Get Mystery Box with random crypto!

በመዲናዋ የሰራተኛ ምደባን በመቃወም ስራ ያልገቡ ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ | Ayu Zehabesha-Official (አዩ ዘሀበሻ)

በመዲናዋ የሰራተኛ ምደባን በመቃወም ስራ ያልገቡ ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተደረገውን የመንግስት ሰራተኞች ምዘና ተከትሎ የተከናወነውን የሰራተኛ ምደባ በመቃወምና በሌሎች ግላዊ የጥቅም ጥያቄዎች ምክንያት ስራ ያልገቡ ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ የከተማው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ቢሮ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሰራተኞች ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት የስራ ድልድል መደረጉንና ሰራተኞች በተቻለ መጠን በሚኖሩበት ወረዳ እና ክፍለ ከተማ አካባቢ እንዲመደቡ መደረጉን የከተማዋ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ቢሮ የስራ አመራር ዘርፍ ሀላፊ አቶ መላኩ ጉራቻ ተናግረዋል፡

ምደባው ከተከናወነ በኋላ በሁሉም ክፍለ ከተማ አገልግሎቶች ሳይቋረጡ እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በዚህ ሁኔታ ግን መመሪያውን በመቃወም እና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ስራ ገበታቸው ያልተመለሱ ሰራተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁንም በምደባው ላይ ቅሬታ እየቀረበ በመሆኑ ወደ ስራ ገበታቸው ያልተመለሱ ሰራተኞችን ሙሉ ቁጥር አሁን ላይ ማወቅ እንደማይቻል አመላክተዋል፡፡

በስራ ምደባው 3ሺ 266 ሰራተኞች ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ ሳይደረጉ፤ ወደ ሌላ ቦታ በማዘዋወር መመደባቸውን ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡
@ayuzehabeshaofficial