Get Mystery Box with random crypto!

የአጋንንት ምስክርነት ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም ? አንድ ሰው ከፍቅር ልዕልና ሲደርስ ሁ | በማለዳ ንቁ !

የአጋንንት ምስክርነት ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም ?

አንድ ሰው ከፍቅር ልዕልና ሲደርስ ሁሉን አስተካክሎ እንደሚወድ መንፈሳዊ አባቶች ይናገራሉ:: የከበሩ መልእክቶችን የጻፈ ሐዋሪያ ጳውሎስም ፍቅር ከእምነትና ከተስፋ ትበልጣለች ይላል:: (1ኛ ቆሮ. ፲፫፥፲፫) እንደውም መብለጥ ብቻ ሳይሆን፥ ያለ ፍቅር ተራራ የሚያፈልስ ታላቅ እምነት እንኳ ቢሆን ከንቱ እንደሆነ ጨምሮ ተናግሮአል:: (ቁ. ፪)

ነገርን ከዚህ መጀመሬ በምክንያት ነው:: ይኸውም የምንም ነገር መነሻችን ፍቅር እንዲሆን ከማሰብ ነው:: በክርስትናው ዓለምማ (በተለይ በሐዲስ ዘመን) የነገራት ሁሉ ፍጻሜ ፍቅር ነው:: እንዲህም መባሉ ስለ ሁለት ነገሮች እንደሆነ ይረዳኛል:: አንደኛ ሥርዓትም እንበለው፣ ትእዛዝም እንበለው፣ ትምህርትም እንበለው፣ ትሩፋትም እንበለው.. መደምደሚያ አድራሻቸው ከፍቅር ከተማ ሊሆን ግድ ይላቸዋል:: ባልንጀራን እንደ ራስ ወደ መውደድ የማያመራ የትኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ጉዞ መጽሐፍ እንደሚለው ነፋስን እንደመከተል ያለ ከንቱ ነው:: (መክ. ፩፥፲፬) ወደየትም አያደርስም:: ማረፊያ ወደብ የለውም:: የትኛውም ዓይነት ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ጸጋ፣.. ሰውን ከማፍቀር ደጃፍ ካላደረሰ ከእግዚአብሔር አልተነሣም ማለት ነው:: ከእግዚአብሔር የተሰጠ ለሰው ወደ መስጠት ይሄዳል:: የወንጌል ሕግጋት በአብዛኛው መስጠትን ማዕከል ያደረጉ ትእዛዛት ላይ የሚያተኩሩት ስለዚህ ነው::

በሁለተኛው ደግሞ ሕግን የሚያስፈፅመው ፍቅር እንደሆነ ቃሉ እንደሚያሳስብ አምናለሁ:: ለምንወደው ማንኛውም ነገር ሆነ አካል፥ ጊዜ፣ ዋጋና ጉልበት በፍላጎት መሠዋት እንችላለን:: ባከፋናት ክፉ ዓለም ሰንኖር መልካሞቹን ሕግጋት መጠበቅ ከባድና ፈታኝ ቢሆንም በፍቅር ኃይል ግን ከባዶቹ ይቀላሉ፥ ፈተናዎች ይታለፋሉ፥ ስንፍናዎች ይሰንፋሉ:: ክርስቶስ "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል" ሲል የተናገረን ይህን ስለሚያውቅ ነው:: (ዮሐ. ፲፬፥፳፫)

ከርእስ እንዳልርቅ በአጭሩ፥ የምንነጋገረውንና የምናደርገውን ሁሉ በፍቅር ስለፍቅር እንድናደርገው ሁላችንን እለምናለሁ:: አለበዚያ እንደተባለው ወደየትም አንደርስም:: ተመልሰን እዛው ነን:: የዚህም ጽሑፍ መነሻም ሆነ መዳረሻ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደማወቅ ጥግ እንዲደርሱ ታስቦ ስለመዘጋጀቱ አንባቢዎች ያስቡ ዘንድ እማልዳለሁ:: (፩ኛ ጢሞ.፪፥፫-፬) አሁን ወደ ርእሰ ጥያቄው እንሂድ::

ክፉ መናፍስት አማንያን እንደሆኑ ያዕቆብ ይነግረናል:: (ያዕ. ፪፥፲፱) ካመኑ ይመሰክራሉም ማለት ነው:: ታዲያ አጨቃጫቂ የሆነው ይህ ምስክርነት ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም? የሚለው ጥያቄ ነው:: አለው የሚሉ ወገኖች አሉ፥ የለውም የሚሉ ጎራዎችም አሉ (እነዚህ ወገኖች (ምእመናኑ) አሳብን በፍቅር መቀባበል ተስኗቸው ክፉኛ ሲጣሉና ሲበጫጨቁ አያለሁ፤ ሁለቱም ተሳስተዋል! ፍቅር ከሌለ ምንም የለምን ዘንግተዋል):: እኔ ደግሞ የምለው አለውም ሆነ የለውም ለማለት እንዲሁ አይቻልም ነው:: እንዴትነቱን እንደሚከተለው ላብራራ::

ወንጌልን የሚያጠኑ የሃይማኖት ሰዎች የማርቆስን ወንጌል የፈውስ መጽሐፍ ሲሉ ይለዩታል:: ምክንያቱም ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ያደረጋቸው ፈውሶች በብዛት ተነሥተውበታልና ነው:: ከነዚህም ውስጥ አጋንንት ከሰዎች ላይ ሲያስወጣ የሚያትቱ ክፍሎች ገና ከመነሻው ምዕራፍ ጀምሮ በተደጋጋሚ ተጠቅሰዋል:: ጥቅሶቹን ስናነብ እንደምናገኘውም፥ መናፍስቱ ጌታን ባዩት ጊዜ አውቀውት ኖረው ክብሩን ሊመሰክሩ ሲሞክሩ ዝም እንዲሉ ያዝዛቸዋል:: (ማር. ፩፥፳፭ ፤ ፴፬ ፤ ፫፥፲፪) በግብረ ሐዋሪያት ላይም የምዋርት መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት እነጳውሎስን እየተከተለች ስለ እውነት አገልጋይነታቸው ስትናገር ጳውሎስ ዘወር ብሎ ርኩሱን ገሥፆ እንዳስወጣው ተጽፎአል:: (ሐዋ. ፲፮፥፲፯-፲፰)

እነዚህን ጥቅሶች ስንመለከት ክርስቶስና ደቀመዛሙርቱ የመናፍስቱን አንደበት ዝም እንዳሰኙ እናነባለን:: የዚህንም ምክንያት በክርስቶስ ስናየው: ሚሥጢር ከመጠበቅ አንጻር ምስክርነታቸውን እንደከለከላቸው ወንጌል "እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው" በማለቱ ይታወቃል:: 'ጊዜው ሳይደርስ የጌታን ማንነት አውጀው መለኮቱን በሥጋ ድካም ለሰወረበት ለማዳኑ ዓላማ ዕንቅፋት እንዳይሆኑ ከለከላቸው' ነው ማርቆስ የሚለን:: በሐዋሪያት ስናየው ደግሞ: የጳውሎስ ግሣፄ "ዲያቢሎስ የእውነት ቅንጣት እንኳ የለውምና፥ እውነትን ቢያወራት እንኳ አትቀበሉት" ለማለት እንደሆነ መምህሮች ያስተምራሉ:: ለዚህም ዋቢነት ዮሐንስ "እውነትም በእርሱ (በዲያቢሎስ) ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና" ሲል የጻፈውን ይጠቅሳሉ:: (ዮሐ. ፰፥፵፬)

ዲያቢሎስ ውሸት የተፈጥሮው እስከትሆን ድረስ ጠባዩ አድርጓታል:: ከራሱ ሲናገር ከሐሰት በቀር አይናገርም:: እውነትንም ቢናገር ሐሰትን እንድትደግፍ አድርጎ ይሆናል:: ማለትም ሐሰትን ለማሥረጽ የእውነትን ተቀባይነት ይጠቀማል:: በእውነት ስም ታዳኞቹን ያጠምዳል:: በሂደቱም እውነትን በዓላማው መጀመሪያና መካከል ላይ ሊያወራት ይችላል:: ሐሳዌ መሢሕ፣ ነቢያት፣.. እየተባለ የሚገለጸውም ይኸው ነገር ነው:: በፍጻሜው ግን ሐሰቱን ያነግሣታል::

ስለዚህ እውነትን ቢናገር እንኳ አትስሙት የሚባለው ከዚህ አንጻር ነው:: እውነትን ተገዶ ቢያወራት እንኳ ሐሰትን በምትጠቅምበት መንገድ ሊናገራት የሚችለውን ያህል ይጥራል:: ለምሳሌ የመተት መንፈስ በእግዚአብሔር ኃይል በተያዘ ጊዜ እንዴት እንደመጣ፣ ለምን እንደመጣ፣ ከማን እንደመጣ ሳይወድ ሊለፈልፍ ይችላል (ይሄ የውጊያውን ዓለም በሚኖሩት ብቻ የሚታወቅ ሲሆን፥ መንፈሳዊ ትግሉን እንዲሁ ለሚነቅፉት የማይብራራ የሕይወት ጉዳይ ነው (እናብራራውም ብንል አይበራላቸውምና)):: ታዲያ መንፈሱ ሲናገር፥ እንደ ከሳሽነቱ እውነትን በመጠቀም ለእርሱ መልካም የሚሆንለትን አነጋገር በመከተል የመታቾቹን (መንፈስ ላኪዎቹን) መጥፎነትና ጥላቻ አጉልቶና አደንድኖ ለተመታቹ (መንፈስ ለተላከበት ግለሰብ) በመግለጽ፥ ተመታቹ በሰማው መረጃ ምክንያትነት በመታቾቹ ላይ ማንኛውም ዓይነት ክፉ ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል (ከውስጡ ይገፋፋዋል):: ሰልፋችን ከመንፈሳዊያን ሠራዊት ጋር ነው የሚለውን ወሳኝ የወንጌል መልእክት ሰማዒው ካላወቀ፥ ጠላቱ ሰው እንደሆነ ይደሰኩረዋል፤ ካወቀ ደግሞ ይሸፍንበታል:: ከዚህና መሰል ተያያዥ ምክንያቶች አንጻር የአጋንንትን ቃል በተለይ ያለ ጥንቃቄና የደረጀ ዕውቀት የሚሰሙ ሰዎችን ወደሌላ ጥፋት እንዳይመራቸው ሲባል፥ መናፍስት እውነትን ቢመሰክሩ እንኳ አትቀበሏቸው ተብሎአል:: መልካም!