2022-09-04 14:43:58
ከእኔነት ነፃ መሆን
ምንጭ ፦ የነፍስ መንገድ (ኦሾ)
ትርጉም ፦ መርሻ በነበሩ
በሰው ህይወት ውስጥ ታላቁ ሙዚቃ ሊፈልቅ የሚችለው ልብ በአግባቡ የተቃኙ ክሮች ሲኖሩት ነው፡፡ ልቡን ያጣ ማህበረሰብ ጥሩ፣ እውተኛና ውብ የሆኑትን ክሮች ሁሉ አጥቷል፡፡ እውነት፣ ውበትና አምላካዊ ባህሪያት ወደ ህይወታችን እንዲገቡ ከፈለግን የልብን ሙዚቃ አፍላቂ የሆኑትን ክሮች በአግባቡ ከመቃኘት ውጪ ሌላ መንገድ የለም፡፡
እነዚህን የልብ ሙዚቃ አፍላቂ ክሮች በአግባቡ ለመቃኘት የሚያስችለው መንገድ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅርን “ፀሎት ወይም እግዜርን የማግኛው መንገድ” ብዬ የምጠራውም ለዚህ ነው፡፡ ከፍቅር ያልሆነ ፀሎት ውሸትና የማይጠቅም ነው፡፡ ፍቅር አልባ የፀሎት ቃላት ዋጋ የላቸውም፡፡ ወደ አምላክ ለመጓዝ የፈለገ ሰው ያለ ፍቅር ሊሳካለት አይችልም፡፡ ልባዊ ሙዚቃን የሚያፈልቀው ፍቅር ነው፡፡ ስለፍቅር የተወሰኑ ነገሮችን ልንገነዘብ ይገባል፡፡
የመጀመሪያው “እናውቀዋለን” የሚል ስለ ፍቅር ያለን የተሳሳተ እይታ ነው፡፡ ይህ የተሳሳተ እይታ በእጅጉ የሚጐዳ ነው፤ ምክንያቱም ቀድሞውኑ እናውቀዋለን ብለን የምናስበውን ነገር ለማግኘት ወይም ለመቀስቀስ በጭራሽ ጥረት አናደርግም።
ፍቅርን ያወቀ መለኮትን የማወቅ አቅም እንዳለው አናውቅም፡፡ ፍቅርን ካወቅን በህይወታችን ሳናውቀው የሚቀር ምንም ነገር አይኖርም፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን ምንም አናውቅም፡፡ ሁሉም ነገር ገና የሚታወቅ ነው፡፡
ፍቅር እንደሆነ የምናስበው ፍቅር ላይሆን ይችላል። ፍቅር ብለን የጠራነው ፍቅር ሳይሆን ሌላ ነገር ነው፡፡ ስለፍቅር ጠንቅቀን እናውቃለን የሚል የተሳሳተ እይታ እስካለን ድረስ ፍቅርን ፈልገን ልናገኘው አንችልም፡፡ በቅድሚያ ልገነዘበው የሚገባን ፍቅርን በጭራሽ እንደማናውቀው ነው::
ከእኩለ ቀን በኋላ ሙቀቱ አይሎ በነበረበት አንድ ቀን እየሱስ ከርስቶስ በአንድ የአትክልት ስፍራ ውስጥ ከነበረ ዛፍ ስር ጥላ ለማግኘት ቆመ፡፡ ከሙቀቱ ሃያልነት የተነሳ ደክሞት ነበር። እናም ዛፉ ጥላ ስር ተኛ፡፡ ቤቱ፣ የአትክልት ስፍራውና ዛፉ የማን እንደሆነ እንኳን አላወቀም ነበር:: የአትክልት ስፍራው በጊዜው እጅግ በጣም ቆንጆ የሆንችው የመቅደላዊት ነበር፡፡
መቅደላዊት በመስኮቷ አሻግራ ስትመለከት አንድ በጣም የተለየ ሰው ዛፍ ስር ተኝቶ አየች፡፡ እንዲህ አይነት በጣም ቆንጆ ሰው አይታ አታውቅም፡፡ አካላዊ ውበት እንዳለ ሁሉ የነፍስ ውበትም አለ፡፡አካላዊ ውበት ብዙውን ጊዜ ሊታይ ይችላል፤ የነፍስ ውበት ግን እጅግም አይታይም፡፡ የነፍስ ውበት ሲገለጥ በጣም አስቀያሚ አካል እንኳ እጅግ በጣም የሚያምር አበባ ይሆናል፡፡ ብዙ ሰዎች ወደ ቤቷ ጐራ ስለሚሉ ብዙ ቆንጆ ወንዶችን አይታለች፡፡ ወደ ቤቷ ለመግባት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ልክ በአስማት የሆነ ይመስል መቅደላዊት ወደ ዛፉ ተሳበች፡፡
እየሱስ ተነስቶ ሊሄድ አካባቢ ነበር፡፡ እረፍቱን አጠናቋል። መቅደላዊት ግን ወደ እሱ ቀረበችና፡- “እባክህ ወደ ቤቴ ገብተህ እረፍ፡፡ ስትል ጋበዘችው፡፡
ክርስቶስም፡- “አሁን እረፍቴን ጨርሻለሁ፡፡ የመሄጃ ጊዜዬ ነው፡፡ ነገር ግን ዳግመኛ በዚህ መንገድ የማልፍና የደከመኝ ከሆነ በእርግጠኝነት አንቺ ቤት ውስጥ አርፋለሁ፡፡” ሲል መለሰላት፡፡
በዚህም መቅደላዊት የተሰደበች ያህል ተሰማት፡፡ ታላላቅ ልዑሎች ቤቷ የመግባት እድል ሳያገኙ ከበሯ ተመልሰዋል፡፡ ይህን ተራ የመንገድ ሰው ወደ ቤቷ ገብቶ እንዲያርፍ ስትጋብዘው ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ይህ ለመቅደላዊት ስድብ ነበር፡፡ እናም፡- “ይህን ማድመጥ አልችልም፡፡ ወደ ቤቴ መምጣት አለብህ፤ ይህን ያህል እንኳ ለፍቅሬ ስትል ማድረግ አትችልም? ለጥቂት ቅፅበታት እንኳ ቤቴ ውስጥ እረፍት አታደርግም?” ስትል ስሜታዊ ሆና ጠየቀችው፡፡
ክርስቶስ ግን፡- “ስለ ጋበዝሸኝ ብቻ ወደ ቤትሽ ገብቻለሁ፤ ምክንያቱም ከልባዊ ስሜቶችሽ ውጪ ምን ቤት አለሽ? ይህን ያህል ፍቅር እንኳ አታሰየኝም ወይ? ብለሽ ጠይቀሽኛል። እንደሚወዱሽ የገለፅልሽ ብዙ ሰዎች አጋጥመውሽ ይሆናል፡፡ አንዳቸውም ግን አይወዱሽም ነበር፡፡ በውስጣቸው የሚወዱት አንቺን ሳይሆን ሌላ ነገር ነበር፡፡ ማፍቀር የሚችለው በልቡ ውስጥ ፍቅር የሞላ ሰው ብቻ ነው፡፡ እኔ ደግሞ አንቺን በእውነት ሊወዱሽ ከሚችሉ እና ከሚወዱሽ ጥቂት ሰዎች አንዱ መሆኔን ላረጋግጥልሽ እችላለሁ፡” ሲል መለሰላት፡፡
በውስጣችን የፍቅር ፍሰት ስለሌለ ማናችንም ማፍቀር አንችልም፡፡ አንድን ሰው እንደምናፈቅረው ስንናገር በእርግጥ ፍቀር እየሰጠነው ሳይሆን ፍቅርን እንዲሰጠን እየጠየቅነው ነው፡፡ ሁላችንም ፍቅር እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡ ታዲያ ፍቅር እንዲሰጠው የሚጠይቅ ሰው እንዴት ፍቅርን ሊሰጥ ይችላል? ለማኞች እንዴት ንጉሶች ሊሆኑ ይችላሉ?
አንዳችን ካንዳችን ፍቅርን እንጠይቃለን፡፡ ፍቅርን ከሌላው የምንጠይቅ ለማኞች ነን፡፡ ሚስት ከባሏ ፍቅርን ትጠይቃለች፤ ባል ከሚስቱ ፍቅርን ይለምናል፡፡ እናት ከልጇ፣ ልጅም ከእናቱ ፍቅርን ይጠይቃሉ፡፡ ጓደኛ ከጓደኞቹ ፍቅርን ይፈልጋል፡፡ ፍቅር እንዲሰጠን የምንለምነው ጓደኛችን ራሱ ፍቅርን ከእኛ እየለመነ መሆኑን ባለመገንዘብ ሁላችንም አንዳችን ከአንዳችን ፍቅርን እንጠይቃለን፡፡ መለመኛ ከረጢታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው እንደቆሙ ለማኞች ነን፡፡
አንድ ሰው ፍቅርን ሌላው እንዲሰጠው እስከጠየቀ ድረስ እሱ ራሱ ፍቅርን መስጠት አይችልም፡፡ ምክንያቱም የእሱ ከሌላው ፍቅርን መጠየቅ የሚያመለክተው በውስጡ ምንም የፍቅር ምንጭ አለመኖሩን ነው፡፡ ያ ካልሆነ ለምን ፍቅርን ከውጪ ይጠይቃል? ፍቅርን ከሌላው የመጠየቅ ፍላጐት በላይ የሆነ ሰው ብቻ ፍቅርን መስጠት ይችላል፡፡ ፍቅር ማካፈል እንጂ ልመና አይደለም፡፡ ፍቅር ንጉስ እንጂ ለማኝ አይደለም፡፡ ፍቅር የሚያውቀው መስጠትን ብቻ ነው፡፡ ስለ ልመና የሚያውቀው ነገር የለም፡፡
በእርግጥ ፍቅር እናውቃለን?
ሌላው እንዲሰጠን የምንጠይቀው ፍቅር ፍቅር ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ዓለም ፍቅርን ከሌላው የሚጠይቅ በጭራሽ አያገኝም፡፡ እጅግ በጣም ወሳኝ ከሆኑ ዘላለማዊ የህይወት ህጎች አንዱ ፍቅርን ከሌላው የሚጠይቅ መቼም ፍቅር እንደማያገኝ መሆኑን አስታውሱ።
ፍቅር የሚመጣው በልመና አይደለም፡፡ ፍቅር መዝነብ የሚጀምረው ፍቅር መጠየቅ ባቆመ ሰው ቤት ላይ ነው፡፡ ፍቅርን ፍለጋ ለሚዞር ሰው ቤት ላይ ግን ጠብ የሚል የፍቅር ዝናብ የለም፡፡ በጠያቂ ልብ ውስጥ የፍቅር ፍሰት የለም፡፡ ጠያቂ ልብ ፍቅር ወደ ውስጡ ሊዘልቅ የሚያስችል ክፍተት የለውም፡፡ ፍቅር ወደ ውስጡ ሊዘልቅ የሚችለው አካፋይ ወይም ሰጪ ልብ ውስጥ ነው::
ፍቅር በራችንን አንኳኩቶ ያውቃል? በጭራሽ! ምክንያቱም ገና ፍቅር መስጠት አልቻልንም:: ማስታወስ ያለባችሁ የሰጠነው ሁሉ ወደ እኛው ተመልሶ እንደሚመጣ ነው። ይህም ከዘላለማዊ የህይወት ህጐች አንዱ ነው::
መላው አለም ከገደል ማሚቱ የተሻለ አይደለም፡፡ ጥላቻ እንሰጣለን፤ ጥላቻም ወደኛው ተመልሶ ይመጣል፡፡ ቁጣ ስንሰጥም ቁጣው ተመልሶ ወደኛው ይመጣል። ሌሎችን እንሰድባለን ከዛም ስድብ ወደኛው ተመልሶ ይመጣል። እሾህ ስንሰጥ እሾህ ወደ እኛው ተመልሶ ይመጣል። የምንሰጠው ሁሉ በተለያዩ መንገዶች ወደ እኛው ተመልሶ ይመጣል፡፡ ፍቅርን ካካፈልንም እንደዚሁ በተለያዩ መንገዶች ወደ እኛው ተመልሶ ይመጣል፡፡ ስፍር ቁጥር በሌላቸው መንገዶች ፍቅር ወደ እኛ ተመልሶ ካልመጣ ፍቅር እንዳልሰጠን ማወቅ አለብን፡፡
@Zephilosophy
@Zephilosophy
674 views11:43