2022-10-07 08:48:21
አሳዛኙ የራሕዋ ገብረዋሕድ ደብዳቤ
(ቆቦ፣ ደጋ በላጎ ከኪሷ ከተገኘ)
" ከታጋይ ራሕዋ( ሚጡ) ለመላ ቤተሰቤ፦
በመጀመሪያ ለተከበራችሁት ለምወዳችሁ ወላጆቼ ፣ ወንድም እኅቶቼና ቤተሰቦቸ ሆይ ! ይቺ ምትክ (አቻ) የማይገኝላት የእግዚአብሔር ፀጋ ለሆነዉ ጤናችሁ እንደምን አላችሁ? ለማለት እወዳለሁ። ደኅና እንደምትሆኑ ደግሞ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።
- እኔ ግን ናፍቆታችሁ እንደ ዉኃ ይጠማኛል፤ እንደ እንጀራ ይርበኛል፤ እንደሰማይ ርቆኝ መቻል አቅቶኛል። ግን እችለዋለሁ። የማይቻል የለም። ኹሉንም ለፈጣሪ ሰጥቼዋለሁ። ጸሎቴንም አላቋረጥኩም። ኹሉም የእግዚአብሔር ፈቃድ እስከሆነ ድረስ የሚበልጠዉ በተስፋ መኖር ነዉ ብዬ ነዉ እማምነዉ።
-በተለይ ያቺ ሩሕሩሕ ፣የዋህ የሆነቺዉና ነፍሴን አሳልፌ የምሰጣት፣ ከሌሎች እናቶች ጋር የማላወዳድራት እናቴ (ኣብረኸትዬ ) የኔ ማር የሆንሽዉ አንድ ቀን እንኳ እፎይ ሳትይ ከችግር ወደ ችግር የሆነዉ ህይወትሽ እንዴት ኾኖ ይኾን ? አብረኸትዬ ዘወትር ባንቺ የተነሳ ሳስብና ስጨነቅ እዉላለሁ። አላረፍኩም።
በተለይ የኔን እገዛ በሚያስፈልግሽ ጊዜ አላገዝኩሽም። ከሁሉም በላይ ደጋፊ የሌለዉን ቤታችንን በህመም ምክንያት ሳልነግርሽ ትቸሽ ሄድኩ። ምክንያቱም ከፊቴ ስታለቅሺ ማየት አልፈለኩም። ከወንድሜ ከገ/ሕይወት ይልቅ እኔ እዘምታለሁ ብዬ ወስኛለሁ። ምክንያቱም እኔ ከማግዛችሁ ይልቅ እሱ የሚያግዛችሁ ስለሚበልጥ ነዉ። አትቅየሙኝ። አብረኸትዬ በኔም የተነሳ አታስቢ (አትጨናነቂ)። ደኅና ነኝ። አሁን በህልሜም በእዉኔም እየመጣ ከአቅሜ በላይ ሆኖ የሚያስቸግረኝ ጉዳይ የመልከኛዉ፣ ምሑሩ እና ልባሙ ወንድሜ የሃለቃ በርሄ ጉዳይ ነዉ።
ከቀናት በፊት መጥፎ ህልም አይሉት ቅዠት አየሁ። እዉነትም መሰለኝ። ከወንድሜ በርሄ ጋር የተያያዘ መስሎኝ ከእንቅልፌ ብድርግ ብዬ ተነስቼ ማልቀስ ስጀምር ጓደኞቼ "ምን ሆነሽ ነዉ?" ብለዉ ጠየቁኝ። እኔም ያስጨነቀኝን ቅዠት ነገርኳቸዉ። እነሱም ህልሙ ጥሩ መሆኑን ነግረዉ አፅናኑኝ። እኔም ኹሉንም ለበጎ ያድርገዉ ብዬ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ነገርኳት።
በርሄ ወንድሜ ጤናህ እንዴት ነዉ ? እንደቀድሞዉ መለስ አላለልህም? ከቤተሰቦችህ ጋር ቤተክርስቲያን እያገለገልክ ነዉ? ከጓደኞችህ ጋር እየተጫወትክ እንደማገኝህ በጉጉት እጠብቃለሁ።
በርሄ ወንድሜ በዚህ እገዛ በሚያስፈልገኝ ጊዜ ትታኝ ሄደች ብለህ አደራ እንዳታዝንብኝ (እንዳትቀየመኝ) ! የኔ ማር ይቅርታ እየጠየኩህ ነዉ። ጊዜዉ ሲደርስ ደግሞ እክስሃለሁ። ሰላም ነዉ ያለኹት እንገናኛለን።
-ባባ (ገ/ዋሕድ ብርሃኔ) (ሣሙና) )፣ ወንድሜ ገ/ሕይወት ፣ እኅቴ ትርሓስ ፣ ማኅደር ፣ ዳናይት ፣ ዳንኤል (ፀጋዬ)፣ ወንድሜ አሉላ ፣ ወንድሜ ቢኒያም እስከምንገናኝ ኹላችሁንም ሰላም ሰላም ብያለሁ።
ለመገናኘት ደግሞ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልካም ፈቃድ ነዉና ስለኔ አትጨነቁ:: በተጨማሪም ለኹሉም ጎረቤት ሰላም በሉልኝ።
- ለእናቴ (አብሻይ)፣ አረጋዊ ፣ ጨርቆስ ፣ ማርቆስ ብቻ ኹሉንም ሰላም በሉልኝ።
- ያዬ (ብርሃነ ግደይ) ሥ ደኅና ነዉ? እያረጀ ነዉ እንዴ? ምግበይሥ እንደምን ነዉ ? ዳንኤል ገ/ሄርንም ሰላም በሉልኝ። የሹስ ተሻላት ወይ ? ሰላም በሉልኝ:: በተጨማሪም ለኹሉም ቤተሰብ ሰላም በሉልኝ። ቻዎ ፣ ቻዎ !!
[ከድብዳቤዉ ራስጌ ላይ ሰረዝ ደለዝ ተደርጎ የተጻፈው ደግሞ እንደሚከተለው ይላል።]
" አንድ ነገር የረሳኹት፣ ምጣዱን ነዉ:: ይኸዉም አዬር ቤት ዉስጥ ተከራይቼ ከነበርኩበት ቤት ነዉ ትቸዉ የመጣሁት ( ያለዉ) :: ቦታ እንዳይዝባቸዉ እስከዛዉ እነሳራ ይጠቀሙበት፤ ወይም ደግሞ ማርቆስ ቤት አድርግልኝ:: ብር ከጠየቁ ደግሞ መሸጫ ዋጋዉ 2,000.00 ብር ነዉ::"
ቤተሰቦቼ ከልብ የመነጨ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ :: እና እኔ አኹን ያለሁበት ቦታ ራያ -ጨርጨር የሚባል ቦታ ኾኖ
አርሚ -44
ኮር -441(1)
ሬጅመንት (ሻለቃ)-3
ኃይል - 4
ደጀና ክፍለ ሠራዊት ነዉ !!
ትግራይ ትስዕር !!!"
*ማስታወሻ፦ ራሕዋ ወንድሟን ተክታ ለትሕነግ ወታደር የነበረች ሴት ናት። ይህ ደብዳቤ የተገኘው ከኪሷ ነው። አስከሬኗም የተገኘው ቆቦ፣ በላጎ ነው። ደብዳቤው የትሕነግን እብደት፣ የትግራይ ልጆችን ያሉበትን ሁኔታ፣ የትግራይ እናቶችን ስቃይና ዋይታ ያሳያል በሚል ነው ተርጉሞ የቀረበው።( Wubshet Mulat)
ለፈጣን መረጃ የቻናሌ ቤተሰብ ይሁኑ
http://t.me/ayuzehabeshaofficial
17.6K viewsAyu, edited 05:48