2022-07-04 22:23:05
ላኦ ዙ (Laozi) ማን ነው?
ምንጭ ፦ የፍልስፍና ሀሁ
ፀሀፊ ፦ በላይ ደስታ
ከመጀመሪያዎቹ የቻይናውያን ፈላስፎች አንዱ፣ የታኦይዝም ትምህርቶች መሥራች ላኦ ዙ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በቁሳዊ ቅንጣቶች ላይ የተመሰረቱ የሚታዩ የተፈጥሮ ክስተቶች የእርሱ አስተምህሮ መሰረቶች ናቸው፡፡ እንደተገለጸው፣ ላኦ ዙ የቻይና ጥንታዊ ፈላስፋ እና የታኦይዝም መስራች አባት ነው፡፡ “ላኦ ዙ” የሚለው ቃል የእንግሊዝኛ ትርጉም ጥንታዊ ፈላስፋ እንደማለት ነው፡፡ "የጥንቱ ሕፃን" ተብሎም የሚታወቅ እንደሆነ ተጽፏል። በጥልቅ ጥበቡና በታዋቂ ተጫዋችነቱ በታኦኢስት የቻይና ነገስታት ዘንድ በሰፊው ይታወቃል፡፡
ስለ ላኦ ዙ ታሪካዊ ሕይወት እምብዛም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የሚታውቀው ነገር ቢኖር፣ ትክክለኛ ስሙ ሊ ኸር ሲሆን፣ በደቡባዊው የዙፋን ዘውድ ቤተሰብ ውስጥ የተወለደ መሆኑ ነው፡፡ በእድሜ ትልቅ ሰው በነበረበት ጊዜ፣ በመንግሥታዊው ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የቤተ-መጻህፍት ባለሙያ በመሆን ከማገልገሉ በተጨማሪ አነስተኛ የመንግስት ቦታን ይዞ እንደነበር ተጽፏል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በቻይና ንጉሳዊ አገዛዝ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ፣ የታኦይዝም ፍልስፍና አንደኛው መንገድ፣ ሀገርን ማስተዳደር ጥበብ ላይ የተመሠረተ ነው። ከሰራቸው ታዋቂ የጥበብ ስራዎች መካከል፤ ግዛትን ለማስተዳደር የተገለጹ አራቱ ጥበቦችንና መንገዶችን የተመለከቱ ነበሩ። እነሱም፣ የንጉሠ ነገሥት መንገድ፣ የንጉሠ ነገሥታዊ መንገድ፣ የንጉሳዊ መንገድ እና የሄግሜኒንግ መንገድ የተሰኙት እንደሆነ ተዘግቧል።
በማሰላሰል ላይ የተመረኮዘ፣ ሙሉ በመሉ ኦፊሴላዊ ያልሆነ ዶክትሪን የሚያስተምረው ላኦ ዙ፣ በዘመናዊው አነጋገር ምስጢራዊ እና ጸጥተኛ መሆንን የሚያስተምር አስተሳሰብ እንደነበረው አሁን ካሉ የጽሑፍ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል። “ሰው በራሱ ውስጥ ካሉ ውሸቶች ሁሉ ራሱን በማውጣት እውነትን ያገኛል” የሚለው አስተሳሰቡ የሚታወቅበት አስተሳሰቡ ነው:: ላኦዙ በአስተምህሮው እንዲህ ሲል ተናግሯል “ከሰማይና ከምድር በፊት የነበረ ማለቂያ የሌለው ፍጡር አለ፡፡ እንዴት የማይደፈር፣ እንዴት የተረጋጋ! እሱ ብቻውን የሚኖር እና የማይለወጥ ነው። ሁሉንም ነገር ያንቀሳቅሳል፣ ግን አይጨነቅም። እንደ ሁለንተናዊ እናት ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ስሙን አላውቅም፡፡ ታኦ ብዬ እጠራዋለሁ” በማለት አስተምሯል፡፡
የፍልስፍና እሳቤዎቹ
"እኔን ማወቅ ከፈለግህ፣ በልብህ ውስጥ አንተነትህን ተመልከት።"
"አንድ ሀገር በጥበብ ከተመራች ኗሪዎቿ ባላቸው የረኩ ይሆናሉ፡፡ "
"የሰውን ልጅ ለመረዳት አለምን ተረዳ፣ አለምን ለመረዳት ደግሞ ሰማየ ሰማያትን እወቅ።"
"ሙሉ ለመሆን ከፈለግህ ጎደሎ ለመሆን ፍቀድ፣ ቀጥ ያለ ለመሆን ካሻህ ጎባጣ ለመሆን ፍቀድ፣ እንዳትጠግብ ከፈለግህ ለመራብ ፍቀድ፣ ለመወለድ ከፈለግህ ለመሞት ፍቀድ፣ እንዲሰጥህ ከፈለግህ ያለህን ስጥ።"
"አብረቅርቆ ለመታየት የሚሞክር የራሱን ብርሀን ያደበዝዛል፣ ለራሱ የማይገባውን ክብር የሚሰጥ እውነተኛ ማንነቱን ያጣል፡፡"
"ሁሉም ነገር የተገኘው ከመሆን ነው፣ መሆን እራሱ የተገኘው ደግሞ ካለመሆን ነው፡፡"
"ጥሩ ተጓዥ የተወሰነ መድረሻ የለውም፣ ጥሩ አርቲስት ምእናቡ ወደ ወሰደው ይሄዳል፤ ጥሩ ሳይንቲስት አእምሮውን ለሆነውና ለሚሆነው ሁሉ ክፍት ያደርጋል፡፡"
"መደበኛ ህልሞችህንና ከንቱ ሀሳቦችህን ተዋቸው፣ አለም ራሷን ታስተዳድራለችና፡፡"
"ህጉን ስትተወው ሰዎች ሀቀኛ መሆን ይጀምራሉ፣ ምጣኔ ሀብትን ስትተወው ሰዎች ሀብታም መሆን ይጀምራሉ፣ ሀይማኖትን ስትተወው ሰዎች በመንፈስ መርካት ይጀምራሉ፡፡"
"ሁሉም ነገር እንደሚለወጥ ከተረዳህ፣ እንዲኖር የምትፈልገው ነገር አይኖርም።"
"ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ሲጋጩ አሸናፊነት የምትሄደው መረታትን ወደተቀበለው ጎራ ነው።"
"እውነተኛ ቃላት ማራኪ አይደሉም፣ ማራኪ ቃላትም እውነተኛ አይደሉም።"
"አለም ብጽእት ናት፣ ልትሻሻል አትችልም፤ ከነካሃት ታወድማታለህ፣ እንደ እቃ ከቆጠርሀት ታጠፋታለህ።"
"ከማጣት ብዙ ይገኛል፤ ከማግኘት ብዙ ይታጣል፡፡"
"ሀያልነት የፈለገውን ያህል ምክንያታዊ ቢሆንም፣ አጥቂውን መልሶ ማጥቃቱ አይቀርም፡፡"
"ሁሉም ወንዞች ከተራሮች ፈልቀው ወደ ባህር የሚፈሱት፣ ባህሩ ዝቅ ብሎ ስለሚገኝ ነው።"
"ዳዋው መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዘላለማዊ ነው፡፡"
"ታላቁ ዳዋ ወደ ሁሉም ይፈሳል፣ ሁሉም ነገሮች ከእርሱ የተፈጠሩ ናቸው፤ ይሁን እንጂ አልወለዳቸውም፡፡"
"ዳዋውን ማእከል ያደረገች፣ ወደ ፈለገችው ቦታ ያለስጋት ትሄዳለች፡፡"
"የሰው ልጅ በአምላኩ ስራ ጣልቃ ይገባል፣ ሰማይ ይቆሽሻል፣ መሬት ሀብቷ
ያልቃል፣ ሚዛኑ ይዛባል፣ ፍጥረታትም ይጠፋሉ፡፡"
"የጦር መሳሪያዎች በበዙ ቁጥር፣ የሰዎች ደህንነት ስጋት ላይ ይወድቃል፣
ለዜጎች ብዙ ድጋፍ ባደረግህ ቁጥር የሰዎችን ራስ የመቻል ጉዞ ይቀንሳል።"
"አንዲት ሀገር ትልቅ ሀይል ሲኖራት እንደ ባህር ትሆናለች፣ ሁሉም ወንዞች ወደ እርሷ ይፈሳሉ።"
@Zephilosophy
@Zephilosophy
3.8K viewsedited 19:23