2022-11-28 11:44:55
የገና አከባበርና ትውፊታዊ ክንውኖች በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ (ሶዶ ጉራጌ)
*****
ክፍል አንድ(በዘፀአት ቱቼ)
*የክስታኔ ማህበረሰብ ገና እንዴት እንደሚከብርና ሃይማኖታዊ ትውፊቱና ባህላዊ ዳራው ለመተንተን ከመሞከራችን በፊት ስለማህበረሰብ ስያሜና ማንነት በጥቂቱ መጥቀሱ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነገር ይሆናል።ከስያሜው ስንነሳ ክስታኔ ማለት ክርስቲያን ማለት ሲሆን በዓለም ህዝብ በክርስቶስ ስም የሚጠራ ብቸኛ ህዝብም ጭምር ነው።
የክስታኔ ማህበረሰብ ክስታኔተብሎ ከመጠራቱ በፊት አይመለል ተብሎም ተጠርቷል።አይመለል ማለት የማይደፈር የታፈረ አማኝ ህዝብ ማለት ነው።ክስታኔና አይመለል በሚሉት ቃላቶች መካከል ይሄን ያህል የትርጉም ልዩነትም የላቸውም(ክስታኔ =ክርስቲያን =አይመለል =አማኝ)
የክስታኔ ማህበረሰብ ልክ እንደስያሜው በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታይ ሲሆን ባህሉና አኗኗሩም ከክርስትና ሃይማኖት ጋር እጅግ በጣም ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው።በመሆኑም የክስታኔ ማህበረሰብ ባህልና ማንነት ጠለቅ ብለን ስንመረምርና ስናጠና በአብዛኛው ከክርስትና ሃይማኖት ትውፊት ጋር ተያይዞ እናገኘዋለን።ለአብነትም አዳብና ፣ኬርታ ዪምር ዪምርና ሌሎችም ባህላዊ ክንውኖች ከባህላዊ ይዘታቸው በተጨማሪ ጠለቅ ያለ ከክርስትና እምነት ጋር የተያያዘ ሃይማኖታዊም ይዘት ያላቸው ናቸው።
በአጠቃላይ ስለክስታኔ ማህበረሰብ ባህልና አኗኗር ስንፅፍም ስናነብም በዚህ አውድና ክስታኔዎች ልክ እንደስያሜያቸው ክርስትናን ባህላቸው አርገው ለዘመናት የኖሩ መሆናቸው መረዳት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።
ስለማህበረሰቡ ይችን ታክል ፍንጭ ሰጥተን ወደ ተነሳንበት ዋና ርዕሰ ጉዳይ ስንመለስ ክስታኔዎች ገናን እንዴት ያከብሩታል? በገና ወቅት ምንምን አይነት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክንዋኔዎች ይከወናሉ?ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊታቸውስ ምንድነው?የሚሉትን አንኳር ነጥቦች ማንሳት ግድ ይለናል።
የገና በዓል በክስታኔ ጉራጌ ዘንድ በአብዛኛው በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደው ሃይማኖታዊና ባህላዊ የገና አከባበር እንዳለ ሆኖ ነገር ግን በክስታኔዎች ዘንድ ሌሎች ሃይማኖታዊ ትውፊት ያላቸው ባህላዊ ክንዋኔዎች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ዪምር ዪምር፣፣አንቃትና፣እንዞሪቴ የሚጠቀሱ ናቸው።
በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ገና ላይ ከሚከውኑ ባህላዊ ክንውኖች አንዱ ዪምር ዪምር ነው።ዪምር ዪምር በአንድ መንደር የሚኖሩ ልጃገረዶችና ወጣቶች የገና ዕለት ወንፊት ፣ጠላ በጣሳና በቂቤ የታሸ የገብስ ቆሎ ይዘው በመንደሩ ቀጣይ በምታገባው ልጃገረድ ግቢ ውስጥ ባለ መስክ ላይ በሰብስበው ያያዙትን ወንፊት ወደ ፀሀይ አቅጣጫ (ወደ ምስራቅ) በማንሳትና ፊታቸውን በያዙት ወንፊት በመሸፈን "ዪምር ዪምር አንድ፣ ዪምር ዪምር ሁለት... "እያሉ እስከ 12 ጊዜ ከቆጠሩ በኋላ የያዙትን ወንፊት ወደ መሬት ወርውረው በመጣል ወጣቶች የሚያከብሩት ስነስርዓት ነው።በመቀጠል ወጣቶቹ እስከ 12 ጊዜ ዪምር ዪምር ካሉ በኋላ የያዙትን ወንፊት ወርውረው ይጥሉታል።በመቀጠልም እያንዳንዳቸው ይዘው የመጡትን ጠላና በቂቤ የታሸ ቆሎ አንድ ላይ በማደባለቅ ቆለው እየበሉ ጠላውን እየጠጡ ጫወታቸው ይቀጥላሉ። በመጨረሻም ዪምር ዪምር ብቅ ቤል የዳኮኛ(የሚትኛ) ጠላት ጠክ ቤል" በማለት የዪምር ዪምር ስነስርዓታቸው ያጠናቅቃሉ።
ነገርግን የልጃገረዶቹ ጫወታ በዚህ ብቻ አያበቃም በድጋሚ ማታ ላይ እያንዳንዳቸው ከየቤታቸው እንጀራ በወጥ በመያዝ በሚቀጥለው ጥር ወይም መጋቢት ላይ በምታገባው ልጃገረድ ቤት ማታ ማታ በመሰብሰብና በማደር እስከ ጥር ድረስ የተለያየ ጨዋታ ይጫወታሉ። ማታ ማታ ልጃገረዶቹ ሲሰበሰቡ የአካባቢው ጎረምሶችም የተሰበሰቡበት ቤት ድረስ ሄደው አብረዋቸው ይጫወታሉ ።ነገር ግን ጎረምሶቹ ማደር አይችሉም ተጫውተው በጊዜ ወደየቤታቸው መሄድ ይጠበቅባቸዋል።
የዪምር ዪምር ትውፊታዊ አመጣጥ
በክስታኒኛ(ጉራጊኛ) ቋንቋ ዪምር ማለት ፀሀይ ወይም ኮከብ ማለት ሲሆን ዪምር ዪምር ማለት ደግሞ ፀሀይ ፀሀይ ወይም ኮከብ ኮከብ ማለት ነው።
የዪምር ዪምር ጥሬ ትርጉሙ ይሄ ከሆነ የልጃገረዶችና ወጣቶቹ ወደ ፀሀይ አቅጣጫ በመዞር ፊታቸውን በወንፊት በመጋረደ "ዪምር ዪምር አንድ ..." እያሉ 12 ጊዜ መቁጠራቸው ትርጉሙ ምንድነው የዪምር ዪምር ስነስርዓት ከገና በዓል ጋር ያለው አጠቃላይ ስዕልና ቁርኝት እንዲሁም ሃይማኖታዊ ዳራው ለመረዳት እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው።
የልጃገረዶቹና የወጣቶቹ ፊታቸውን ወደ ፀሀይ አቅጣጫ በማዞርና በወንፊት በመጋረድ 12 ጊዜ "ዪምርዪምር አት፣ ዪምር ዪምር ኪት፣ዪምር ዪምር ሶስት..." እያሉ መቁጠራቸው ሰባሰገል የክርስቶስን መወለድ ያበሰራቸው የምስራቅ ከከብ ተከትለው እየሱስ የተወለደበት ስፍራ ለመድረስ ያደረጉትን ፍለጋ የሚያሳይ ነው በማለት የአካባቢው የአይማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎች ይናገራሉ። ሰባ ሰገል(ሰባሰገል ማለት በግዕዝ የጥበብ ሰዎች ማለት ነው) ከምስራቅ ተነስተው ወደ እየሩሳሌም ከመድረሳቸው በፊት እንደመፅሐፍ ቅዱስ ገለፃ የምስራቋ ኮከብ አንዳንዴ ትሰወርባቸው ነበር።ሰባሰገሎችም ጎዞቸው ለመቀጠል ሰማይ ላይ ካሉት እልፍ አህላፍ ከዋክብት የምስራቋን ኮከብ ፈልገው ማግኘት ግድ ይላቸው ነበር።
ክፍል ሁለት ይቀጥላል።
389 views08:44