Get Mystery Box with random crypto!

የአንድ ሰው ጥያቄ ፦ ለምንድነው እግዚአብሔር ግን ራሱን የማይገልጥልን? ተገልጦ ቢያሳውቀን እ | በማለዳ ንቁ !

የአንድ ሰው ጥያቄ ፦ ለምንድነው እግዚአብሔር ግን ራሱን የማይገልጥልን? ተገልጦ ቢያሳውቀን እኮ የምናያቸው ሁሉ እንደምናያቸው አይሆኑም ነበር:: ስለምን ነው ለሁሉም ሰዎች ሁሉን ግልጥልጥ የማያደርግላቸው?

የአንድ ሰው መልስ ፦ የትኛው ንባብ ላይ እንደሚገኝ አሁን የማላስታውሰው መልካም ቃል "የሰው ኅሊና ወደ ደግ ነገር ሳትሳብ የእግዚአብሔር ጸጋ ሰውን አትረዳውም" ይላል:: አብርሃም አምላክን የገለጠበትን ታሪክ ሲያስረዱ ነው ይህንን ያሉት:: ዝርዝሩን ወደኋላ እናመጣዋለን:: እንግዲህ የማምነውን ዕውቀት ነው የምነግርህ:: ..እግዚአብሔር በየዕለቱ ራሱን ለሰው ልጆች ይገልጣል:: መገለጡ ያልተገለጠልን ለኛ ነው:: በምሳሌ ላስረዳህ:: ፀሐይ ወጥታ ሳለ በጨለማ ቤቱ ተክትቶ ያለ ሰው ፀሐይ የለችም ቢል: እውነቱ አለማየቱ እንጂ የፀሐይ አለመውጣቷ አይደለም:: ብርሃኗን ሊያይ ከወደደ ቢያንስ መስኮቱን መክፈት አለበት:: የአንተ ጥያቄ አንድ በመጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈ ባለጠጋ ሲጠየቅ አንብቤያለሁ:: እስቲ ሉቃስ 16'ን ተመልከተው:: [1] ኑሮ ደስ ያለው ሐብታም ሰውና በድህነት፣ ሳይበቃው በቁስልም የሚሠቃይ ሰው ታሪክ ታገኛለህ:: ያው ሞት አይቀርምና ሁለቱም ከዚች ዓለም አረፉ (በርግጥ አልዓዛር የሚባለው፣ ደሃው ነው ያረፈው):: ነገሩን ላሳጥረውና ሐብታሙ ወደ ሲዖል የተቸገረው ወደ ሕፀነ አብርሃም በነፍሳቸው ሄዱ:: ባለጠጋው የወኅኒ ቤት መከራ ሲጸናበት እዛው ሆኖ ጸለየ አሉ:: ረፍዷል ተባለ:: እሺ ቢያንስ ቤተሰቦቼን እንደኔ እንዳይዘገዩ አስጠንቅቁልኝ አለ፤ ሙሴና (ሕግ) ነቢያት (ትምህርት) አሏቸው እነርሱን ይስሙ የሚል መልስ ተሰጠው:: አይደለም፥ ሙታን ተነሥተው ቢመክሩልኝ ይሻላል አለ (የጨነቀው!):: ሙሴና ነብዮቹን ካላደመጡ ሙታኑን አይሰሙም ተብሎም ቁርጡ ተነገረው:: ልብ ካልክልኝ የመጨረሻይቱ ቃሉ ያንተ የጥያቄ ሐሳብ ነው:: የሙታን ትንሣኤ ይመስክርልኝ ያስባለው ከቃል የተሻለን መገለጥ ሲመርጥ እንደሆነ አስተውልሃል? ትምህርት አይጨበጥማ:: የትምህርት መገለጥ ለዓይን አይደለም፤ ለልብ ነው:: ቤተሰዎቹ ዓይን እንጂ ልብ እንደሌላቸው ያውቃል ማለት ነው:: ..እግዚአብሔር የመጨረሻውና ፍጹሙ ደግ ባሕርይ ነው:: ዘመናትን አላንዳች ምልክት አይተዋቸውም:: ሰዎችን እንዳሉበት ልዕልና ማናገሩን ለደቂቃ አልተወም:: ለምሳሌ አንተ ከቤት ወጥተህ እስክትመለስ ምን ያህል በጎ ሰዓታትን አሳለፍክ? በእርምጃዎችህ ገለል ብለህ ያለፍካቸው አልዓዛሮች የሉም? ምናልባት ደምቆ የተጻፈ ጽሑፍ እያነበብህ አላየኻቸው ይሆናል:: በዓይንህ ብቻ የምታይ ከሆነ: የሕንፃ ቀለም በመንገድ ከተኮራመቱ ወገኖች በላይ ትኩረት ይወስድብሃል:: 'ነርቩ' ከልቡ'ጋ ያልተገናኘለት ብሌን ከውበት አስተርፎ ሊመለከት አይችልም:: ይህንን ነው የሰው ኅሊና ለደግነት ሳትሳብ የእግዚአብሔር ጸጋ ሰውን አትስበውም የሚሉህ:: ለባለጠጋው ሰውየ ረፍዶብሃል የሚለው አብርሃም ነበረ:: እርሱ ከአባቱ ቤት ሳለ የቀዬውን ጣዖት ይቀርጽ ነበር አሉ:: [2] የኋላ የኋላ በእጁ የሠራው ሥራ እኔንም ሠርቶኛል ብሎ መቀበል ስላቅ ሆነበት:: አፍንጫውን የማረዝም የማሳጥርለት ይሄ እንዴት አፍንጫዬን ቀረጸልኝ? ሲል ተመራመረው:: አሁንም ልብ በል! ይሄን የአብርሃምን ጥያቄ ሌሎቹ እንዳይጠይቁ አልታፈኑም:: ግን እርሱ ብቻ ጠየቀ:: በሌላ አባባል እርሱ ብቻ መስኮት ከፈተ:: ስለዚህ የከፈተውን ያህል ብርሃን አየ:: ኅሊናው ጣዖቱን ናቀበት:: ተውም ቢለው በጄ አላለለትም:: በቃ ይሄ እኮ ነው መገለጥ ማለት! እንዳልኩህ እግዚአብሔር በየቀኑ የሚከፍትልን አንድ የሆነ በር አለ:: ይሄ ግን የሚገባን ልቡናችንን ስንከፍት ነው:: ይኸውም ጥልቅ ፍላጎት ነው:: አብርሃም ጣዖቱን ሰበረው:: በእጁ የሰበረው በኅሊናው ከሰበረው በኋላ እንደሆነ ያዝልኝ:: ስለዚህ ጸጋ እግዚአብሔር በልቡናው አድራ እርሱን ወደ መፈለግ መራችው:: ፍለጋውን ጀመረ:: ከግዙፉ ተራራ ጀመረ:: ሌላ የገዘፈ ተራራ ተመለከተና የቀደመ ሐሳቡን ተወው:: ወደ ባሕር ቀጠለ:: እያንዳንዱ እያነሳ የሚጥለው ፍጥረት ወደ ፈጣሪ ያስጠጋው ነበረ:: አግኝተኸኝ ከሆነ: አብርሃም የአምላክን መኖር ነበር የፈለገው:: አለመኖሩን ቢፈልግ ኖሮ የፍለጋ ውጤቶቹ ጉዞውን ለማቋረጥ በቂ ምክንያቶች ነበሩ:: ለካ ጽኑ ፍላጎት አለመሳካትን ሂደት እንጂ ገደብ አያደርገውም:: በጣም ለምትሻው ነገር አለመመቸትን ጆሮ ዳባ ልበስ ትለዋለህ:: ነጮቹ ስለዚህ 'ፍላጎት እኮ ኃይል ነው' ይላሉ:: ቅን ፍላጎት ወደ አምላክ የሚመራ መንገድ ነው:: አብርሃምን: በእያንዳንዱ የፍላጎት እርምጃዎቹ በኩል ጌታ ይቀርበው ነበር:: ይህን የምታውቀው የአብርሃም አፈላለጉ እየረቀቀ መሄዱን ካጤንክ ነው:: ከሚታዩት ወደ ማይታዩት እየረቀቀ ሄዷል:: ብርሃን፣ ነፋስ፣.. እያለ ወደማይጨበጡት ፍለጋው ተጉዟል:: ቅን ፍላጎት ወደ አምላክ ትወስዳለች:: እርሱም'ኮ ፈልጉ ታገኙማላችሁ ብሏል:: [3] ፈልጉ ሲል እኔንም ፈልጉኝ ይጨምራል:: ከፍላጎት ትይዩ ታገኛላችሁ ደሞ ካለ: እናገኘው ዘንድ አስቀድሞ ያኖረው አንዳች ነገር አለ ማለት ነው:: ሳይንስ አፈላለጉ ጥሩ ነው:: አነሳሱ ግን አይደለምና ከባክቴርያ የሚረ'ቀው 'አተም' ነው አለ:: በመሠረቱ አንድን ነገር በዓይንህ ካየኸው አልረቀቀም ማለት ነው:: እና በሥጋ ለሚታዩህ እምብዛም አትደከም ወንድሜ:: ጳውሎስ የሚባል ሰው "የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ" እያለ ይናገራል:: [4] "የማይታየው.. ይታያልና.. ነገር ግን.. ልቡናቸው ጨለመ" ያላቸውን አሰናስለህ አስተውልልኝ:: ልብ ነው ከነፋስ የሚረቀውን የሚያየው:: እርሱ ከታወረ የማይታየው ባለመታየቱ ይቀጥላል:: ወዳጄ "አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና":: [5] .. በል ሰንብትልኝ!

[1] ሉቃ. 16፥19-31
[2] ኦሪት ዘልደት ም. 12 አንድምታ
[3] ማቴ. 7፥7
[4] ሮሜ. 1፥20-21
[5] ምሳ. 4፥23


( ለአቀራረብ የተሞረደ እውነተኛ ቃለ ምልልስ )

@bemaleda_neku