Get Mystery Box with random crypto!

የሬኒ ዴካርት ፍልስፍናዊ ሃሳቦች ምንጭ ፦ የፍልስፍና ሀሁ ትርጉም ፦ ራሴላስ ጋሻነህ ዴካርት | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

የሬኒ ዴካርት ፍልስፍናዊ ሃሳቦች

ምንጭ ፦ የፍልስፍና ሀሁ
ትርጉም ፦ ራሴላስ ጋሻነህ

ዴካርት ይበልጡን "አስባለሁ፤ ስለዚህ አለሁ” በሚለው አባባሉ ይታወቃል፡፡ ለዴስካሬት የማሰብ ሂደት በራሱ ለግለሰባዊ ህያው መሆን ማረጋገጫ ነው፡፡ እንዲሁም የሰው ልጅ ማሰብና ምክንያት ማቅረብ መቻሉ የሰብአዊነቱ መሰረታዊ ባህሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ህያው ስለሆኑ ስለሌሎች ነገሮች እርግጠኛ መሆን በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ፣ ማሰብ እና ምክንያት ማቅረብ መቻሉን እርግጠኛ መሆን ይቻላል ብሎ ያምናል፡፡ ሃሳቦች እንዲኖሩ ለማሰብ ግብዓት የሚሆኑ ነገሮች መኖር አለባቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ካሰበ ህያው ነው ማለት ነው፡፡ ለዴስካሬት፣ ስዎች አመክንዮን ማቅረብ ይችላሉ፤ ይሄንን ካላደረጉ ግን በቀላሉ ሰዎች አይደሉም ማለት ነው፡፡

ዴካርት እውነት የሚመስል ህልም ካየ በኋላ ከእንቅልፉ ባነነ፤ ለራሱም አሁንስ እያለምኩ ቢሆን ምን ማስረጃ አለኝ? ብሎ ጠየቀው:: ዴካርት በአለም ውስጥ ሊያምነው እና በፍጹም እርግጠኛ ሊሆን የሚችልበትን ነገር ፈለገ። ህልሙ ስለ እውነታው አለም ሊያታልለው ከቻለ ሌላ እርግጠኛ ሊሆንበት የሚችል ምን ነገር ይኖረዋል? አንድ ሲደመር አንድ- ሁለት ባይሆንስ? የሆነ ሰይጣን አንድ ሲደመር አንድ ሁለት እንደሆነ እያሳመነው ቢሆንስ? ሁሌም አንድን ከአንድ ጋር ለመደመር ሲያስብ ሁለት እንደሆነ የሚነግረው ሰይጣን ቢኖርስ? ዴካርት ሁሉንም ነገር ጠረጠረ፤ የስሜት ሕዋሳቶቹ የሚነግሩትን ነገር በሙሉ ጠረጠረ፡፡ ምናልባትም የሰይጣን ቤተ ሙከራ ውስጥ ባለ በፈሳሽ ብልቃጥ ውስጥ ጭንቅላቴን ብቻ ዘፍቀውት ይሆናል፤ የማየው እና የምሰማው ሁሉም የውሸት እና የሌለ ነገርን ሊሆን ይችላል።

ዴካርት በአለም ላይም እርግጠኛ ሊሆንበት የሚችልን ነገር ፈለገ፡፡ በመጨረሻም አንድ ነገር ላይ እርግጠኛ ሆነ - 'መኖሩን'

የሰው ልጅ ማሰቡ ብቻውን፤ (ምንም ያስብ ምን) እርሱ ህላዊ እንደሆነ (እንዳለ) ይነግረዋል፡፡ ማንም እኔ ሳልኖር እንዳለሁ አድርጎ ሊያታልለኝ አይችልም:: ይህንን ሃሳብም ለማሰብ በቅድሚያ መኖር ይኖርብኛል:: የሞተ እና የሌለ ሰው አያስብም፡፡ ሰው ሃሳቡ' ይርባም ይጥቀምም፣ ካሰበ ለመኖሩ ማስረጃ ይሆነዋል፤ ሰይጣን ጭንቅላቴን በቤተ- ሙከራ ውስጥ ባለ ብልቃጥ ውስጥ ቢያስቀምጠውም ሆነ ሁሉም ነገር የውሽት ቢሆን፣ እኔ በዚህ ምድር አለሁ፤ እኔ ሳልኖር ሊያታልለኝ ፈጽሞ አይቻለውም። ለመኖሬ ማስረጃውም አሁን ላይ እያሰብኩ መሆኔ ነው፡፡

እናም ዴካርት እርግጠኛ የሆነበትን ነገር አገኘ እንዲህም አለ፤ “አስባለሁ፣ ስለዚህም አለሁ" ( I think, Therefore I am)

በተጨማሪም ዴካርት ሰዎች በአመክንዮ ችሎታቸው እውነተኛ እውቀትንና ሳይንሳዊ ሃቀኝነትን (እርግጠኝነትን) ማግኘት ይችላሉ ብሎ ያምናል፡፡ ምክንያታዊነት ተፈጥሯዊ የሆነ፣ ለሁሉም ሰዎች የተሰጠ ስጦታ መሆኑን ስለሚያምን፣ እጅግ ውስብስብ በሆኑ ፍልስፍናዊ ጉዳዮች ላይ ለመፃፍ ገፋፍቶታል። ዕሁፎቹም ለአብዛኛው ሰው እንዲገቡ ተደርገው የተፃፉ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ስራዎቹን ከላቲንኛ ይልቅ በፈረንሳይኛ ይፅፍ ነበር፡፡ ምክንያቱም ፈረንሳይኛ በጊዜው በምሁራን ዘንድ ጥቅም ላይ የሚውል ቋንቋ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ መጽሐፎቹ ለብዙሃን ህዝብ ተደራሽ መሆን ቻሉ፡፡

ዴካርት ፍልስፍናዊ ክርክሮች የሃሳብ አመክኖአዊ ልምምዶች ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ እንዲሁም ማናቸውም ሰው በዚህ ልምምድ ውስጥ መሳተፍ ይችላልም ይላል፡፡ ማናቸውም ሃሳባዊ ችግር ወደ ቀላል ችግሮች ከተሰባበረ በኋላ፣ እነዚህ ትንንሽ ችግሮች ደግሞ በረቂቅ እኩልታዎች በኩል ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ይሄንን በማድረግም ማናቸውም ሰው (ዴካርት ተዓማኒ አይደሉም የሚላቸውን) የስሜት መረዳቶች ማስወገድ ይችላል ይላል፡፡ ከዚያም ችግሮቹን ለመፍታት ግላዊ ምክንያታዊነትን መጠቀም ይችላል፡፡

ስሜታዊ ወይም የስሜት መረጃዎች ተዓማኒ ባለመሆናቸው ዴካርት ብቸኛ እውነተኛ እና እርግጠኛ መሆን የቻለበት ጉዳይ ሰዎች አሳቢ ቁሶች እንደሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያታዊነት እና ሃሳብ የሰው
ልጆች መሰረታዊ ባህሪ ናቸው፡፡ ደግሞም
በንፁህ ምክንያታዊነትና በስሜታዊ መረጃዎች መካከል ልዩነት ስላለ የነፍስ መኖር ግዴታ ነው ሲል ዴካርት ይከራከራል፡፡

ህልወተ እግዚአብሔር

እንዲያውም አንድ ጊዜ የሰው ልጅ ህያው ሆኖ ያለው፣ የሚያስብ ነገር ስለሆነ ብቻ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ከዚያም ሌሎች ግላዊ ማረጋገጫ ያላቸውን እውነታዎች ለማግኘት ጥረት ጀመረ:: በስተመጨረሻም ዴካርት መረዳት እና ምናብ የንቃት መገለጫዎች ስለሆኑ፣ በአእምሮ ውስጥ መኖር አለባቸው ሲል ደመደመ፡፡ ነገር ግን እውነትን የግድ ሊይዙ የሚችሉ አይደሉም አለ፡፡ _ ስለዚህ ዴስካሬት በስተመጨረሻ ስለ ሌሎች ነገሮች ሀቀኛ እውቀት ሊኖረን የሚችለው፣ ስለ እግዚአብሔር እውቀት ሲኖረን ብቻ ነው ሲል ደመደመ።

ዴካርት እግዚአብሔር ፍፁማዊ ነው ብሎ ከማመኑ የተነሳ፣ እግዚአብሔር ማንንም ሊያታልል አይችልም የሚል እምነት አለው፡፡ ዴካርት እራሱ እንኳን ፍፁማዊ እንዳልሆነ በማመን፣ ስለ ፍፅምና በተመለከተ ሃሳብ ለመፀነስ እንኳን፣ የግድ ፍፅምና መኖር አለበት ብሏል። ያ ፍዕምነት ደግሞ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ፍፅምና ለማሰብ ራሱ ፍፁም የሆነ አካል መኖር አለበት፡፡ ያም ፍጽምና ደግሞ እግዚአብሔር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰ፡፡

@zephilosophy
@zephilosophy