2022-09-13 14:13:46
ፍኖተ አበው ዘኦርቶዶክስ (መ/ር ንዋይ ካሳሁን):
“መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ”
ጢባርዮስ ቄሳር ከ 14 -37 ዓ.ም ድረስ የሮማ ንጉሥ ነገሥት ነበር። ጢባርዮስ ቄሳር የነገሠበት አስራ አምስተኛው ዓመት ወደ 28 ኛው ዓ.ም ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አገልግሎቱን ጀመረ።
ከአይሁድ ነቢያት ሁሉ በጣም ኃያሉ ነበር። “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል ” ማቴ .11:11 ትኅትናው የተለየ ነው ። ራሱ ሲናገር "በኋላ የሚመጣውን መሲህ የጫማ ማሳሪያ እንኳ ልፈታ አይገባኝም" ይል ነበር። ባሪያዎች እንኳ የጌታቸውን ጫማ አይፈቱም ነበር። ባርያ የማይሰራውን ስራ እንኳ አልችልም አለ።
ከሴቶች ከተወለዱ ሁሉ የሚበልጠው ዮሐንስ ግን የጌታችንን ጫማ ክር ለመፍታት የበቃሁ አይደለሁም አለ። ይህ ትኅትና ቀርቶ አንጥፍጣፊ አለን ይሆን። እኛ ሁሉን አዋቂ፡ ብዙ የምንበልጣቸው እንዳሉ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ እንደሆንን እናስብ የለ።
እግዚአብሔር ለሰው ደኅንነት ወደ ዓለም መምጣቱ በብዙ ምሳሌዎች ተገልጧል። ከነዚኽም ጉልህ ሆኖ የሚታየው በዮሐንስ የደረሰው ነገር ነው። ዮሐንስ የካህን ልጅ ነው። ምንም የምድራዊ ክብር ያልፈለገ ሲሆን ቢፈልግ ኖሮ በሔሮድስ አንቲጳስ ከፍተኛ መፈለግ ነበረው።
ዮሐንስ ቅዱስና ጻድቅ ስለነበረ ሔሮድስ ይፈራው ነበር። ክፉዎች ጥሩዎችን ይፈራሉ። እግዚአብሔርን የማይወዱ ሃይማኖትን ይጠላሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ኅሊናቸው እንዲነካ አይፈልጉም። “ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር” ማር.6:20
የዮሐንስ ስብከት ለአይሁዳውያን እንግዳ ነበር። ምክንያቱም ንሰሐ መግባት መጠመቅ አለባችሁ ይል ነበር። አይሁዳውያን አሕዛብን ያጠምቁ ነበር እንጂ እነርሱ አይጠመቁም ነበረ። አስፈላጊ እንደሆነ አያምኑም ነበር። እግዚአብሔር ለራሱ የመረጣቸው የአብርሃም ወገኖች በመሆናቸው ራሳቸውን የሚመለከቱት እንደ ጻድቅ ነው። ነገር ግን የንሰሐ ፍሬ እንዲያፈሩ ነገራቸው። ዮሐንስ ለፈሪሳውያን ለሕዝቡ ለወታደሮች ማድረግ ያለባቸውን ነገራቸው።
“ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው፦ መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉት። ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ አላቸው። ጭፍሮችም ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ አላቸው ” ሉቃ.3:10
እንደ ሄሮድስ ያሉ ዓለማውያን፣ አዋቂዎች አልያ የተማሩ ሰዎች አዲስ ነገር ብቻ መስማት ይፈልጋሉ። ኑሮን የሚነካ ነገር ከተነሳ ሌላ ሐሳብ ወደ ልባቸው ይገባል።” አግሪጳም ፊስጦስን፦ ያንንስ ሰው እኔ ዳግም እኮ እሰማው ዘንድ እወድ ነበር አለው። እርሱም፦ ነገ ትሰማዋለህ አለው።” ሐዋ.25:20
ማንም ቢሆን የልቡን ሲነግሩት ቁስሉን ሲነኩት ማኩረፍ ይጀምራል። ተሰደብን፣ ተደፈርን ይላል። እግዚአብሔር ተናገረን የሚል ጥቂት የእግዚአብሔር ሰው ይኖራል። ስለዚኽም ሔሮድስ ከዮሐንስ አድናቆት የሚፈጥረውን ስብከት መስማት ይፈልግ ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ ግን ሌላውን ነገር ትቶ ወደ ሔሮድስ ሕሊና ዓላማ አድርጎ አስተማረ።
የትምህርት ዓላማው ሰውን ማሳቅ ማስደሰት አይደለማ ። ወደ ሕሊና ጓዳ መግባት ይጠይቃል። ዛሬ ዛሬ ስብከቱም ትምህርቱም ሰው የሚወደውን ጊዜ የሚወልደውን ብቻ ሆኗል። እነ አንቶኔን ለማስደሰት አልያ መድረክ ላይ ለመሞጋገስ ብቻ ይመስላል። የሰውን ሕሊና ምንም ሳያገኙ ሲያስጨበጭቡ ያመሻሉ።
ሔሮድስ በዮሐንስ ስብከት አልተደሰተም። ዮሐንስ በሔሮድስ መሞገስን ፈልጎ ቢሆን ኖሮ የወንድሙን ሚስት ማግባት ክፋት መሆኑን መናገር ባላስፈለገው ነበር። ነገር ግን ሥራው እግዚአብሔርን ማስደሰት ብቻ ስለነበር ለሔሮድስ ነፍስ አስቦ ገሰጸው። ስለዚህ ሳይፈራ እውነቱን ገለጸ። “ዮሐንስ፦ እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና ” ማቴ 14:4
ሔሮድያዳ ወዲያው የሔሮድስን ልብ ይዛ ስለ ነበር ወደ ወኅኒ አስጋዘችው። ዮሐንስ ታሰረ ቃሎቹ ግን አልታሰሩም ነበር። ድምጹ ዝም ቢል እንኳ በሕሊና ይናገራል።
ዮሐንስ ታስሮ ብዙ ወራት ቆየ። ከደቀ መዛሙርቱ ጠርቶ ሁለቱን ወደ ኢየሱስ ላካቸው። “ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ወደ እርሱ ጠርቶ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ” በመሲሁ ላይ የነበረው እምነት ታላቅ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ፊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዮሐንስን ክብር በመግለጥ ተናገረ።
ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስክሮ ነበር አሁን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዮሐንስ መሰከረ። ጌታችንም ምን ልታዩ ወጣችሁ ብሎ ጠየቀ። የሕዝቡ ስህተት ለማየት ብቻ መምጣት ነበር። ዛሬም በቤተ ክርስቲያንም የምናየው ከዚህ የተለየ አይደለም የሚታይ ተአምር፣ የሚለፈልፍ ጋኔን ለማየት ተኮልኩሎ ጸሐይ ሲመታው ይውላል። አዲስ ሰባኪ መጣ ሲሉት ግር ይላል። በማግስቱ የለም። በቃ ማየት ነው ፍላጎቱ።
እግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የመጡ እየመሰሉ የፈለጉትን ድንቅ ነገር ለማየት ብቻ ነበር። ለመስማት ሳይሆን ለማየት ሔዱ። ዮሐንስ በሕዝብ አሳብ አልሔደም ሳይፈራ ያስተምር ነበር። የምትከተለው እውነት ከሆነ የሰው ግርግር አያስደንቅህ። እንደ አብርሐም በመስመርህ ላይ ሰዎች ባይሔዱም አንተ ያመንከውን እውነት ብቻ ተከተል። ሰዎች ደጋፊ በሞላበት ማጨብጨብ ይሻሉ።
ዮሐንስ በነገሥታት ቤት መኖር ሲችል ምድረበዳ ኖረ። ከነቢይ የሚበልጥ ነቢይ ነበር። የእርሱ ትልቅነት በሰማያዊ ደረጃው ነው። የርሱ ትልቁ ሥራው የእግዚአብሔርን በግ ለዓለም ማስታወቅ ነበር።
ሔሮድስ ልደቱ ሲከበር መኳንንቶቹ ተሰበሰቡ ሔሮድያዳ በዘፈን አሰደሰተችው። የፈለገችውን እንደሚሰጣት ጠየቃት እናቷን አማከረች። ዮሐንስ የተናገረው አልተረሳትም እና እርሱን በማስገደል ሕሊናዋ የሚያርፍ መሰላት። “እርስዋም በእናትዋ ተመክራ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚኽ በወጭት ስጠኝ አለችው” ማቴ 14:8 ። ሰው የሚያርፈው የተጣላውን በመታረቅ የበደለውን በመካስ ወደ እውነት በመምጣት እንጂ ራሱን በማታለል እውነትን አርቆ ስለደበቃት አይደለም።
የዮሐንስን አንገት ለመነች። ሔሮድስ የሰው ይሉኝታን ፈርቶ በመጠጥ ኃይል ተይዞ ዮሐንስን አስገደለው። የጌታን መንገድ አዘጋጅ ገደለ "ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው” ከዚያ በኋላ ሐሮድስ ፍርሐት አስጨነቀው። ሔሮድስ የጌታችንን ዝና ሲሰማ ዮሐንስ ከሞት ተነስቷል አለ። ነገር ግን ፈሪሳዊ ስለሆነ በሙታን ትንሳኤ አያምንም ነበር። ይሁን እንጂ ሕሊናውን ፈራ። ምክንያቱም ያስገደለው ራሱ ነበር። እርሱን ለመበቀል የዮሐንስ መንፈስ ተመልሶ የመጣ መሰለው።
በደለኝነት መንፈስ የተሞላ አዕምሮ የተለያዩ አላስፈላጊ ፍርሃቶች ይኖሩታል።” ኃጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል” ምሳ.28:1 ጌታችንንን ሊያየው ይመኝ ነበር። ነገር ግን ያየው በመጨረሻ ሰዓት ነው። ሊሰማው ቢወድ እንዳይገደል ቢፈልግም ላደረገው ክፋቱ ንሰሐም አልገባ፣ ከማስገደል አላመለጠም።
4.0K viewsወሰንየለው ባህሩ, 11:13