Get Mystery Box with random crypto!

ሕያውነት (Resurrection) ካለፈው የቀጠለ ክርስቶስ መጥቶ የክርስትናን አስተምህሮና የሰ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ሕያውነት (Resurrection)
ካለፈው የቀጠለ

ክርስቶስ መጥቶ የክርስትናን አስተምህሮና የሰውን ልጅ መንፈሳዊ እሳቤዎች ከቀየረበት አብዮት በፊትም ቢሆን “ስለ ትንሳዔ (ሕያውነት) ምንም ፍልስፍና አልነበረም” ማለት አይቻልም። በግብጽ የኦስሪስ፣ በግሪክ አፈታሪክ የአችሊስና ሄሪኩለስ እንዲሁም በሂንዱኢዝሙ ሳምባዶር እንደ ምሳሌ ሆነው መቅረብ የሚችሉ ናቸው።

ነገር ግን የሕያውነት ወይም ትንሳዔ ፍልስፍና ግልጽ ምስል መሰበክ የጀመረው በክርስቶስ ነው፤ በኋላም በእስልምና ሃይማኖት ተመሳሳይነት ያለው አስተምህሮ ተራምዷል። ይህም አስተምህሮ በምጽአት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ነፍስ ትንሳዔን ያገኛል፤ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሱ ታሪኮች ከሞቱ ኋላ የሚነሱ ሰዎች አሉ —(ክርስቶስ ራሱ እና ክርስቶስ ያስነሳው አላዛር)።

“Resurrection” የሚለው ቃል ከተመሳሳዩ ላቲን ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜው “የሞተ ነገር ወደ ሕይወት ሲመለስ” ማለት ነው። ትንሳዔ ሁለት መገለጫዎች አሉት፤ መንፈሳዊ ትንሳዔና ቁስአካላዊ ትንሳዔ።

በመንፈሳዊ ትንሳዔ ዕይታ ማንኛውም ሰው ዘለዓለማዊት ነፍስ ስላለችው ከሞት ይነሣል፤ ዘለዓለማዊ ፍርዱን ይዞ ኑሮውን ይኖራል። በቁስአካላዊ ትንሳዔ ደግሞ አንድ የሞተ ነገር ተመልሶ ህያው ሲሆን ማለት ነው።

ነገር ግን ቁስአካላዊ ትንሳዔ እንበል እንጂ የነፍስን ረቂቅነት እስከተቀበለ ድረስ የሐሳባዊያን ተቃራኒ የሆነውን ቁስ አካላዊ ፍልስፍና ማለታችን አይደለም።ስለዚህም ሁለቱም ዕይታዎች ተመሳስሎሽ ያለባቸው መሆኑን ልብ ማለት ይቻላል። ነገር ግን አንዳንዶች ደግሞ አይጠፉም፤ “የሰው ልጅ የተሠራው ከቁስ ነው፤ ትንሳዔም ቢኖረው ቁሳዊ ትንሳዔ እንጂ ነፍስ የሚባል የለም” የሚሉ አይጠፉም።

በመካከለኛው ዘመን ፈላስፎች በተለይ በ“ቅዱስ አውጉስቲን”ና “ቅዱስ ቶማስ አኩይናንስ” ይሄ አስተምህሮ ይበልጥ ተስፋፍቶና ፍልስፍናዊ ብያኔዎች እየተሰጡት ሊብራራ ችሏል።

እንደ አኩይናንስ ዕይታ ሞት ለሰው ልጅ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊም ነው፤ መሠረታዊነቱም ዘለዓለማዊ የሆነችው ነፍስ አዲስ ትንሳዔን ታይ ዘንድ ሞት ግድ መሆኑ ነውና ነው። እንዲህም እያለ ይሞግታል፤ —ነፍስ ከሥጋ ውጭ መኖር ይቻላታል፤ ምክንያቱም ነፍስ በሥጋ ውስጥ ትኖራለች እንጂ የሥጋ ጥገኛ አይደለችምና።

ነፍስ በሥጋ ውስጥ ስትኖር ይህን ዓለም መስላ ትኖራለች፤ እናም የሥጋ ጥገኛ መስላ ትታያለች፤ እውነታው ግን “ሥጋ የነፍስ ጥገኛ እንጂ ነፍስ የሥጋ ጥገኛ አይደለችም።” የሚለው የአኩይናንስ ፍልስፍና ነው።

ስለዚህም ይላል አኩይናንስ ነፍስ ከሥጋ ስትነጠል ይህን ዓለም የምታይበት መንገዱ ሌላ የኑሮ ዘይቤዋም ሌላ ይሆናል። የሥጋና ነፍስ መለየት ለነፍስ ውጤቱ፤ አዲስ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ እንደ መብራት ዓይነት እንጂ አምፖል ቢሰበር መብራቱ ድርግም እንደሚለው ዓይነት አይደለም። ይሁንና በትንሳዔ ጊዜ አምፖሉና ኤሌክትሪኩ ይገናኙና ያ ቀዳማዊው ሁነት (ዓለም) እንደገና ይታያል።

አውጉስቲን ደግሞ ነፍስ ኢ-መዋዕቲ መሆን አለባት የሚለውን የፕሌቶን ፍልስፍና አብራራው እንጂ ኢ-መዋዕቲ መሆኗን አይደለም። ነፍስ በተፈጥሮዋ ንጽሕና፣ ብጽዕናና ፍጽምና የሚስማማት ናትና ይላል።

ፕሌቶ “ፍጹም ደስታ የነፍስ ጠባይ ነው” እንዳለው አውጉስቲንም “ለእዚህ እውነተኛና ፍጹም ደስታ ደግሞ ሞት የሚስማማው ባሕርይ አይደለም፤ እናም ነፍስ መዋዕቲ መሆን የለባትም፣ አይደለችምም” ይላል።

ለአውጉስቲን ሞት ሁለት ዓይነቶች (ደረጃዎች) አሉት። የመጀመሪያው አንደኛ ሞት የሚለው የማትሞተው ነፍስ ከሚሞተው ሥጋ ስትለይ ነው። እንዲህ ያለው ሞት የሰው ልጆች ሁሉ ባሕርይ (ዕጣ ፈንታ) የሆነው አዳምና ሄዋን በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ከአባቶቻችን በወረስነው መርገም የተነሣ ነው። “ይህኛው ሞት የአምላክ ቅጣት ነውና በበጎ መታየት አለበት” —ይላል አውጉስቲን። በጎነቱ ግን እንደ ቅጣት እንጂ እንደ ውስጣዊ ስሜት አይደለም። ውስጣዊ ስሜትን ያጤንን እንደሆነ ለበጎው በጎ ለመጥፎው መጥፎ ውጤት ያለው ነው። በውጤቱ መልካም ከሆነ ነፍስን ወደቀጣዩ ጥሩ ሽግግር መግፍኤ ይሆናል።

ለአውጉስቲን ሁለተኛው የሞት ዓይነት ወይም ደረጃ ደግሞ የነፍስ መሞት ነው። እዚህ ላይ “ነፍስ ኢ-መዋዕቲ ናት” ከተባለ በኋላ “የነፍስ መሞት እንዴት ይመጣል?” የሚለው ቁም ነገር መነሣት አለበት። አውጉስቲን እዚህ ጋ የነፍስ ሞት የሚለው እግዚአብሔር ነፍሳችንን በኃጢአታችን ሰበብነት ሲርቃት ነው።

"It falls on us as a result of our own personal sin we commit in our life; and it is characterize by eternal dam- nation of our soul in the purgatory and then, when rejoin with the body, in hell; this death is good to none for it happen to nothing good” —(Augustine, 1908: 3-4).

በእነዚህ ዕይታዎች መሠረትነት በሕያውነት (ትንሳዔ) ለሚያምኑ ሞት ዳግም ዕድል የላትም፤ አንድ ናት፤ ነፍስም አንዴ ዘላለማዊ ሆና ተፈጥራለች እንጂ ድጋሚ የምትፈጠርበት ዳግም ዕድል የላትም።

@Zephilosophy
@Zephilosophy