2024-05-21 23:17:23
ግንኙነቶች (RELATIONSHIPS)
ሰዎችን ለመገምገምና የመሰለንን ማንነት ለመስጠት ምን ያህል ፈጣኖች ነን! ለሌሎች የራሳችንን የፈጠራ ማንነት ስንሰጣቸውና ስንሰይማቸው ኢጐአችን
ይደሰታል።
እያንዳንዱ የሰው ልጅ እንደዚያ እንዲያስብና እንዲያምን በሁኔታዎች ተቃኝቷል (conditioned) ሆኗል። ኹሉም ሰው በውልደት ፣ ወይም በልጅነት ገጠመኝ እንዲሁም ባደገበት ባህላዊ መስተጋብር ተቃኝቶ እንደዚያ ለማሰብና ለማመን ይገደዳል።
ይህ ቅኝታቸው ነው እንጂ ማንነታቸው አይደለም። ለሰዎች ስም ስንሰጥና እንዲህ ናቸው ብለን ስንበይን ማንነታቸውን ከሁኔታዊ ቅኝታቸው ጋር አደናግረናል ማለት ነው። ለሰዎች ሃሰተኛ ማንነት ስንሰጣቸው እኛ የፈጠርነው ማንነት ለእነርሱም ሆነ ለእኛ እስር ቤት ይሆንብናል።
በሰዎች ላይ መፍረድ ማቆም ማለት እነርሱ የማያደርጉትን አለማየት ማለት አይደለም። ባሕርያቸውን እንዳለ መቀበልና ማንነታቸው ሳይሆን የተቃኙበት (conditioning) ሁኔታ መሆኑን መገንዘብ መቻል ማለት ነው። ለዚያ ሰው ማንነት ከመፍጠርም መታቀብ ማለት ነው።
ይህንን ማድረግ ስትጀምሩ ሰዎችን በቅኝታቸው፣ በአካላቸውና በአእምሮ እይታችሁ መሰየም ታቆማላችሁ። የዚያኔ ግንኙነታችሁ በኢጐ ከመመራት ነፃ ይወጣል።
ኢጐ ሕይወታችሁን እየመራው ከሆነ ሃሳብ ፣ ስሜትና ድርጊታችሁ በሙሉ ከፍርሀትና ከምኞት ይመነጫሉ። በመሆኑም ከሌሎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት እነርሱን በመፍራት ወይም ከእነርሱ ነገሮችን በመፈለግ ይመሠረታል።
ከግንኙነት አጋራችሁ የምትፈልጉት ደስታ ፣ ቁሳቁስ ፣ ክብር ፣ ትኩረት ወይም ለራሳችሁ ያላችሁን አመለካከት ለማጉላት እነርሱን እንደ ማነፃፀሪያ መጠቀም ሊሆን ይችላል። እናንተ ከእነርሱ የተሻላችሁ መሆናችሁን ለማሳየት የግድ እነርሱን ልትፈልጉ ትችላላችሁ። የምትፈሩት ነገር ደግሞ ነገሮች ከፈለጋችሁት ተቃራኒ ሊሆኑ ከቻሉ የሚፈጠርባችሁን የበታችነት ስሜት ሊሆን ይችላል።
ሙሉ ትኩረታችሁን አሁናዊ ቅጽበት ላይ ስታደርጉ ከኢጐ ባሻገር የሆነ እይታ ይኖራችኋል። አሁናዊ ቅጽበትን እንደመጠቀሚያ ማየት ታቆማላችሁ። የዚያኔ ራሳችሁን ከሌሎች ጋር በማነፃፀር ከፍ ማድረጋችሁ ያበቃል። ከምትገናኙት ሰው ጋር ሳላችሁ ሙሉ ትኩረታችሁን ለእነርሱ ስጡ። የዚያኔ የእነርሱ ያለፈና የወደፊት ታሪክ ወይም እናንተ የሰጣችኋቸው መለያ ማንነት ይወገዳል። ከኢጐ ፣ ከፍላጐትና ከፍርሀት የተላቀቀ እይታ ይኖራችኋል። ስለዚህም ትኩረት ወይም ንቁ የሆነ ፀጥታ (alert stillness) ወሳኝ ቁልፍ ነው።
ነገሮችን መፈለግና መፍራት የሌለበት ነፃ ግንኙነት ምን ያህል አስደናቂ ሊሆን እንደሚችል አስቡ። ፍቅር ምንም ነገር አይፈልግም ፤ በምንም አይፈራምም።
የእርሷ ያለፈ ገጠመኝ ያንተም ቢሆን ፤ ሕመሟ ሕመምህ ቢሆን ፤ የነበራት የማስተዋል ደረጃ ያንተም ቢሆን አንተም እርሷ ያደረገችውን ታደርግ ነበር። ይህንን ሃቅ በመረዳት ብቻ ርኅራኄ ፣ ይቅርታና ሰላምን ወደ ግንኙነታችሁ ማስገባት ትችላላችሁ።
የቀረቧችሁን ሰዎች በሙሉ፤ ወደ አሁናዊ ስፍራችሁ የሚገቡትን ኹሉ እንደተከበረ እንግዳ መቀበልና በማንነታቸው ማየት ስትጀምር እነርሱም መቀየር ይጀምራሉ።
አንድን ሰው በሰውነቱ ለማወቅ ስለ እርሱ ያለፈ ታሪክ ፣ የነበረበት ሁኔታና የመሳሰለውን ነገር አያስፈልጋችሁም። ብዙ ጊዜ ሰዎችን ማወቅ ስለእነርሱ ማወቅ ይመስለናል። ይሁንና ማወቅና ስለእነርሱ ማወቅ የተለያዩ ናቸው። አንዱ የሚታይን ነገር ማወቅ ሲሆን ሌላው ግን ከሃሳባችን ባሻገር በፍፁም ፀጥታ
እነርሱን ማወቅ ነው።
ለዕለታዊ ጉዳዮች እንደሆንን ስለሰዎች ማወቅ ጠቃሚ ነው። ይሁንና ስለእነርሱ ማወቅን ወደ ግል ግንኙነታችን ስናመጣው አስቸጋሪ ይሆናል። የሰዎች ታሪክ የግንኙነት እንቅፋትና አጥር ይሆናል። እውነተኛውን ሰብአዊ ማንነት ከማየትም ይጋርደናል። ስለዚህ ከሌሎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በአጥር የተለየ መሆን የለበትም። የሃሳብ እንቅፋት ከሌለ በኹሉም ሰብአዊ ግንኙነት ላይ ፍቅር
ይነግሳል።
አብዛኛው የሰው ግንኙነት በቃላት ልወውጥ ላይ የተመሠረተ የሃሳብ ዓለም መስተጋብር ነው። ፍፁም ፀጥታን ወደግንኙነት ማምጣት አስፈላጊ ነው። ፀጥታ የሌለበት ግንኙነት ፍሬያማ ሊሆን አይችልም። አብራችሁ በፀጥታ መቀመጥና መመሰጥ ያስፈልጋል።
ፀጥታ እናንተ የምትፈጥሩት ሳይሆን በራሱ ያለ ነገር ነው። ስለዚህ ፀጥታውን ማግኘት ብቻ ይጠበቅባችኋል። ፀጥታን የምታገኙት የአእምሮ ጩኸታችሁ
ሲቋረጥ ነው።
ፀጥታ ከጠፋ ግንኙነታችሁ በጩኸትና የአእምሮ ሁካታ የተሞላ ይሆናል። ችግርና ግጭትም የዘወትር ክስተታችሁ ይሆናል። ፀጥታ በዚያ ስፍራ ሲኖር ግን የትኛውም ችግር ይወገዳል።
እውነተኛ አድማጭነት ፀጥታን ወደ ግንኙነታችን የምናመጣበት ሌላው መንገድ ነው። ሰዎችን የእውነት ስታደምጧቸው የፀጥታ ስፍራ ትፈጥራላችሁ። ይሁን እንጂ የዚህ ዓይነቱ እውነተኛ አድማጭነት በብዛት የለም። ሰዎች በራሳቸው ሃሳብ በመዋጥ የተናጋሪውን ቃላት በመመዘን ፤ ቀጥሎ የሚናገሩትን በማሰብ የእውነት ከማድመጥ ይታጐላሉ። ወይም ደግሞ በራሳቸው ሃሳብ ርቀው በመሄድ ሙሉ በሙሉ የሚነገረውን አያደምጡ ይሆናል።
የእውነት ማድመጥ ማለት አሁናዊ ትኩረት ውስጥ መግባት ማለት ነው። ማድመጡ በራሱ ከሚነገሩት ቃላት በላይ ጠቃሚ ነው። በፍፁም አትኩሮት ስናደምጥ ተናጋሪውን አድማጩ በፀጥታ ስፍራ ይዋሃዳሉ። “ሌሎች” የሚል መነጠል ሳይኖር አንድነት ይሰፍናል።
ምንጭ፦ አሁናዊ ሀይልን ማግኘት
ትርጉም ፦ ሙሉቀን ታሪኩ
@Zephilosophy
@Zephilosophy
5.2K viewsedited 20:17