Get Mystery Box with random crypto!

የስራዋ ልዕልት ጊስት (እማሆይ) ዘምዘም ገርቢ ---------------- ድንቅ በጎ ስራ ለሰሩ፣ | አዳብና መልቲ ሚዲያ

የስራዋ ልዕልት
ጊስት (እማሆይ) ዘምዘም ገርቢ
----------------
ድንቅ በጎ ስራ ለሰሩ፣ አርአያ ለሆኑ እና ለታታሪ ሴቶች የሚሰጥ“ጊስት” የሚባል ማዕረግ ከጉራጌ ህዝብ በክብር ተሰጥቷቸዋል፡፡ የስራ ልዕልት እንደማለት ነው፡፡
ዘምዘም ገርቢ፡፡ በኋላም መንኩሰው “እማሆይ” ተብለዋል፡፡
ልክ እንደ ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን፣ ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና የማይረሳ በጎ ስራ የሰሩ ብርቱ ሰው ናቸው፡፡ ነገር ግን የስራቸውን ሩብ እንኳን ያልተነገረላቸው፡፡
በልጅነታቸው ትምህርት የመማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ነገር ግን በተወለዱበት ጉራጌ ክፍለሀገር አማውቴ አካባቢ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የሚመኙትን ትምህርት ሳያገኙ የልጅነት ጊዜያቸው አለፈ፡፡ በዚህ በተፈጠረባቸው ቁጭት እና ከአምላክ በተቸራቸው የዓላማ ፅናት ትምህርት ቤት ለመመስረት ተነሱ፡፡ ተሳክቶላቸውም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል አስጀመሩ፡፡ በ1964 ዓ.ም፡፡
ምን ይሄ ብቻ መንደራቸውን ከዋና መንገድ የሚያገኛኝ የ20 ኪ.ሜ የጥርጊያ መንገድ አሰሩ፡፡
በንግዱ ዓለምም ከሁለት ብር መርፌ ንግድ ተነስተው የትላልቅ የንግድ መደብሮች እና የሆቴሎች ባለቤት ለመሆን በቁ፡፡ ከገነቧቸው ሆቴሎች መርካቶ የሚገኘው “አስፋውወሰን ሆቴል” ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ስኬታማ ስራቸው በወቅቱ የነበሩ ነጋዴዎች “በለጠች” በሚል ቅጽል ስም እንዳወጡላቸው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
በቀደማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በበጎ ስራቸው የሚታወቁ ሴት ስራ ፈጣሪ እና ባለፀጋ ነበሩ፡፡ በታታሪነታቸውም ልዩ ሽልማት አግኝተዋል፡፡
እነዚህ ድንቅ ስራዎቻቸው ለህዝብ አሸጋግረው በተወለዱ በዘጠና ዓመታቸው በ1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
በጊስት ዘምዘም የተመሰረተው ትምህርት ቤት ከ30 ዓመታት በኋላ በአካባቢው ተወላጆች ጥረት ሁለት ክፍሎችን ጨምሮ እስከ እስከ ስምንት አደገ፤ ቀጥሎም በቅርቡ ወደ ሃይስኩል ከፍ አለ፡፡ አሁን ደግሞ 11 እና 12ኛ ክፍል ለማስጀመር ጥቅምት 29/2013 ዓ.ም ቀን ተቆርጦለታል፡፡ እማሆይ ዘምዘም ዕድሜ ሰጥቷቸው የመሰረቱት ትምህርት ቤት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ቢያዩት ምኞቴ ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ ይህንን ለማየት አልታደሉም፡፡
ከትምህርት ባሻገር እማሆይ ዘምዘም ስማቸው በስፋት የሚነሳው ከእንሰት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩ የመንግስት ባለስልጣናት እንሰትን በግብታዊ ውሳኔ ሊያጠፉት ሲነሱ “ይሄማ እንዴት ይሆናል“ ብለው የባለስልጣናቱን እንሰት የማጥፋት ሃሳብ አሳምነው ያስቀየሩ ስመጥር ሰው ናቸው፡፡
እኚህ ብዙ ያልተነገረላቸው እማሆይ ግለ-ታሪካቸው ለሌሎች አስተማሪ እና አነሳሽ በመሆኑ በፕሮግራም ወይም በዶክመንታሪ መልክ መስራት የምትፈልጉ የሚዲያ ባለሙያዎች ብታናግሩን እና ብንተጋገዝ መልካም ነው፡፡
ከ48 ዓመታት በፊት በአንድ ሰው ይህ ሁሉ ከተሰራ ከተባብረን ምን እንደምንሰራ መገመት አያዳግትም፡፡ በዚሁ አጋጣሚ እማሆይ ለመሰረቱት ትምህርት ቤት መፃህፍት የመስጠት ፍላጎቱ ያላችሁ የቀድሞ ተማሪዎችና ይህን በጎ ዓላማ መደግፍ የምትፈልጉ ወዳጆች በሙሉ በውስጥ መስመር አናግሩኝ በተቀናጀ ሁኔታ ለማገዝ አንዳንድ ስራዎችን ጀምረናል፡፡
እማሆይ ይህን ትምህርት ቤት ባይመሰርቱት አሁን ያለሁበት ደረጀ መድረስ እስል ነበረ ወይ?! ማሰብ አልፈልግም ብቻ እንኳንም መሰረቱት፡፡
አርአያ የሆኑ መንፈሰ ጠንካራ ሴት የመሰረቱት ትምህርት ቤት በመማሬ እድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል፡፡
ጋሻው ታደሰ ነው ያቀረበው


ባህላችን ለዓለም እናሰተዋውቅ!
ቅርሶቻችን በአንድነት እንጠብቅ!

አዳብና  መልቲ ሚዲያ Telegram ሊንኩን በመንካት ይቀላቀሉ። https://t.me/Adabnamidea

አዳብና You tube like share subscribers
በማድረግ ግዴታችን እንወጣ።

አዳብና ሚዲያ ዩቱብ https://youtube.com/channel/UCbihhwTdI6hy-e7Kj6T_J8g