንደ ሕይወትነታቸው አንድም እርሱ የኖረውን ሕይወት እንድንኖር ያሳስባሉ:: ለምሳሌ፥
"በመንፈስ ድሆች የሆኑ (ትሑታን)
ብፁዓን ናቸው" ሲል የተራራው ስብከት ይጀምራል:: የትሕትና ጠባይ፣ ልክና መሠረት ደ'ሞ ሌላ ማንም ሳይሆን ክርስቶስ ነው (እኔ በልቤ ትሑት ነኝና ማለቱን ያስታውሷል
(ማቴ. ፲፩፥፳፱)):: እንደገና ዝቅ ብለን ብናነብ
"የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና" ሲል እናገኛለን:: እንግዲያስ ነፍስና ሥጋን፣ ሰውና እግዚአብሔርን፣ መላእክትና ሰውን፣.. ያስማማው የእግዚአብሔር [የባሕርይ] ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንቀጥል ብለን
"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው" የሚለው ጋር ብንደርስም እንዲሁ የምናገኘው መድኃኒታችንን ነው:: ገና ከልደቱ ስፍራ ከቤተልሔም ጀምሮ ማረፊያ አጥቶ ሲሰደድ ኖሯልና::
እንኪያስ ክርስቶስን መኖር የፈለገ ሰው አንቀጸ ብፁዓንን መኖር ይገባዋል::
(፩ኛ ዮሐ. ፪፥፮) እርሱ እንደኖረው ሳይኖሩ ክርስቲያን (እንደ ክርስቶስ) ነኝ ማለት ሐሰት ይሆንብናል::
"ማንም በኋላዬ ሊከተለኝ የሚወድ መስቀሉን ተሸክሞ ዘወትር ይከተለኝ" በማለት ክርስቶስ ክርስትናን ሲሰብካት እኮ፥ መስቀሉን (መከራውን) ያሸከመን አንገታችን ላይ በምናኖረው ማኅተብ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ በምንኖረው፥
"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ (መከራን የሚታገሡ)
ብፁዓን ናቸው" ባለው ቃል ጭምር ነው:: እንደዚህ ያሉትን የጌታን ቃላት ሳይሸከሙ፥ ጌታን መከተል አይቻልም:: መስቀል በአንገት የሚያጠልቁት ከልብ ግን የሚያወጡት ምልክት አይደለም:: እንዲህማ ከሆነ፥ የዳዊትን መጽሐፍ ይዘው ዳዊትን ከማያውቁት አይሁዳውያን በምን ተሻልን?
ክርስቶስን የምንወድ ልቦናዎች እንስማ:: ቃሉን ሳይኖሩ ክርስትናን መኖር አይቻልም:: እርሱም
"የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል" ያለው ይህንን ነው::
(ዮሐ. ፲፬፥፳፫) አንቀጸ ብፁዓንን ትቶ ክርስቶስን አለመተው አይቻልም:: እውነትስ የዋህ ሳይሆኑ ክርስቲያን የሚሆኑት እንደምን ባለ ጥበብ ነው?
አንቀጸ ብፁዓንን ስናነብ ክርስቶስን እንደምናነብ፥ ክርስቶስን ስናነብ ሰውነትን እንደምናነብ፥ ሰውነትን ስናነብ ሁላችን ልንሆን የሚገባውን እንደምናነብ እናስተውል:: አንቀጸ ብፁዓን አንድ የሃይማኖት ተቋምን የተመለከተ ጉዳይ ሳይሆን ከሁሉ የሚቀድመውን ሰውነትን የተመለከተ ጉዳይ መሆኑን የምናውቀው፥ ትምህርቶቹ በአንድም በሌላም መንገድ የሚያምኑም ሆነ የማያምኑ ሰዎችን ቀልብ ሲገዙና ክርስቶስን የሚቃወሙ ርእዮቶች ጭምር ሲስማሙባቸው መገኘቱ ነው:: "ሰው" የሆነ ሰው ሁሉ አንቀጸ ብፁዓንን ሊገፋት አይችልም:: ቢያንስ በብያኔ ደረጃ ትሕትናን የሚጠላት፣ ምሕረትን የሚነቅፋት፣ ንጽሕናን የሚቃወማት፣.. አይገኝም::
ስለዚህ አንቀጸ ብፁዓን፥ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ለሰውነት የሚያበቃ የስብዕና ትምህርት ነው:: እንዲህ ባለ አረዳድ ብንረዳው፥ እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ ዓለምን ለመጠቅለል የወደደበትን ሚሥጢር እንረዳዋለን:: ይሄን ባንረዳ እንኳ ሌላው ቢቀር እንደተፈጠርንበት ተፈጥሮ ሰው ሆኖ የመኖር ዕድሉን እናገኛዋለን::
ሌላው ከመንፈሳዊው ውጊያ አንጻር አንቀጸ ብፁዓን ያለው አገልግሎት ነው:: ለብዙ ሰዎች የመንፈሳዊው ፍልሚያ ጦር ዕቃ የሚመስላቸው መንፈሳዊ ልምምድ (ስግደት፣ ጸሎት፣ ጾም፣.. ) ብቻ ነው:: በዚህም አስተሳሰብ የተነሣ የነዚህ ሰዎች የፍለጋ ዝንባሌ የሚያተኩረው ልምምዶቹ ላይ ሆኖ ይወሰናል:: ይሄ መወሰንም፥ ዞሮ ከተነሡበት የሚያደርስ፣ ሃይማኖታዊ ጉልምስናን የሚያቀጭጭና ጊዜ እየሰነበተ ሲሄድም ወደ መሰላቸት የሚያመራ ይሆናል::
መንፈሳዊ ልምምዶች መነሻዎች እንጂ ውጤቶች አይደሉም:: ይኸውም መጽሐፍ
"ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ" በማለቱ ታውቆአል::
(ማቴ. ፫፥፰) መንፈሳዊ ልምምዶች አንድ ዘር ተዘርቶ እንዲበቅል ውኃ በማጠጣት፣ ተገቢ ብርሃን በመለገስ፣ ከአረም በመጠበቅና አስፈላጊ ማዕድናት በመስጠት የሚጠበቀው ፍሬ እንዲገኝ እንደምንሠራው ያሉ ሥራዎች ናቸው እንጂ
በራሳቸው ፍሬዎች አይደሉም:: ማለትም የሚጸልይ ሰው በመጸለዩ ምክንያት የመጣው ለውጥ መታየት ይኖርበታል:: የሚሰግድም እንዲሁ ከማይሰግደው የሚለይበት መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል:: አለዚያማ እንግዲያ በመጾምና በመራብ መካከል ያለው ልዩነት ምን ሊሆን ነው?
በመንፈሳዊ ልምምዶች መናፍስትን መዋጋት አንቀጸ ብፁዓንን እንድንኖር ማስተዋል የሚከፍትልን ሂደት እንጂ መደምደሚያ አይደለም:: በሌላ አገላለጥ
በመንፈሳዊ ልምምዶች ላይ ተገኝቶ ከአንቀጸ ብፁዓን የጠፋ ምእመን፥ በረጅሙ የታሰረ የዲያብሎስ ምርኮኛ መሆን አይቀርለትም:: እውነትም ከጌታ ፊት ራሱን ሊያዋርድ ስለ አምልኮት የሚሰግድ ጉልበት፥ በሕይወቱ ገጠመኞች ውስጥ የተከበረችውን ውርደት (ትሕትና) የማይገልጣት ሲሆን፥ ትሕትናን የሚያሳድዳት ክፉውን ኃይል እንዴት አድርጎ ያሸንፈዋል?
2.1K views11:55