Get Mystery Box with random crypto!

በማለዳ ንቁ !

የቴሌግራም ቻናል አርማ bemaleda_neku — በማለዳ ንቁ !
የቴሌግራም ቻናል አርማ bemaleda_neku — በማለዳ ንቁ !
የሰርጥ አድራሻ: @bemaleda_neku
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 18.24K
የሰርጥ መግለጫ

(2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕ. 13)
----------
11፤ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።
14፤ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን፡፡
@bemaledaa_neku_bot

Ratings & Reviews

2.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

2

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 4

2022-08-27 11:57:25 መልእክት ለመንፈሳዊው ውጊያ ተማሪዎችና መምህራን

"ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ። በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን፡፡" (፩ኛ ቆሮ. ፲፮፡፲፫-፲፬)

ሐዋሪያ ጳውሎስ ከጻፋቸው የተወደዱ ቃላት መካከል በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው: ብዙ መልእክታትን በሁለት ዓ.ነገሮች የገለጸው የመጽሐፍ ጥቅስ ይገኝበታል:: ከማስተዋል ጋር ስናነብ: የመጀመሪያው ዓ.ነገር ውስጥ ያሉት ቃላት በሦስት የቅደም ተከተል ደረጃ (ሂደትም ቢሉ) ተከትበው እናያቸዋለን:: አስቀድሞ ንቁ አለ፥ በሃይማኖት ቁሙ ሲልም ቀጠለ፥ ሲደመድም ጎልምሱ ጠንክሩ ብሎ ጨረሰ:: ይሄ አጻጻፍ የራሱ ምክንያትና ግብን ይዞአል:: ይኸውም ለጥቆ ለሚነሣው ጭብጥ ሐሳብ ማስተንተኛ ሲሆን ያገለግለናል:: እስቲ ወደ ፍሬ ነገሩ እንሂድ::

አገልግሎታቸውን በትውልድ ልብ ውስጥ እግዚአብሔር አምላክ ያትምላቸውና መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ ከ፴ ዓመታት በላይ በዘለቀ መንፈሳዊ ትምእርታቸው: ሐዋሪያ መልእክቱን በጀመረበት በ"ንቁ" ኃይለ ቃል ሰማያዊ ሚናን በመውሰድ: ለበርካቶች ከሥጋ ሕዋስና ዕውቀት ተሰውረው ሰውነትን ስለሚያጠፉት ክፉ መናፍስት ንቃተ ግንዛቤ እንዲኖረን አድርገዋል:: ማንኛውም ቅን አስተሳሰብ ያለው ሁሉ የማይክደው ውጤታማነታቸውን መዘርዘር ድካም ነው ትርፉ:: እንደው አንዱን ብቻ ለኔ በግል የሚያስደስተኝን ብጠቅስ: በአሁኑ ትውልድ ካሉ በኑሮ የተገለጸ የትሕርምት ሕይወት ካላቸው ወጣቶች መካከል አብዛኛው የኚህ መምህር ተማሪዎች ናቸው:: ይሄ ታላቅ ነው፤ የአሁኑ ሳይሆን ቀጣዩ ትውልድ የሚያመሰግነው ክቡር ሥራ ነው::

የኚህ መምህር የማስተማር ዋነኛ ተልዕኮ ወይንም ድርሻ "ንቁ" የሚለውን ወሳኝ ደውል መደወል ነው:: መንቃትም በዕውቀት ነው:: ዝነኛይቱ የሆሴዕ ትንቢት ስትል እንደምትናገረው ባለማወቅ ምክንያትነት ሕዝብ ይጠፋልና: ካለማወቃችን ጀርባ ተደብቀው የነፍስም የሥጋም ጉዳት የሚያስከትሉት ክፉ መናፍስትና ዓለምን የሚመሩበት ሥርዓታቸው ሕዝብን በሁለገብ አቅጣጫ እያጠፉ አዝማናትን አሳልፈዋል:: በመሆኑ የክፉዎቹ: ምግባራዊ ግንኙነት ባለው ዕውቀት አለመታወቅ ከፍተኛ ጥፋትን እያደረሰ እንዳለ የተረዱት አገልጋይ "ንቁ" እያሉ: የአጥፊዎቹን ማንነት፣ የጥፋት ስልትና ጥበብ ይፋ እየገለጡ አስተምረውናል:: እንደ አንድ ግለሰብ አቅም እና ከስልሳዎቹ አብዮታዊ ዘመን በኋላ እንዳለው: መንፈሳዊውን ዓለም ክዶ ወደ ዓመፃ እንደሄደው ትውልድ ብዛት: የመምህሩ ድርሻ ንቁ የሚለውን መልእክት እያስደመጡ ምእመናን በሃይማኖት እንዲቆሙ እስከማትጋት የሚሄድ ነው::

በሃይማኖት ለመቆም: በመናፍስቱ ላይና መናፍስቱ በሚመሩት በዚህ ሥጋዊ ዓለም ላይ በቂ የዕውቀት ንቃት ያስፈልጋል:: በቀላል ምሳሌ: በእንቅልፍ ድንግዝግዝታ ውስጥ ያለ ሰው ሳይወድቅ ሊቆም አይችልም:: ያልተገለጠ ዓይኑ ይጥለዋልና:: እንዲሁ በሃይማኖት ጎዳና ላይ ወደፊት ለመጓዝ ዕንቅፋቶችን፣ ገደሎችን፣ አሳሳች አቅጣጫዎችንና መሰል እርምጃ የሚከለክሉ ተግዳሮቶችን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የዕውቀት ብርሃን ያስፈልጋል:: ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ጊዜ እንዲኖራቸው እየተመኙ ነገር ግን የማያገኙበት ምክንያት: በሕይወታቸው ውስጥ ሰርገው ገብተው ስለሚዋጓቸው መንፈሳዊ ጠላቶቻቸው ያላቸው ዕውቀት እጅግ ደካማ ከመሆኑ የተነሣ ነው:: ለብዙዎች የዲያብሎስ መንፈስ ማለት ወይ ከነአካቴው የተረሳ፣ ወይ ምናባዊ የሆነ ሩቅ ጠላት፣ ወይ ትንሽ የሃይማኖት ትምእርት ላገኙት እንደ ወፍ ከላይ ከላይ እየበረረ አንዳች ጥቃት ጣል አድርጎ የሚዞር ውጪያዊ ጠላት ተደርጎ ነው የሚታሰበው:: እንጂ በሰው ባሕርይ ውስጥ ዘልቆ ጠልቆ በመግባት አእምሮና (ዕውቀት) ልቡናን (መንፈሳዊነት) ተቆጣጥሮ ሁለንተናዊ ማንነትን በመምራት ዓይነተ ብዙ ጥፋቶችን በእግዚአብሔር እውነት ላይ እንደሚያስፈጽም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ገና የተገለጠ አይደለም:: በዚህ ምክንያት ሃይማኖት በዚህ ዘመን ዘወትራዊ ሕይወትነቱ ቀርቶ የሚለበስ የሚወለቅ የክብረ በዓላት ጌጥ ለመሆን ተገደዶአል:: አሊያም እንደ ድርጅት በአንድ ተቋም ውስጥ አባልነትን የመግለጫ የቡድን መለያና መሟገቻ ሊሆን ተበይኖበታል:: እንዳልነው: ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈው ክታብ የሚያውጀው መንፈሳዊ ውጊያ ላይ ንቃት ከሌለ በሃይማኖት ለመቆም የሚቻል አይደለም:: (ኤፌ. ፮፡፲፪)

ነቅቶ በሃይማኖት ከመቆም አስከትሎ ጎልምሱ ጠንክሩ የሚለው የሚመጣ ይሆናል:: መልአከ መንክራት ከአንደበታቸው የማትጠፋው "በርቱ" የሚሏት ማሳሰቢያ ነች ጎልምሱ ጠንክሩ ማለት:: ስደግመው የኚህ አገልጋይ ኃላፊነት ሕዝብን በማንቃት በሃይማኖት ውስጥ እስከማኖር የሚረዝም ነው:: በተሰጠው ትምእርት ላይ መሠረት ሆኖ ራስንም ሆነ ሌሎችን የማጎልመስና የማጠንክሩ ድርሻ ከመምህሩ ለተማሩ መምህራንና ተማሪዎቻቸው የተወወ ክፍት ቦታ ነው::

ነገር ግን ይሄ በአብዛኛው ሲሆን አይታይም:: ንቁ የምትለዋ ዐዋጅ ጥሪዋ የሚሰማው ብዙ ጊዜ የሥጋ ችግር ለገጠማቸው ሰዎች በመሆኑ ትምእርቱን መከራ እንደመገላጊያ ወስዶ ስለ ውጪያዊ ፈውስ የሚዳክሩ ምእመናን እንዲበራከቱ ሆኖዋል:: የትሕርምቱ ሕይወት (አንድም የመጋደሉ አንድም የመንፈሳዊ ልምምዱ) በራሱ መድረሻ ሳይሆን ክርስቶስን በመምሰል ጉዞ ወደ ሱታፌ አምላክ (አማልክት ዘበጸጋ) የሚደረስበት የሂደት አካል ወይንም መንገድ ነበረ:: ሰዎች እንዲነቁና በሃይማኖት እንዲቆሙ የሚታወጀው: ስብዕና ክርስቶስን እየለበሱ ብሉይ ዓለምን በመጀመሪያ ከውስጣቸው ሲቀጥል በዙሪያቸው እያፈረሱ ድል እንዲነሱ ሲባል ነው:: እንጂ መናፍስት የሚያመጡትን ፈተና አስቁመው በዚህ ዓለም ላይ ተደላድለው እንዲያርፉ አይደለም::

ይሄ በእንዲህ ሳለ: እንደ ትንሹ ልጅ ታሪክ የዚህ ዘመን ሰው ያለውን ካላጣ፣ ካልተቸገረ፣ ካልታመመ፣.. ወደ እግዚአብሔር አይመጣምና ከላይ እንደተገለጸው የመምህርን ንቁ ትምህርቶች ብዙው ሰው መከታተል የጀመረው ችግር አስቸግሮት ነው:: (ሉቃ. ፲፭:፲፩-፳፩) አንዳንዶቻችንም መንፈሳዊ ሕይወትን ሳንፈልገው ነገሩ የጨነቀው ሆኖብን ነው በትሕርምቱ ሕይወት ያለነው:: በዚህ ነገር ምክንያት ትምእርቱ (የንቁ ዐዋጁ) ከነፍስ ይልቅ የሥጋ ትርፍን ስለተመለከቱ ርእሶች የሚባትቱ: የሥጋ ጉዳይ ያሳመማቸው ሕሙማን ለፈውስ ሲሉ የሚንከራተቱበት ጉባዔ ወደመሆን ሲያዘንብል ይስተዋላል::

ሐዋሪያት ከመጀመሪያው በተጠሩበት ጥሪ በኩል ብናየው: የሥጋ ፈውስ ማለት የጎደለውን: የዓሣ አስጋሪዎቹን የነ ስምዖንን መረብ የመሙላት ጉዳይ ነው:: (ሉቃ. ፭፡፫-፲፩) ከታሪኩ ላይ ልብ ስናደርግ: ጌታ ከገሊላውያኑ አጥማጆች አጠገብ መጥቶ ሲያስተምር ደቀመዛሙርቱ ለሊቱን ሙሉ አልያዝ ባላቸው በዓሣ ጉዳይ አሳባቸው ባሕሩ ውስጥ ሰጥሞ ቃሉን አልሰሙትም ነበር:: ልክ አሁን አማኞች በዓለም አሳብ ተገርኝተው ተጨልጠው ጠፍተው መንፈሳዊውን እውነት ከነአካቴው እንደተዉት ማለት ነው:: ታዲያ ጌታ መጥቶ የጎደላቸውን ዓሣ ከሞላላቸው በኋላ: እርሱን አስቀድመው ካዩበት ዓይን በተለየ አስተውለው አዩት:: እንደ ስምዖን ጴጥሮስ ያሉትም ኃጢአታቸውን ተመልክተው ተንበርክከው ተናዘዙ:: በስተመጨረሻም ወንጌሉ እንደሚለው "በስተኋላዬ ኑ: እንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምዱ ትሆናላችሁ" ሲላቸው: ሁሉን ትተው ተከተሉት! ይሄ እንደምን ልብን ይሰረስራል?.. ምን ብለው ተከተሉት?.. "ሁ-ሉ-ን ትተው" ተከተሉት!
4.0K views08:57
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-27 11:57:13
"ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ። በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን፡፡" (፩ኛ ቆሮ. ፲፮፡፲፫-፲፬)
3.7K viewsedited  08:57
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-22 16:20:12 ከፊት ቀድመሽ እውነቶቼን የመራሽ፣ ከኋላ ተከትለሽ መንገዳገዴን የደገፍሽ፣ ከቀኜ ቆመሽ ሞገሴን የሆንሽ፣ ከግራዬም ሆነሽ ስሕተቶቼን ያረምሽ፣ ከሥሬ ተገኝተሽ መሠረቴን የሠራሽ፣ ከበላዬ ሳለሽ መዓልት ለሊቴን ያበራሽ የበጎ ብቃቶቼ ሁለንተና ሆይ፥ ..ብዙ ስለማትናገሪው አንቺ ብዙ ልናገር ያቅተኛል:: ለወትሮ የማዳውራቸው ቃላቴ አንድስ ዓረፍተ ነገር እንኳ ስላንቺ መመሥረት ይሳናቸዋል:: ..አቤቱ!.. ባንቺ ትሕትና ስንቱን ትዕቢት አሳለፍኩት? ባንቺ ዝምታ ስንቱን ጩኸት አሰታገስኩት? ባንቺ ወገግታ ስንቱን ጽልመት ገፈፍኩት?.. ከሆነልኝ እኮ ያላንቺ የሆነልኝ አንዳቹም የለም:: ..፤ መቼም ኖሮሽ ለማያውቅሽ፤ ይሄ ከንባብ የዘለለ ኑሮ አይሆነውም:: ነገርን በልብ መያዝ ያስተማርሺኝ አንቺ የነፍስ ፈገግታዬ ግን፥ ያሳለፍኩትን ሁሉ ያሳለፍሺልኝ ስትሆኝ፥ የሚታዩት የፊደል ቅንጣቶች ሁላቸው የተኖሩ/የሚኖሩ የሕይወት ሰዓቶች እንደሆኑ ታውቂያለሽ:: ..የአባቶች መሐላቸው አንቺ ሆይ፥ ..እነሆ በተቀደሱት አንደበትና አንቀጽ ምስጋናሽ ይሁንልኝ!
8.2K viewsedited  13:20
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-14 13:57:31 አንድ እርምጃ ወደ ሦስት አቅጣጫ

ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወተ ሥጋ የተመላለሰባቸው እርምጃዎቹ በሦስት አቅጣጫ ይጓዙ እንደነበረ መምህራን ያስተምራሉ:: እሊሁም እርምጃዎች ወደ አባቱ ፈቃድ መሥዋዕትን ወደ ማሳረግ፣ የክፉ መንፈስን ፈቃድ ወደ መከልከል እና ከውሸት በቀር ያሉትን ሰውኛ ባሕርያትን በመዋሐዱ ለባሕርያቶቻችን ፈቃድ ወደ መታዘዝ (ሕግጋትን ወደ መፈጸም) የሚራመዱ ነበሩ:: በሦስተኝነት የተገለጸው: ሁላችን ሰው እንደመሆናችን የምንታዘዛቸው የባሕርይ ፈቃዳት ናቸውና የምንነት ትንታኔ አያስፈልጋቸውም:: የመጀመሪያው: የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ፈቃድ በባሕርያችን ውስጥ በመግለጽ እንደ መሥዋዕት ያሳርግበት የነበረው ነው:: ለምሳሌ የእግዚአብሔርን ፍጹም ደግ ፈቃድ ገልጦ ለሰዎች ደግ በመሆን: ደግነትን በመሥዋዕትነት ያሳርገው ነበር (የአባቱ ፈቃድ የእርሱም እንደመሆኑ መሥዋዕቱንም የሚቀበለው እሱዉ ነው):: ፍቅርን፣ ቸርነትን፣ እውነትን በባሕርያችን እየገለጸ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መመላለስን አሳይቶናል:: በሁለተኛው: ከዚህ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የሚቃረኑ ክፉ ፈቃዳት መሹለኪያ እንዳያገኙ ፈለጉን እያጠፋ ይጓዝ ነበር:: ተዓምራትን ይፈጽምና፣ ሕሙማንን ይፈውስና "ለማንም አንዳች አትንገሩ" እያለ ዱካውን ከታዳኞች (ክፉ መናፍስት) እይታ ይሰውረዋል:: (ማር. ፰፥፳፮) ጠቅለል ስናደርገው: ነገራትን በሦስት አንድምታ ማየት የሚልን አሳብ እንውሰድ::

ክርስቲያኖች እንደ ክርስቶስ በሚኖሩት መንፈሳዊ ሕይወታቸው ውስጥ ተፈጥሮ ከሚያስገድዳቸው ከሥጋ ፈቃድ በተጨማሪ አሳቦቻቸውን፣ ቃሎቻቸውንና ድርጊቶቻቸውን እንደ እግዚአብሔርና እንደ ክፉው ፈቃድ እያስተዋሉ ሊኖሩ ይገባቸዋል:: ይህ አሳብ እንደ እግዚአብሔር ሲታይ ምንድነው? በሰማሁት [ወይም በተናገርሁት] ቃልስ የክፉው ፈቃድ (ቁጣ፣ ሐሜት፣ ቅናት፣.. ) ተገልጿል? በዚህ ክዋኔ ውስጥ ማን ይከብራል? እግዚአብሔር ወይስ ዲያቢሎስ?.. እያሉ ውሎዎቻቸውን እየጠየቁ መልስ ሊፈልጉ ያስፈልጋቸዋል::

ምእመናን: ይህን መልስ እንዴት ይፈልጉ?
፩• ዕለቶችን በመዝገብ እያሰፈሩ በመፈተሽ :- እንደሚታወቀው ብዙዎቻችን በውክቢያ ሰዓታት ተጠምደን ቀናትን እናሳልፋለን:: ገሚሶቻችን ቀኑን እንዴት እንዳሳለፍነው በማናስታውስበት ሁናቴ በደመ ነፍስ እንመላለሳለን:: ሌሎቻችን አቅደን ካስቀመጥነው መካከል አንዱንም ሳናሳካ ዕለቱ እንዳደረገን እንሆናለን:: በዚሁ ሁሉ ውስጥ ታዲያ አይሎ የሚገዛን የሥጋችን ፈቃድ ብቻ ይሆናል:: በዚህ የሥጋ ፈቃድ ደግሞ መንፈሰ ክፉ ይመካል:: ሲሆን ከፊት ቀድሞ ይመራዋል: ሲሆን ከኋላ እየተከተለ ይስበዋል:: ድክመቶቹንም እንደማወቁ እንደሚፈልገው እያላላ እያጠበቀ ይቆጣጠረዋል:: እርሱ የሚያቀብለውን ብቻ እንዲወስድ ዙሪያውን በእርሱ ምርጫዎች ይሞላበታል:: የአምላክን ፈቃድ የምትፈቅደው ነፍስ ሥጋን እንዳትመራ: አስተሳሰብን የሚገዛ ሰማያዊ ዕውቀት ከሕይወታችን እንዳይጠጋ ሕዋሳትን ከውጪ ወደ ውስጥ: ከውስጥም ደግሞ ወደ ውጪ እየተመላለሰ ይሸብባቸዋል:: ይህንን መሠረት አድርገን ካሰብን: "ሥጋን ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነው" ያለው የሐዋሪያው ቃል ግልጽ ሆኖ የሚረዳን ይሆናል (ሥጋ: ብሉዩ ዓለም: ከእግዚአብሔር የተጣላው ለዲያቢሎስ ተሰማምቶ እንደሆነ አልዘነጋንም):: (ሮሜ. ፰፥፯)

ስለዚህ: ዕለት ዕለት ከማይቋረጡ መንፈሳዊ ልምምዶች በተጓዳኝ በቀኑ መጨረሻ ላይ የጥሞና ሰዓት ወስዶ አዋዋልን እንደ እግዚአብሔርና እንደ ክፉው ፈቃድ መገምገም: ከላይ ያልነውን: የሥጋንና የክፉውን ፈቃድ ተጋቦት እንድናጤን ጊዜ ይሰጣል (በሥጋ ዘዴና ችሎታ በመታገዝ ይህ ተጋቦት በተገለጸበት ቅጽበት ላይ ልናስተውል አንችልም፤ በሥጋ ነገራት ውስጥ በመደበቁ ረገድ የዲያቢሎስ ተንኮል ልናስብ ከምንችለው በላይ ረቂቅና ጥልቅ ነው፤ ስለዚህ ነው ወደኋላ (ወደ ቅጽበቶቹ) እየተመለሱ ውሎን መፈተሽ ያስፈለገው):: በመሆኑ ለሁለት የተከፈለ ሠንጠረዥ በማዘጋጀት: እንደ እግዚአብሔርና ተቃራኒው ፈቃድ እንዴት እንደዋልን መስመር በመስመር በመጻፍ ሳናስተውል ካለፍናቸው ሰዓታት ትምህርት መውሰድ: ቀጣዩ ቀን ከራሱ ክፋት ተጨማሪ የዛሬን ክፋት ጨምሮ እንዳያከማች በመጠበቅ: የሚሰበሰቡ ጥፋቶች ከሥር ከሥሩ እንዲጠፉ ያደርግልናል::

፪• በተዘክሮተ እግዚአብሔር :- መጽሐፍተ መነኮሳት በየትኛውም መቼት ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔርን ማሰብን ተዘክሮተ እግዚአብሔር ሲሉ ይጠሩታል:: በልቡና: አምላካዊውን ነገር ሳያቋርጡ ማውጣት ማውረድ: መንፈሳዊውን እውነት ቸል ሳይሉ በአሳብ ማመላለስ: የነፍስና የሥጋ ሕዋሳት እየተናበቡ ማስተዋላችን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲቆይ ያግዛልም ሲሉ ልምዶቻቸውን ያካፍሉናል:: ብቻም ሳይሆን: አሳብን ተመሳስሎ አሳብ የሚያቀብለውን ክፉ ሹክሹክታ እንድንለይ: ለይተንም አውጥተን እንድንጥል ጉልበት የሚሆንን ኃይል እንደምናገኝበት ያሳስቡናል:: በዚህም: በጥድፊያ ደቂቃዎች ተሳብበው በኛ ለመገለጽ ከሚቻኮሉ ክፉ ፈቃዳት ተጠብቀን: ሰላም የምናስብ፣ ሰላም የምንናገር፣ ሰላምንም የምናስተላልፍ የክርስቶስ መልኮች በምንሆንበት ዕድል ዘወትር እንድንተጋ ይመክሩናል::

ተዘክሮተ እግዚአብሔር: ልቡናችን በሰቂለ ኅሊና ወደ ሰማያት ከፍ ከፍ እያለ እሾህና አሜኬላ ካጫነቁት ምድራዊ አነዋወር ተለይተን በእግዚአብሔር ዘንድ የምንሆንበት ውብ ጸጋ ነው:: በቅዳሴ ዘሐዋርያት: ካህናት 'አልዕሉ አልባቢክሙ - ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ'፤ ባሉ ጊዜ 'ብነ ኅበ እግዚአብሔር አምላክነ - በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን' እያልን ተሰጥዖን የምንመልስላቸው ይህንኑ ጸጋ ስለማስመልከት ነው:: በእግዚአብሔር ዘንድ ካለን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመዋል አንቸገርም:: ቀኝ አውለን ብለን ወጥተን በግራው አንመላለስም:: በሚለክፉ ገጠመኞች ተለክፈን ቀናችንን አናማርርም:: ምክንያቱም: አሳባችን እንደ እግዚአብሔር አሳብ ምሳሌነቱ ሁለንተናችንን አስቦ ያስገኛልና: ፍላጎታችንን፣ ስሜታችንን፣ ጠባያችንን፣ ድርጊታችንን ከቁጥጥር መዳፋችን አውሎ: በሰውነት እርሻ ላይ የሚያብቡትን የወይን (የመንፈስ) ፍሬዎች የሚያጠፉ ጥቃቅን ቀበሮዎችን (ክፋቶች፣ ስሕተቶች፣.. ) አጥምዶ ስለሚይዝልን ነው:: (፩ኛ ቆሮ. ፫፥፱ ፤ ገላ. ፭፥፳፪ ፤ መኃ ፪፥፲፭)

@bemaleda_neku
10.4K viewsedited  10:57
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-11 22:14:12 ለኵነኔ የማያበቃ የኃጢአት ትንሽ ባይኖረውም: መሠረትነታቸውን ለመናገር ያህል አበው ሦስቱ አርእስተ ኃጣውኡ (የኃጢአት ታላላቆች) ሲሉ የሚጠሯቸው አበይት የሰይጣን ፈተናዎች አሉ:: ስስት፣ ትዕቢትና ምቾት (ፍቅረ ንዋይ) ይባላሉ:: ዓይነተ ብዙ የዲያቢሎስ ውጊያዎችን ሰብስበን ብንደምር ብንቀንስ ከነዚህ ከሦስቱ አይወጡም:: በዚህ የተነሣ በነዚህ ፈተናዎች ድል የተነሣ: የተቀሩትን ማሸነፍ እንደማይቻለው ይነገራል:: ስግብግብነት ያስቸገረው፣ ትሕትና የጎደለው፣ ድሎት ደስ የሚለው ሌሎች ጥፋቶችን ማጥፋት አይሆንለትም ነው ብሂሉ:: ለምሳሌ ዝሙትና ቅንጦት ይዋደዳሉ፤ የስንፍና እጮኛ ሆድ ናት፤ ዕብሪትና ንስሐ ተግባብተው አያውቁም:: ... አንቺ ማስተዋል የሚሉሽ ሆይ፥ አንዴ ነይማ: እዚህ ትፈለጊያለሽ!

@bemaleda_neku
9.2K views19:14
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-07 12:43:13 ፬. ዮሴፍና ዮሃንስ

ዮሴፍ ለማርያም በእጮኝነት ስም የተመደበ ባለአደራ ነው። ይህ ሰው በማያውቀው ሁኔታ የማርያምን መፀነስ ሲያውቅ ሊተዋት ሲፈልግ ‘እርሷን ለመውሰድ አትፍራ፣ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና ውሰዳት” ተብሎ ወስዷታል። ዮሓንስ በቀራንዮ “እነሆ እናትህ“ ተብሎ ወስዷታል። ሁለቱ ሰዎች ማርያምን ውሰዱ በመባል አንድ ናቸው፤ አንዱ በጽንስ ሌላው በመስቀል። ዮሴፍ ተወዳጁ በህጻንነቱ እንዳይገደል ከእናቱጋ ይዞት ሸሽቷል። ሄሮድስ አላገኘውም። በመከራው ብዙ ተፈትኗል። ቤተሰብ ይዞ መሰደድን የሚያውቅ ያውቀዋል። ፈተናው “ውሰድ” ከተባለ በኋለ የተከተለው ነው። ዮሓንስ ማርያምን ተወዳጁ በመከራ ሳለ ነው የወሰዳት። እነሆ እናትህ ተባለ። በማርያም እናትነት በኩል የጥምቀትን እናትነት ተመልክቶበታል። በጌታ ሞት እኛ ተወልደንበታል። ስለዚህ በማርያም ውስጥ የዮሓንስ ልጅነት ሲኖር በዮሓንስ ውስጥ የማርያም እናትነት ታውቋል። በዚህ ውስጥ የአብን ወላዲነት የወልድን ልጅነትንም አውቋል። “አባት ሆይ አንተ በእኔ እኔም ባንተ እንዳለሁ እነርሱም በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ” ያለውን ቃል ያስቧል። ዳግም ከተወለድን በኋላ ሰውን በክርስቶስ እንጂ በሥጋው አናውቀውም። ለምሳሌም ማርያምን የምናውቃት ኢየሱስ በእርሷ በሰራው ታላቅ ስራና ጥበብ እንጂ በመልኳ ወይ በዜግነቷ አይደለም። የተነሳው ክርስቶስ በመልክ እንደማንረዳው ሁሉ በትንሳኤው ያሉትንም በመልክ አናውቃቸውም። በቃል፣ በድምጽ ይታወቃሉ። ቃሉም መንፈስና ህይወት ስለሆነ ስንሰማና ስንኖራቸው እናውቃቸዋለን። ዮኃንስ ይህን የመንፈስ ቅዱስ ስርዓት አግኝቶታል። ቃሉን ሰምቶ የሚያደርገው ለጌታ እናቱም ወንድሙም ዘመዱም ነው። ተወዳጇ እመቤትም “እንደቃልህ ይደረግልኝ” በማለቷ ቃል በእርሷ ሥጋ ሆኗል። እናቱ ሆናለች። በዚህ በኩር ናት።

በዮሴፍ ጊዜ ተወዳጁ አልተገደለም። በዮሓንስ ጊዜ ግን ተወዳጁ በፈቃዱ ሞቷል። ዮሴፍ የግርዘቱን ደም ሲያይ ዮኃንስ የመከራውን ደም ተመልክቷል። ማርያም ሁለቱንም ጊዜ ተመልክታለች። ዮሓንስ በራእዩ ሴቲቱ 1260 ቀን እንደተስደደች ጽፏል። ይህ ሶስት ዓመት ከመንፈቅ በዮሴፍ ጊዜ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ዮሴፍ ህፃኑና እናቱን ይዞ ከሄሮድስ ተሸሽጎባታል። ግብጽና ኢትዮጵያ መሸሸጊያ ናቸው(መንበረ ማርቆስ)። ይህን ያወቅነው በዮሃንስ የመቅደስ መለኪያነት ነው።መለኪያው ያለው ዮሓንስን ሆኗል (ማርያምን “ፀጋን የሞላብሽ” የሚያስብለን መንፈስ ለእኛም የተሰጠ እንደሆነ ያመለከተን ዮሓንስ ነው።”ቃል ስጋ ሆነ።ጸጋና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ” በማለት...በዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ክፍፍል መነሻዎች ይህ የቃል ሥጋ ሆነ ነገር ነው)።

1260 ቀን በሰሜኑ በር 1985 ዓመታት ናቸው። ዓለምም እውነቱን ሲያሳድድና ሲገል እስከዛሬ አለ። ለዚህን ያህል ዘመን ይህ የወንጌል እውነት ተሸሽጎ ነበር። አሁን ከስደት ተመልሷል። እንደ ዮሴፍ በዚህ ተሸሽጓል። እንደዮኃንስ ከዚህ ይነገራል። 1985 ዓመታቱ ተጠናቀዋል። ዮሴፍ ስራውን ፈጽሟል። ዮሓንስ ይቀጥላል። በትንሣኤው “ና ተከተለኝ” ተብሎ በድጋሚ የተጠራ እሱ ነው።ወደ አብ የሚያርገው ተወዳጅ ስለጠራው ሙሉውን መለኪያ አግኝቷል። ‘በመጀመሪያ ቃል ነበር’ ብሎ ከአብ መወለዱን መስክሯል። የማርያምን የአብ ምሳሌነት አውቋል። አግኝቶታልም። ኖሮታልም።

ቅዳሴያችን በቤተልሄም ጀምሮ በቀራንዮ ያልቃል። እንደ ማርያም ስናየው በዮሴፍ ጀምረን በዮሃንስ እንፈጽማለን። ይህ እውነት በህይወታችን ከተፈጸመልን በእውነት ፍልሰታው ለእኛም ሰርቷል። በእምነቱ በዮሴፍነት ላይ ያለም በበአለ ሃምሳ ያለም ይጸልይ። ፍጻሜው ጌታ ነው፤ ይገለጻል። አበው ዮሴፍና ዮሃንስ አብረው ሲቀድሱ የዓለም ፍጻሜ ይሆናል ይላሉ። ሁለቱን በአንድ ሰብእናና ዘመን አግኝተን እየኖርነው አይደል? ኢትዮጵያ የዮኃንስ ራእይ ማእከል ናት። በመቅደሱ ፍጻሜ በቅድስተ ቅዱሳን ነን። በሃያው ክንድ ወይም በአስሯ ቀን ነን። እርሷም መቶሃያው ቤተሰብ የተጉባትና በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁባት ናት። አህዛብን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛው ወንዱ ልጅ በዚያ ይኖራል። ለሁሉም እንደየቋንቋው ሊሰማው የሚችል ከነገድ ከቋንቋ የሚዋጅ የፅዮን ድምጽ ይነገርባታል።

፻፳ን በ፲ ስናበዛው ፲፪፻(1200) ቀናትን ይሆናል። ከዋናው የበዓለ ሀምሳ ፶ ቀናት'ጋ ሲደመር ሶስት ዓመት ከስድስት ወር ይሆናል (እራሳቸው መቶሃያው ቤተሰብ ሶስት ዓመት ከመንፈቅ ተሰደዋል። አሁን ይህ እየሆነ ነው። በምስራቁ በር መንፈስ ቅዱስ የወረደው በማርቆስ እናት ቤት ነው። በሰሜኑም እንደዚያው ይሆናል (ኢትዮጵያ በማርቆስ መንበር ናት፤ እዚያ ነን)፡፡ ዛሬ በዓለምና በተለይ በሃገራችን ዘንዶው እያሳደደ ያለው ይህን እውነት ነው። ምእመኗን ካላጠፋሁ ብሎ የከበበው ለዚህ ነው። ለ1260ቀን ውሸቱን እየለቀቀ ያሳድዳል። "ምድር ግን ሴቲቱን ረዳቻት" ይላል ዮኃንስ። ዘንዶው የተፋውን ውኃ ውጣዋለች። እኛ ከተማይቱን ገልጾልን አይተናታል። ከሃያው ክንድ ኅይል ይወጣል። እንደሄደብን ይመጣል። ደግሞም መጥተናል። እስቲ እንደሀዋርያት እንዲገለጽልን የምንፈልገውን ነገር እንንገረው። ፍጻሜው ላይ ነን፤ ሚካኤል ስራ ላይ ነው (ለዛሬ በጸሎት ያላችሁ የዮኀንስ ወንጌልን እያነበብችሁ አስቡን)።

ተጻፈ: በደመወዝ ጎሽሜ
ማስታወሻ :- ፲፮ የሚለውን መጽሐፉን ካላነበባችሁ የቁጥር ስሌቱን ጨምሮ ሙሉ መረዳት አይኖራችሁም:: ለአሁን፣ የሆነ ነገር ካገኛችሁበት በቂ ነው:: ዞሮ ዞሮ፣ እስቲ መልካም ቆዩ!

@bemaleda_neku
11.9K viewsedited  09:43
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-07 12:42:27 ሰሙነ ፲፮
ማርያምና ኢትዮጵያ

ሰሞኑ ለተዋሕዶ ክርስትና አማኞች የፆም ወቅት ነው። የፍልሰታ ፆም! እስቲ አንዳንድ እውነታዎችን እንጨዋወትበት።

፩. የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም!

ከቶማስ ውጭ ያሉት ሌሎች ሐዋርያት የማርያምን ትንሣኤ ከእርሱ ሰምተው መንፈሳዊ ቅናት ይይዛቸውና ሱባኤ ይገባሉ። ተገለጸችላቸውም። ጾሙ የዚህ መታሰቢያ ነው። እኛ ጾሙን ለሕይወታችን እንጠቀምበታለን። ታሪኩ እንዳለ ሆኖ 'ለሐዋርያት ምስጢር ይከፈልባቸዋል ወይ? ለአንዱ ተገልጾ ለሌላው ሳይነገር የሚቀር ነገር አለ?' ብለን እንጠይቅ። እርገት በመጽሀፍ ቅዱስ ሲመሰጠር የወንድ ስርዓት ነው። የሴት አይደለም። ዝርዝሩ ይቆየን። ሐዋርያትን ሊያስደንቃቸው የሚችለውም ይሄ ነው። በተለምዶ ይሁን ለቃል ካለመጠንቀቅ ባላውቅም የድንግል ማርያም እርገት ከተወዳጁ እርገት'ጋ ተመሳስሎ ይነገራል። የማርያም እርገት ከጌታ እርገት ይለያል። የጌታ ወደአብ፣ ወደክብሩ፣ ወደ አባቱ የገባበት ነው። በሊቀ ካህንነቱ እስካሁን ነፍሳችን ትገለገላለች። ወደ አብ በመግባቱ በምልአት እንደ አባቱ ሆነ። በሰው በኩል ሲታይ “ሰው አምላክ ሆነ “። የእግዚአብሔር ሀሳብ በእኛ ለመታሰብ ቻለ። ይህ የሆነልን በተወዳጁ እርገት ምክንያት ነው። ጳውሎስም ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም የሚለው ለዚህ ነው። የማርያምና የሀዋርያት ግን በትንሳኤው ቢመስሉትም በእርገት ወደ አብ አልሄዱም። በነፍስ ስርዓት ይኖራሉ። ጌታ ተነስቶ ለአርባ ቀናት በኖረው ስርዓት ይቆያሉ። እነሱ የሞትና የሕይወት ቁልፍ ያለው የእግዚአብሔር ልጅ የሰጣቸው ልጅነት አለቻቸው። ስለዚህ ሲሞቱም ፈልገውት እንጂ ሞት ገዝቷቸው አይደለም። ጳውሎስ “ቢሆንልኝ የሞቱን ጥምቀት እጠመቃለሁ” የሚለው በሞት መንገድነት የሚገኝ ታላቅ ምስጢር ስላለ ነው። ልጅነት ካለችህና ሙት ካስነሳህ አንተም ትነሳለህ ማለት ነው (ጠንቋይ ነው ለራሱ የማይሆነው)። ጌታ የኅያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እነማርያም ሕያዋን ናቸው። ጌታ እንዳለው ”አምላክ ሙሴን ሲያናግረው የአብርሃም፣ የይስሃቅ፣ የያእቆብ አምላክ ነኝ” ማለቱን በመጥቀስ የህያዋን አምላክነቱን ተናግሯል። በሞቱ እንደመሰሉት በትንሳኤውም ይመስሉታል። ሞቶ መነሳት ዋንኛ መገለጫው በአንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ መገኘትን ነው። አንዱ ስንዴ ሞቶ ሲነሳ ብዙ ሆኖ መውጣቱን ይመለከቷል። ጳውሎስ ስለ ትንሳኤ ሙታን ሲናገር “እኛ ህያዋን ሆነን የምንቀረው ያንቀላፉትን አንቀድምም” በማለት ነው። ታሪክ ጳውሎስ እንደሞተ ይናገራል። እርሱ ግን እስከ ምጽአት ህያው እንደሆነ ይናገራል። ጳውሎስ ትክክል ነው። እነርሱ በዙሪያችን አሉ። እንደ ደመና ከበውናል። የትንሳኤን ትምህርት ምስጢር የሚያሰኘውም እንደዚህ አይነት በመኖር ብቻ የሚታወቁ ነገሮች ስላሉት ነው። በዚህ የተነሳ ማርያምም ተነስታለች። ሁሉም ግን በራሱ ተራ ነው።

፪. ቶማስ

ሀዋርያት በቶማስ ያዩት ግን ያላወቁት አንድ ጉባኤ አለ። ይህም ከእርሱ በስተቀር ትንሣኤውን ያመኑት በቃልና በመገለጽ ነው። እንደ ቶማስ በመንካት አላመኑም። የተወዳጁን ጎን በመንካት የሚያነጋግረው ኢየሱስ እንደሆነ አውቆ አመነ። ያ ጎን በቀራንዮ ደምና ውኃ የፈሰሰበትና አባት በልጁ አምጦ እኛን የወለደበት ነው። ማየ ገቦ እንዲል መጽሀፍ። ከተወለድንበት ማህጸን ነው ማለት ነው። እናት!

የተነሳው ተወዳጅ ስጋና አጥንት ከመስቀል በፊት ከነበረው ስጋው የሚለይበት አንድ ነገር አለ። የተነሳው የሞት አገልግሎት አይከናወንበትም። ቀን በጨመረ ቁጥር ለሞት አይቀርብም እንደማለት ነው(በትንሳኤ የማያስፈልጉ የሰውነት ክፍሎችና ስርዓቶች አሉ። የሆድ እቃ ላያስፈልግ ይችላል እንደማለት ነው) እኛ ወደእርጅና እንገሰግሳለን። ጌታ ከተነሳ በኋላ ይህን አስቀርቶታል። ከክብር ወደ ክብር እየሄደ በመጨረሻም እየረቀቀ ሄዶ ወደ አባት ገብቷል። መርቀቅን ነው ማረግ የምንለው። ቶማስ ይህን አካል ነክቶት አምኗል። ይህ የነካው ስጋ ከማርያም የነሳው ስጋ ነው። ይህ ስጋ በነፍስ ስርዓት ውስጥ ያለ ነው።

፫. መቶ ሃያው ቤተሰብ

ጌታ ካረገ በኋላ ያሉት አስሩ ቀናት በሰሜኑ የመቅደሱ በር ሲለኩ 16.4 ዓመታት እንደሆኑ ከዚህ በፊት አውስተናል። ይህ የቅድስት ቅዱሳን ቁጥር አብን ይወክላል። ከአስሩ ቀን መንፈሱን ልኮ ወልዶናል። ማርያም የአብ ምሳሌ የተባለችውም በዚህ ወላጀነቷ ነው። በ16.4 ዓመቷ ወልዳዋለች። ይህ በስጋ ነው። በእነዚያ አስር ቀኖች ውስጥ 120ው ቤተሰብ እየጸለዩ ነበር። ማርያም እዚህም አለች። በስጋዋ የሆነውን ነገር የተረዳችውና ያወቀችው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነበር። የዚህ እውነት ምሳሌነቷን በሥሉስ ቅዱስ ተረጋገጠላት። ይህ የፅዮን እናትነት ነው፤ ሁሉም የሚወለድበት። 16.4 ለእርሷ ብቻ ታውቆ አልቀረም። ሁሉም ይህን እናትነት አገኙት። ተገለጸላቸው።

አጠቃላይ መቅደሱ በዘመን ሲለካ 1968 ዓመታትን ይሆናል (ፖለቲካችን ከመቅደስ የወጣበት ዘመን ነው)።መቶ ሀያው ቤተሰብ የኖራት ፲ ቀን ወይም 16.4 ዓመታት ቅድስተ ቅዱሳን ናቸው። ሁሉም ይህንን የወላጅነት ስርዓት አግኘተውታል። ተገልጾላቸዋል። በሌላ አባባል እያንዳንዳቸው 16.4 በመሆን ዓለምን ለውጠዋል። ስሌቱ ፦
1968 ÷ 120 = 16.4

በበዓለ ሀምሳ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ድምጹ ተነግሯል። ይህ ሁነት በሰሜኑ በር ለ1968 ዓመታት ክርስትና ለዓለም ሁሉ ተሰብኳል። በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተመስክሯል። እኛም ይህ እንዲገለጽልንና እንድንኖረው ያስፈልጋል። ስሌቱም የሚናገረው ይህንን ነው (በነገሬ ላይ አንድ ሰው ለመብቃት 16 ዓመት ይፈጅበታል ማለት አይደለም። ይህ በጉ በሄደበት ሁሉ ለሚሄዱት የተሰጠ ነው። ከእነሱ የተነሳ ይህን በማመን የምናገኘውን ጸጋ ሰው ሆኖ በተገለጸበት ምልዓት መጠን ለመግለጽና ምን ያህል አምላክ እየሰራ እንደሆነ ለማወቅ እንዲረዳን ነው። ሁሉ በእርሱ ሆኗል። ያለ እርሱ የሚሆን እንደሌለም እንድናይበት ነው።)
8.6K viewsedited  09:42
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-01 17:32:34 በሌላውም ጎን አሁንም ማርቆስ: ጌታችን አጋንንት ያደሩበት ሰውን ሲያነጋግረው ጽፎአል:: መንፈሱ ኢየሱስን በተመለከተ ጊዜ እየሰገደ እንዳያሰቃየው ሲለምነው: እርሱም "ማን ትባላለህ?" ብሎ ሲጠይቀው ተጽፎአል:: መንፈሱም "ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው" ብሎ መልሶአል:: (ማር. ፭፥፯-፲) ደግሞ ክፉ መንፈስ ልጁን ዲዳና ደንቆሮ ያደረገበት አባት፥ መንፈሱ ልጁን የያዘው ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ በጌታ ሲጠየቅ በሌላ ገጽ ተጽፎአል:: ወላጁም ከሕፃንነት ጀምሮ እንደያዘው ተናግሮአል:: (ማር. ፱፥፳፩) አሁን እዚህ ደግሞ "ዝም ብሉ" የተባሉት መናፍስት ስማቸው ሲጠየቅ፣ ከመቼም ጊዜ ጀምሮ እንደገቡ ሲነገር እናነባለን:: ትምህርተ ኅቡዓት የሚሰኝ ጸሎትም የሆነ መጽሐፍ የዲያብሎስን ምስክርነት "የተረታ ባላጋራ የወደቀ ወይራ እንዲሉ የጠላትም ምስክርነት የታመነ ነው" ሲል በአንድምታ ገጹ አጽድቆ አሰቀምጦታል:: የተወደዱ ሰው አለቃ አያሌው ታምሩ ደግሞ "እግዚአብሔር፤ በፈቀደ ጊዜ ሥራውን ለማስመስከር ኃጥእ፣ ጻድቅ፣ አማኝ፣ መናፍቅ፣ ሰው፣ ሰይጣን፣ እንስሳ፣ ደንጊያ አይመርጥም" ሲሉ ጽፈዋል:: (የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት) እንዴት ነው ነገሩ?..

ፍቅር የአንድነት ኃይል ነው:: የማይስማሙትን እንኳ የሚያስማማ ልዑል ጥበብ ነው:: ይሄ በተፈጥሮአችን ውስጥም ምስክርነት ያለው እውነት ነው:: ሥጋ፥ ማይ፣ እሳት፣ ነፋስና መሬት ከሚባሉ ከአራቱ ባሕርያት እንደተፈጠረ የዘፍጥረት ትምህርት ያስተምራል:: እነዚህ ባሕርያት በተፈጥሮአቸው አንዱ ከአንዱ የማይስማሙ ናቸው:: ግን በሥጋዊያን ፍጥረታት የተስማሙ ሁነው አሉ:: ውኃው እሳቱን ሳያጠፋ፣ እሳቱም ውኃውን ሳያፈላ፥ ነፋሱ አፈሩን ሳይበትን፣ አፈሩም ነፋሱን መውጪያ ሳይከለክል አሉ:: ምክንያቱም ፍቅር ከመካከላቸው ሆኖ ለተዋሕዶ አስታርቋቸዋል:: እንዲያውም ልዩነቶቻቸውን የአንድነታቸው ምክንያት አድርጎ አስውቧቸዋል:: ውበታቸውም መልካም እንደሆነ አይቶላቸዋል:: (ዘፍ. ፩፥፴፩)

ዘመዴም የሆነ አንድ ወዳጄ "እግዚአብሔር ግን በዚህች ቅጽበት ዓለሙን እንዴት ይሁን የሚያየው?" ሲል በአንድ ወቅት ይጠይቀኛል:: ልመልስለት ጀመርኩና ነገሬን መልሼ ማሰብ ጀመርኩ:: እውነትስ ሁሉን በያለበት እንዳለበት ሳለ የሚያይ አምላክ ምን እየተመለከተ ይሁን? ይሄን ሁሉ ቢሊዮን ሕዝብ በየተናጠል ማየት የሚችል እርሱ ስንት ዓይነት ነገር እየተመለከተ ይሁን? በአንድ ሰኮንድ ብቻ እንዴት ያሉ ኃጢአትና ጽድቆችን እያየ ይሁን?.. ለማሰብ እንኳ ያስጨንቃል! አሉን የምንላቸው እውነቶች መልክና ታሪክ ለውጠው ሌሎችም ጋር ሊኖሩ እንደሚችሉ አውጠነጠንኩ:: እውነት እንደ አንድ መጽሐፍ ብትሆን ልዩ ልዩ ምዕራፎችን በገጾቿ ልትይዝ እንደምትችል ማስተዋል በጎ ነው:: አንዳንዴ እስ በእሳቸው የሚጣሉ አሳቦችም የየራሳቸው እውነት ሊኖራቸው ይችላል:: ይሄ የሚረዳን ግን ግብዝነት የተለየው ፍቅር ያገበረን እንደሆነ ብቻ ነው::

በአንዱ በማርቆስ መጽሐፍ: አንዴ ዝም ብሉ፣ አንዴ ተናገሩ የተባሉትን አጋንንት ኑዛዜያቸውን የማዳመጥ ነገሩ በደፈናው ተገቢ ነው ተገቢ አይደለም ተብሎ የሚደመደም ሳይሆን እንደ ባለብራና አባቶቻችን ንባብን የማጤን እይታ በአንድምታ አውድ ቢገናዘብ ደግ ነው:: አበው የሚጣሉ ትርጓሜዎችን በአንድ ቃል ሥር 'አንድም' እያሉ አስታርቀው የሚተነትኑበት ድንቅ ስልት አላቸው:: ሙሉ አሳብና ታሪክ እንዲኖር: ከሰይጣን አንጻር መተርጎም ካለባቸው፥ ይተረጉማሉ፤ እንደገና ክፉን ወክሎ የተነገረ ቃልን ለቅዱስ አድርገው ያመጣሉ [ለምሳሌ ራእየ ዮሐንስ ም. ፱ አንድምታ]:: ይሄ ቅንነታቸውንና መንፈሳዊ ልዕልናቸውን ያመለክታል:: ብቻም ሳይሆን ሁሉን በተለያየ ጎኑ ለሚመረምረው መንፈስ ቅዱስ መታዘዛቸውን ያረጋግጣል::

"ማን ትባላለህ?" ተብሎ በነጠላ ቁጥር ለተጠየቀው ጥያቄ "ብዙዎች ነንና ሌጌዎን እንባላለን" ሲል ርኩስ መንፈስ ለጌታችን የመለሰው መልስ: አጋንንት በሰው ሕይወት ውስጥ ገብተው ከመኖራቸው በላይ ብዙ ሠራዊት ሰብስበው እንደሚሰፍሩ ይጠቁማል:: ይህንና ከሕፃንነት ጀምሮ እንደገባና የተለያዩ ሥቃዮችን በልጁ ላይ እንደሚያደርስበት የተናገረው የተጨነቀውን አባትን ጨምሬ ሳስብም: መናፍስት ምን ዓይነት ማንነት (ሁሌ ባይሆንም በስያሜአቸው ሊገለጥ የሚችል ነው) ይዘው እንደሚገቡ፣ መቼ እንደሚገቡ፣ ስንት ሆነው እንደገቡና ገብተው ምን እንደሚሠሩ አውቆ ማሳወቅ: አድራሻው ሰዎችን ለማስጠንቀቅ፣ ከክፉ ለመጠበቅ፣ በክፉ የተያዙትንም ከክፉ ለማስለቀቅ ታስቦ እንደሆነ፥ ወንጌልን ዋቢ ያደረገ በጎችን ከተኩላዎች የመጠበቅ አስፈላጊ አገልግሎት እንጂ ሌላ አይደለም:: ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ፥ የመናፍስትን ዓይነተ ብዙ ጾር ከየአደፋፈጥ ጥበባቸው ጋር ልዩ ትኩረት ሰጥተው የሚያስተምሩ እንደ መጽሐፈ ፊልክስዮስ ያሉ ታላላቅ መንፈሳዊ መጽሐፍት ሊጠቀሱ ይችላሉ::

ይሄ ሲባል ግን መናፍስት ሁልጊዜ ሲናገሩ በተቻለ አቅም የሐሰትን ጠርዝ ተጠንራርተው ለመንካት ዳክረው እንደሆነ ማስተዋል ደግሞ እንደ ኃላፊነት ከውጊያ ትምህርት መምህራን ይጠበቃል:: በወንጌል ዕውቀትና ትሕርምት ያልዳበሩ ምእመናን የክፉዎቹን ኑዛዜ የሚያመዛዝኑበትን የአእምሮ ልክ ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት ሊሰጡ ያስፈልጋቸዋል:: በላይኛው አንቀጽ እንደተገለጠው ምእመናንም እንደ ፈውስ፣ እንደ ተዓምር፣ የትምህርት መጽሐፉን ሥዕል ሥዕሉን እንደሚያይ ታዳጊ ሳይሆን፥ እንደ መንቂያ ዕውቀት፣ ወደ አምላክ እንደ መመለሻ ምክንያት የመናፍስትን የውጊያ ዘዴዎችና የሚገልጧቸውን ጠባያት ቦታ ሰጥተው ሊሟራቸው ያስፈልጋቸዋል:: ብቻም ሳይሆን ይሄ ትምህርት ራስን ከክፉ ዕውቀት (ርኩስ መንፈስ) የመከላከያ ሲሆን ራስን በመልካም ዕውቀት (መንፈስ ቅዱስ) ለማሳደግና ለማትጋት መጽሐፍትን የመመልከት፣ ቢያንስ መሠረታዊ ትምህርቶችን የመከታተል ጊዜም ሊኖራቸው ግድ ይላል:: አለበለዚያ ማደግ አይመጣም:: የውጊያ ሕይወት ራስን በእውነት ጋሻ ከሐሰት የመጋረጂያ ጥንቃቄ እንጂ ሥጋን መፈወሻና መናፍስትን ማወቂያ ብቻ እንዳልሆነ ደጋግሜ አንስቼዋለሁ:: ማስተዋል የሚጨምረው፣ ትሩፋት ደስ የሚለው፣ ትሕርምት ዋጋ የሚኖረው፣ አገርም የምትጠቀመው እንደተቀበልነው ጸጋ ከሐሰት እየተጠበቅን የእውነት ዕውቀትን ስንማርና ስንገልጥም እንደሆነ በግሌ አምናለሁ:: ቀደምቶቻችን፥ ዲያቢሎስን አበጥረው አንጠርጥረው ያውቁታል፤ ደግሞም መንፈሳዊ ጥበብና ዕውቀታቸውም ያስደንቃል:: ሲዋጉ ብቻ አልኖሩም ሲመራመሩም ከርመዋል:: ሲመራመሩም ብቻ አልባከኑም ምርምራቸውን የሚነጥቅ ክፉንም ሲዋጉ ቆይተዋል:: እንግዲያስ የአባቶቻችን ልጆች ብንሆንስ?.. እስቲ ያሰንብተን!

@bemaleda_neku
10.3K viewsedited  14:32
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-01 17:25:22 የአጋንንት ምስክርነት ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም ?

አንድ ሰው ከፍቅር ልዕልና ሲደርስ ሁሉን አስተካክሎ እንደሚወድ መንፈሳዊ አባቶች ይናገራሉ:: የከበሩ መልእክቶችን የጻፈ ሐዋሪያ ጳውሎስም ፍቅር ከእምነትና ከተስፋ ትበልጣለች ይላል:: (1ኛ ቆሮ. ፲፫፥፲፫) እንደውም መብለጥ ብቻ ሳይሆን፥ ያለ ፍቅር ተራራ የሚያፈልስ ታላቅ እምነት እንኳ ቢሆን ከንቱ እንደሆነ ጨምሮ ተናግሮአል:: (ቁ. ፪)

ነገርን ከዚህ መጀመሬ በምክንያት ነው:: ይኸውም የምንም ነገር መነሻችን ፍቅር እንዲሆን ከማሰብ ነው:: በክርስትናው ዓለምማ (በተለይ በሐዲስ ዘመን) የነገራት ሁሉ ፍጻሜ ፍቅር ነው:: እንዲህም መባሉ ስለ ሁለት ነገሮች እንደሆነ ይረዳኛል:: አንደኛ ሥርዓትም እንበለው፣ ትእዛዝም እንበለው፣ ትምህርትም እንበለው፣ ትሩፋትም እንበለው.. መደምደሚያ አድራሻቸው ከፍቅር ከተማ ሊሆን ግድ ይላቸዋል:: ባልንጀራን እንደ ራስ ወደ መውደድ የማያመራ የትኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ጉዞ መጽሐፍ እንደሚለው ነፋስን እንደመከተል ያለ ከንቱ ነው:: (መክ. ፩፥፲፬) ወደየትም አያደርስም:: ማረፊያ ወደብ የለውም:: የትኛውም ዓይነት ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ጸጋ፣.. ሰውን ከማፍቀር ደጃፍ ካላደረሰ ከእግዚአብሔር አልተነሣም ማለት ነው:: ከእግዚአብሔር የተሰጠ ለሰው ወደ መስጠት ይሄዳል:: የወንጌል ሕግጋት በአብዛኛው መስጠትን ማዕከል ያደረጉ ትእዛዛት ላይ የሚያተኩሩት ስለዚህ ነው::

በሁለተኛው ደግሞ ሕግን የሚያስፈፅመው ፍቅር እንደሆነ ቃሉ እንደሚያሳስብ አምናለሁ:: ለምንወደው ማንኛውም ነገር ሆነ አካል፥ ጊዜ፣ ዋጋና ጉልበት በፍላጎት መሠዋት እንችላለን:: ባከፋናት ክፉ ዓለም ሰንኖር መልካሞቹን ሕግጋት መጠበቅ ከባድና ፈታኝ ቢሆንም በፍቅር ኃይል ግን ከባዶቹ ይቀላሉ፥ ፈተናዎች ይታለፋሉ፥ ስንፍናዎች ይሰንፋሉ:: ክርስቶስ "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል" ሲል የተናገረን ይህን ስለሚያውቅ ነው:: (ዮሐ. ፲፬፥፳፫)

ከርእስ እንዳልርቅ በአጭሩ፥ የምንነጋገረውንና የምናደርገውን ሁሉ በፍቅር ስለፍቅር እንድናደርገው ሁላችንን እለምናለሁ:: አለበዚያ እንደተባለው ወደየትም አንደርስም:: ተመልሰን እዛው ነን:: የዚህም ጽሑፍ መነሻም ሆነ መዳረሻ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደማወቅ ጥግ እንዲደርሱ ታስቦ ስለመዘጋጀቱ አንባቢዎች ያስቡ ዘንድ እማልዳለሁ:: (፩ኛ ጢሞ.፪፥፫-፬) አሁን ወደ ርእሰ ጥያቄው እንሂድ::

ክፉ መናፍስት አማንያን እንደሆኑ ያዕቆብ ይነግረናል:: (ያዕ. ፪፥፲፱) ካመኑ ይመሰክራሉም ማለት ነው:: ታዲያ አጨቃጫቂ የሆነው ይህ ምስክርነት ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም? የሚለው ጥያቄ ነው:: አለው የሚሉ ወገኖች አሉ፥ የለውም የሚሉ ጎራዎችም አሉ (እነዚህ ወገኖች (ምእመናኑ) አሳብን በፍቅር መቀባበል ተስኗቸው ክፉኛ ሲጣሉና ሲበጫጨቁ አያለሁ፤ ሁለቱም ተሳስተዋል! ፍቅር ከሌለ ምንም የለምን ዘንግተዋል):: እኔ ደግሞ የምለው አለውም ሆነ የለውም ለማለት እንዲሁ አይቻልም ነው:: እንዴትነቱን እንደሚከተለው ላብራራ::

ወንጌልን የሚያጠኑ የሃይማኖት ሰዎች የማርቆስን ወንጌል የፈውስ መጽሐፍ ሲሉ ይለዩታል:: ምክንያቱም ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ያደረጋቸው ፈውሶች በብዛት ተነሥተውበታልና ነው:: ከነዚህም ውስጥ አጋንንት ከሰዎች ላይ ሲያስወጣ የሚያትቱ ክፍሎች ገና ከመነሻው ምዕራፍ ጀምሮ በተደጋጋሚ ተጠቅሰዋል:: ጥቅሶቹን ስናነብ እንደምናገኘውም፥ መናፍስቱ ጌታን ባዩት ጊዜ አውቀውት ኖረው ክብሩን ሊመሰክሩ ሲሞክሩ ዝም እንዲሉ ያዝዛቸዋል:: (ማር. ፩፥፳፭ ፤ ፴፬ ፤ ፫፥፲፪) በግብረ ሐዋሪያት ላይም የምዋርት መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት እነጳውሎስን እየተከተለች ስለ እውነት አገልጋይነታቸው ስትናገር ጳውሎስ ዘወር ብሎ ርኩሱን ገሥፆ እንዳስወጣው ተጽፎአል:: (ሐዋ. ፲፮፥፲፯-፲፰)

እነዚህን ጥቅሶች ስንመለከት ክርስቶስና ደቀመዛሙርቱ የመናፍስቱን አንደበት ዝም እንዳሰኙ እናነባለን:: የዚህንም ምክንያት በክርስቶስ ስናየው: ሚሥጢር ከመጠበቅ አንጻር ምስክርነታቸውን እንደከለከላቸው ወንጌል "እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው" በማለቱ ይታወቃል:: 'ጊዜው ሳይደርስ የጌታን ማንነት አውጀው መለኮቱን በሥጋ ድካም ለሰወረበት ለማዳኑ ዓላማ ዕንቅፋት እንዳይሆኑ ከለከላቸው' ነው ማርቆስ የሚለን:: በሐዋሪያት ስናየው ደግሞ: የጳውሎስ ግሣፄ "ዲያቢሎስ የእውነት ቅንጣት እንኳ የለውምና፥ እውነትን ቢያወራት እንኳ አትቀበሉት" ለማለት እንደሆነ መምህሮች ያስተምራሉ:: ለዚህም ዋቢነት ዮሐንስ "እውነትም በእርሱ (በዲያቢሎስ) ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና" ሲል የጻፈውን ይጠቅሳሉ:: (ዮሐ. ፰፥፵፬)

ዲያቢሎስ ውሸት የተፈጥሮው እስከትሆን ድረስ ጠባዩ አድርጓታል:: ከራሱ ሲናገር ከሐሰት በቀር አይናገርም:: እውነትንም ቢናገር ሐሰትን እንድትደግፍ አድርጎ ይሆናል:: ማለትም ሐሰትን ለማሥረጽ የእውነትን ተቀባይነት ይጠቀማል:: በእውነት ስም ታዳኞቹን ያጠምዳል:: በሂደቱም እውነትን በዓላማው መጀመሪያና መካከል ላይ ሊያወራት ይችላል:: ሐሳዌ መሢሕ፣ ነቢያት፣.. እየተባለ የሚገለጸውም ይኸው ነገር ነው:: በፍጻሜው ግን ሐሰቱን ያነግሣታል::

ስለዚህ እውነትን ቢናገር እንኳ አትስሙት የሚባለው ከዚህ አንጻር ነው:: እውነትን ተገዶ ቢያወራት እንኳ ሐሰትን በምትጠቅምበት መንገድ ሊናገራት የሚችለውን ያህል ይጥራል:: ለምሳሌ የመተት መንፈስ በእግዚአብሔር ኃይል በተያዘ ጊዜ እንዴት እንደመጣ፣ ለምን እንደመጣ፣ ከማን እንደመጣ ሳይወድ ሊለፈልፍ ይችላል (ይሄ የውጊያውን ዓለም በሚኖሩት ብቻ የሚታወቅ ሲሆን፥ መንፈሳዊ ትግሉን እንዲሁ ለሚነቅፉት የማይብራራ የሕይወት ጉዳይ ነው (እናብራራውም ብንል አይበራላቸውምና)):: ታዲያ መንፈሱ ሲናገር፥ እንደ ከሳሽነቱ እውነትን በመጠቀም ለእርሱ መልካም የሚሆንለትን አነጋገር በመከተል የመታቾቹን (መንፈስ ላኪዎቹን) መጥፎነትና ጥላቻ አጉልቶና አደንድኖ ለተመታቹ (መንፈስ ለተላከበት ግለሰብ) በመግለጽ፥ ተመታቹ በሰማው መረጃ ምክንያትነት በመታቾቹ ላይ ማንኛውም ዓይነት ክፉ ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል (ከውስጡ ይገፋፋዋል):: ሰልፋችን ከመንፈሳዊያን ሠራዊት ጋር ነው የሚለውን ወሳኝ የወንጌል መልእክት ሰማዒው ካላወቀ፥ ጠላቱ ሰው እንደሆነ ይደሰኩረዋል፤ ካወቀ ደግሞ ይሸፍንበታል:: ከዚህና መሰል ተያያዥ ምክንያቶች አንጻር የአጋንንትን ቃል በተለይ ያለ ጥንቃቄና የደረጀ ዕውቀት የሚሰሙ ሰዎችን ወደሌላ ጥፋት እንዳይመራቸው ሲባል፥ መናፍስት እውነትን ቢመሰክሩ እንኳ አትቀበሏቸው ተብሎአል:: መልካም!
8.0K views14:25
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-30 15:47:23
ተሰውረሽ የሰወርሽን ሆይ: አንቺ ኢትዮጲያይቱ ሆይ: እስቲ ክንብንብሽን አውርጂ፤ እስቲ ዓይነ ርግብሽን ግለጪ:: ከልባችን ማድጋ የፈሰሰው ውኃሽ የሚነደውን ቀርቶ ሊነድ ያሰበን ሳይተው ያጠፋል እኮን:: ብትረቂባቸው ጊዜ: የሌለሽ የመሰላቸው እነርሱ ያሉ ያሉ መሰላቸውና መኖሪያ ነፈጉሽ፤ ማደሪያ ከለከሉሽ፤ መጠጊያ አሳጡሸ:: ግና ከሚታየው ሲያሳድዱሽ: ከሚዳሰሰው ሲያርቁሽ: ከመጽሐፉ፣ ከባሕሉ፣ ከአነዋወሩ ሲያባርሩሽ: ይባስ ከደማችን ተሸሸግሽና ላትለዪ ተዋሕድሽባቸው:: አስተሳሰብ ሆንሽና ባለመጥፋት ጸናሽባቸው:: የቀደመው አባት የተከተለሽ እናት ሆይ: እስቲ ከኛ ከተዋረዱት ሳለሽ ከፍታሽን ተናገሪ፤ እስቲ በተወነካከረ ድምፃችን ዝምታሽን ስበሪ:: ነገሩስ አንቺ መቼ ዝም አልሽ?.. ዝም ማለት አቅቶን ዝም ብለሽ የምታወሪን አልደመጥ አለን እንጂ::

@bemaleda_neku
9.5K views12:47
ክፈት / አስተያየት ይስጡ