2022-11-01 02:00:53
‖※‖፧፠፨፠፧‖ ▬ አ ይ መ ለ ል ▬ ‖፧፠፨፠፧‖※‖
ደራሲ፦ ተሥፋ ገብረየስ ዘምድረ-ከብድ
አዘጋጅ፦ ወርቁ ተሥፋ
አርትዖት፦ ነጋሽ ገብረማርያም /ጋዜጠኛ/
የአይመለልን (ሶዶ ጐርደና) ብሔረሰብ ባህልና ታሪክ የሚመለከት መግለጫ በሚዘጋጅበት ወቅት ከሁሉ አስቀድሞ የታሪኩ ምንጭ የሆኑት ቃላት ማለት አይመለል ፥ ጉራጌ ሶዶ ፥ ክስታኔ ፥ ጐርደና ምንን እንደሚያመለክቱና ግንኙነታቸው ምን እንደሆነ መረዳት ጠቃሚ ይሆናል።
ከታሪክ እንደምንረዳው አይመለል በደቡብ ኢትዮጵያ የአዋሽን ወንዝ ተሻግሮ ከሰሜን ወደ ደቡብ መሀከሉ እንደ ሠንሠለት በተያያዘ ተራራ አገምግሞ የሚታየውና ከደጋው ቀጥሎ ወይናደጋው ከዚያም ቆላው በተዋረድ በእንሰት ልምላሜ አሸብርቆ የተንጣለለው ሀገር ነበር። ይህ ሀገር በአሁኑ አጠራር ሶዶ አውራጃ በመባል ይታወቃል። ዛሬም ቢሆን ታሪክን የምታስታውሰን አይመለል ተብላ የምትጠራ ትንሽ አምባ በሶዶ ጐርደና ከደጋው ላይ ትገኛለች።
ጉራጌ ማለትም የጉርዓ ሰዎች ሰብአ ጉራጌ ማለት ነው። ይኸም ጥንተ-ስሙ ጉራዕ ሲሆን ጐንደር ብሎ ጐንደሬ ፥ ወሎ ብሎ ወሎዬ እንደሚባለው ሁሉ ጉራዕ ብሎ ጉራዕጌ ተባለ። ዛሬ ሶዶ ጐርደና በመባል የሚታወቀውን ወረዳ የሚያቅፈው ሰፊ ሀገር የጉራጌ ነገድ ወደዚህ ክፍል ከመምጣቱ በፊት አይመለል ተብሎ ይጠራ ነበር። ይኽንንም ታሪክ የጉርዓ ሰዎች ከጉርዓ ተነስተው በአይመለል ተሠሩ በማለቱ መረዳት ይቻላል። ጉራጌ የነገዱ ስም ሲሆን ፥ አይመለል የሀገሩ ስም ነው። ከረጅም ጊዜ ጀምረው በአይመለል የሚኖሩት ሕዝቦች ክስታኔ ተብለው ይጠራሉ። ክስታኔ ማለትም “ክርስቶስን የተቀበለ ፥ ክርስቲያን” ማለት ነው።
የአይመለል መሬት ቅድመ-ሥሪቱ የጉራጌ ቢሆንም ከግራኝ ወረራና ከዚያም በፊት በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ አቅጣጫዎችና ሀገሮች እየፈለሱ ወደ ተጠቀሰው ሀገር እየገቡ ፥ የሰፈሩባቸውን ቀበሌዎች በጐሳዎቻቸው ግንድ አባቶች ስም እንዲጠሩ እያደረጉ በመኖር እስከ ዛሬ የሚገኙ ነገዶች ብዙዎች ናቸው ፥ ከነዚህም አንዱ ሶዶ የተባለው ነው።
ሶዶ የሚለው ቃል በአንድ በኩል የሀገር ስም ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የነገድ ስም ነው። ሶዶ በምሥራቅና በሰሜን ከጂዳና ከአቡ ገላን ፥ በምዕራብ ከሜጫና ከበቾ እየተካለለ በጉራጌ ሰሜን ይገኛል። የሶዶ ብሔ ረሰብ ከነገደ ኦሮሞ የቦረና ልጅ ነው። አንዳንድ ታሪክ ሶዶን ከበርቱማ የወረንሻ ልጅ ያደርገዋል። የሶዶ ልጆች ግን ከቦረና የወረዱ የዳጪ ልጆች እንደሆኑ ይተርካሉ። ሰዴን ሶዶ ተብለውም ይጠራሉ። ይህም ሦስቱ ሶዶ ማለት ነው። እነሱም ቱምኤ ፥ ሊበንና ኦዲቱ ናቸው።
ጐርዶና ማለት በአንድ ዓይነት ወግና ሥርዓት የሚተዳደሩትን ኅብረተሰቦች የሚያቅፍ አንድነትን ፥ ሕብረትንና ጥንካሬን የሚያመለክት የጥቅል ስም ነው።
የአይመለልን (ሶዶ ጐርደና) ሕዝብ ታሪክ በምናነሳበት ወቅት በአጠቃላይ ስለ ጉራጌ ብሔረሰብ የተነገሩትንና የተጻፉትን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው። ስለ ጉራጌ ብሔረሰብ ታሪክ ጥቂቶች ኢትዮጵያውያንና ቁጥራቸው በርከት ያለ የውጭ ሀገር ምሁራን ያሠፈሩት ጽሑፍ ይገኛል። አብዛኞቹ ደራሲያን ለሚጽፉት ታሪክ መነሻ ያደረጉት በሀገሩ ውስጥ ይገኙ ከነበሩት ሽማግሌዎች የሰበሰቡትን አፈ-ታሪክ ነው።
ስለ ጉራጌ ብሔረሰብ ታሪክ ከጻፉት ደራሲያን መካከል አለቃ ታዬ ፥ አቶ ሰይፉ ድባቤንና እንዲሁም ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን ለአብነት ያህል መጥቀስ ይቻላል። ከውጭ ሀገር ደራሲያን መካከል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለ ጉራጌ ሕዝብ ማንነት የጻፉት ጥቂቶች አይደሉም። በኪንግሃምና ሐንቲንግ ፎርድ ፥ ፊልፕ ሌብል ፥ እርነስት ኦግስትጋት ፥ ዊሊያም ሻክና ሌሎችም እንደ ኮንት ሮሲኒ ያሉት ምሁራን መጥቀስ እንችላለን። ውልፍ ሌስሎ ፥ ማርጆሪ ፔርሃምና ሌሎችም በአጭሩ ጠቅሰውታል።
የአይመለል ጉራጌ ታሪክ በጉራጌ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የታቀፈ ቢሆንም የራሱ የሆነ የተለየ ታሪክ አለው። ከዚህ በላይ እንደ ተመለከተው አንዱ ደራሲ የሚጽፈው ሌላውን በመጥቀስ መሆኑ ባይካድም አብዛኞቹ ደራሲያን የሚስማሙበት አንድ አቢይ የሆነ ነጥብ አለ ይኸውም በ1327 ዓ.ም. ገደማ በዓፄ አምደ ጽዮን ዘመነ-መንግሥት በአዝማች ስብሀት መሪነት ከአካለ ጉዛይ አውራጃ ከጉራዕ ቀበሌ የተንቀሳቀሰ የንጉሡ ጦር አይመለል በተባለው ሥፍራ እንደሠፈረ የሚተርከውን ታሪክ ነው።
ከዓፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ እስከ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ መንግሥት በነበረው ዘመን የነገሥታቱ ኃይል እየተዳከመና ከሕዝቡ እየራቀ በመሄዱ በአካባቢው ሰላምና ጸጥታ ታጥቶ ነበር። ሕዝቡም ከየጐሣው አማካሪ መርጦ በእነዚህ አማካሪዎች አማካይነት አዝማቾች ፥ አበጋዞች ፥ ዳኞች ሊቀ-ካህናቶች ፥ ቃዲዎች ለተወሰነ ጊዜ እየሾመ ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር ኖሯል። በዚህ አካባቢ ሠላም የተገኘው ዓፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ አድርገው በአካባቢው ሕግና ሥርዓት ከሰፈነ በኋላ መሆኑ የትናንት ታሪክ ነው።
ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ በተለይም ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የአይመለል ጉራጌና ሶዶ በስም ፥ በጋብቻ ፥ በሃይማኖት ፥ በባህል ፥ በቋንቋ በመዋሃድ አንድ ሕዝብ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ “ጉራጌ ሶዶ” “ሶዶ ጉራጌ” ተብሎ ሲጠራ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሶዶ አውራጃ ተብሎ በአንድ ስም እንደሚጠራ ማስተዋል ያስፈልጋል።
የአይመለል ጉራጌ ብሔረሰብ ሁለት ቋንቋዎች ይናገራል። አብዛኛው ሕዝብ የሚናገረው ክስታኒኛ (የአይመለል ጉራጌኛ) ሲሆን ሁለተኛው ኦሮምኛ ነው። ክስታኒኛው ከአማርኛና ከግዕዝ የቅርብ ግንኙነት ያለው ሲሆን ቋንቋው የቃላት ስፋት ያለው በመሆኑ የአማርኛው ቃል በሚያጥርበት ጊዜ በክስታኒኛ ተብራርተው የሚገለጹ ጉዳዮች (ቃላት) መኖራቸው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጿል።
ደራሲው አቶ ተስፋ ገብረየስ የዛሬ 50 ዓመት ገደማ የጻፉት ይህ መጽሐፍ የጉራጌን ሕዝብ ታሪክ በስፋትና በጥልቀት ለመግለጽ የተጻፈ በአንድ ርዕስ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ አይደለም።
ይህ ሁለገብ የሆነ መጽሐፍ የጉራጌን ሕዝብ በተለይም የአይመለል ጉራጌን (ሶዶ ጐርደና) ሕዝብ ለአንባቢ የሚያስተዋውቀው በታሪኩ ላይ ብቻ በማተኮር ሳይሆን ፥ ባሕሉን ወጉን ፥ ሥርዓቱን ሃይማኖቱንና ቋን ቋውን ግንዛቤ እንዲያገኝ በማድረግ የጉራጌ ሕዝብ ማንነት ከአዲሱ ትውልድ ተሰውሮ እንዳይቀር ለማድረግም ጭምር ነው።
አቶ ተስፋ ገብረየስ በመንፈሣዊ ትምህርት የበሰሉና ለነበሩበት ዘመን ቀድመው የተፈጠሩ ምሁር በመሆናቸው ዘመን ተለውጦ ትውልድ ሲተካ ሊዘነጉ ይችላሉ ብለው ያሰቧቸውን የጉራጌን ሕዝብ የኢኮኖሚ ፥ የማህበራዊና የፖለቲካ ሕይወት በአጭር በአጭሩ አስቀምጠውታል።
ይህ መጽሐፍ ሳይታተም ቢዘገይም ፥ የተጻፈው ረዘም ካለ ጊዜ በፊት በመሆኑ የጂኦግራፊ ወሰኖች ፥ የሥፍራ ስሞች * የአነጋገር ፈሊጦች ተለውጠው ይሆናል። መጽሐፉ የደራሲውን ማንነትና የወቅቱን የአነጋገር ዘይቤ ፥ ወግና ሥርዓት እንዲፈነጥቅ ስለ ተፈለገ አዘጋጁ መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ለማረም አልሞከረም። ቢሞከርም ችሎታው ላይኖር ይችላል።
138 views23:00