2022-09-17 17:33:37
ተለቀቀ
የሞት መንገድ
ይሄን ርዕስ ለማንሳት ምክንያት የሆነን ዛሬ በዘመናችን ወደ ሞት ጎዳና የሚወስዱንና ፍጻሜያቸው ሞት የሆነውን፥ ብዙዎችን በሠይጣን አሰራር ውስጥ የከተተ፥ ብዙዎችን የሠይጣን ባርያ አድርጎ እና የእግሩ መረገጫ እንዲሆኑ ምክንያት የሆነውን የእርኩሳን መናፍስት አሠራር ለማጋለጥ ስለወደድን ነው። ይሄውም ጥንቆላ ወይም አስማት ይባላል። ዛሬ በዘመናችን በተለያየ መንገድ ትውልዱን ከሰይጣን ጋር የማቆራኘት ተግባራት እየተመለከትን ነው።
ሠይጣን የኔ በሚላቸው ሰዎች አማካኝነት በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ እና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ የተወለዱትን ሳይቀር ለራሱ ባርያ እያደረገ በተለያየ ዘመኑን በዋጀ መንገድ መጥቷል። በተለይም እራሳቸውን "መሪጌታ" "ደብተራ" እና ሌላም መጠሪያ ስም እየጠሩ በቴሌግራም እና በፌስቡክ እንዲሁም በሌላ ማኅበራዊ ሚድያዎችን በመጠቀም ለራሳቸው ገንዘብን ለሰይጣን የክርስቶስ አካል የሆነውን ምእመን ሲገብሩ እና ሲያስገብሩ ይባስ ብለውም ሲያጭበረብሩ በተደጋጋሚ እናስተውላለን።
በዘመናችን ለዘመኑ ትውልድ እንዲመጥን ተደርጎ እየቀረበ ያለው የእርኩሰት አሰራር የሆነው ጥንቆላ እና አስማት በቤተክርስቲያንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዘ እና በእግዚአብሔር ዘንድም የተጠላ የሞትና የጭለማ መንገድ ነው። ዲያቢሎስን የሚከተል ማንኛውም አካል ፍጻሜው ጭለማና ሞት እንደሆነ ይታወቃል።
የጥንቆላ ተግባርን ዛሬ የተጀመረ አይደለም ።
ጥንቆላ(ጠንቋዮች) በተለያየ መንገዶች የሚጠነቁሉ እግዚአብሔር ባልፈቀደው መንገድ ኃይልን፥ ሥልጣንን፥ ድኅነትን እና ፈውስን ሀብትና ነብረትን ሞገስና ክብርን በመፈለግ የሚሠራ ተግባር ነው።የጥንቆላ ተግባር ዛሬ በዘመናችን የጀመረ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ የነበረ ተግባር ነው። እንዲሁም ለነገሥታት አማካሪ የነበሩ ጠንቋዮች ነበሩ። (ዘጸ 7፥8 - 12, ኢሳ 19 ፥ 3, ዳን 2፥2)
ጥንቆላ በእስራኤላውያን ዘንድ በተለይም በከነኣን ምድር ምዋርተኛ፥ ሞራ ገላጭ፥ አስማተኛ፥ መተተኛ፥ በድግምት የሚጠነቁሉ መናፍስት ጠሪዎች ሙታን ሳቢዎች ነበሩ። እነዚህ ተግባራት የተለያዩ የእርኩሳን መናፍስትን ህቡእ ስሞችን በመጥራት፥ እንስሳትን በመሰዋት እና በሌሎች አስከፊ ተግባራት ከሠይጣን ጋር ቃል ኪዳን ያላቸው ሌሎችንም የቃል ኪዳኑ ተካፋይ በማድረግ የሰይጣን ባርያ የሚያደርጉ ናቸው።
✞ የችግራችን መፍትሄ ማን ነው ።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከሆነ ለየትኛውም ችግራችን እና መከራችን ሰይጣን መፍትሔ መሆን እንደማይችል፥ ጠንቋዮች እና ሟርተኞች አማራጭ ሊሆኑን እንደማይገባ አማራጫችንና ምርጫችን እጣ ፈንታችን እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ይነግረናል። "እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኃጢአት የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ ስለጠየቀ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ ስለዚህ ገደለው።"(1ዜና 10፥ 13) ስለዚህ የመናፍስት ጠሪዎችን መስማት አስማተኞችን እና ጠንቋዮችን መጠየቀ እንደ ሳኦል ከእግዚአብሔር ተለይተን የሞት ተገዥዎች ሆነን በሞት ጥላ ስር የሚጥለን የሞት መንገድ ነው። ስለሁሉም ነገር መፍትሔዎ የሚገኘው ከእግዚአብሔር እና የእርሱ ከሆኑት ከቅዱሳኑ እጅ እና ደጅ ስለሆነ ሁልጊዜ እግዚአብሔር በጾም በጸሎት ደጅ መጥናት መጠየቅ ይገባል እንጂ ከሕይወት ጎዳና ለይቶ ወደ ሞት የሚወስደውን የዲያቢሎስን መንገድ መከተል አይገባም።
ማንኛውም ክርስትያን እራሱ ከእግዚአብሔር ከሚለዩት ነገሮች ፈጽሞ መራቅ አለበት መልካቸውን ቀይረው በዘመናዊ መልክ ማስታወቂያ እያስነገሩ በስመ ደብተራና የባሕል መድኃኒት ቀማሚ እራሳቸውን ሸፍነው የሰይጣንን እቅድ የሚተገብሩ የሰይጣን ሰራተኞቹ እራሳችን ልንጠብቅ ልናድን ይገባል።
✞ እናስተውል ✞
እነዚህ አስማተኞች በእግዚአብሔር የማያምንኑ ነገር ግን "ደብተራ" በሚል ስም የሚነግዱ የሰይጣን ተላላኪዎች ናቸው። በእግዚአብሔር የሚያምኑ ቢሆን ኖሮ በሐዋርያት ሥራ 19 ፥ 19 እንደምናገኛቸው በቀድሞ ሕይወታቸው ጠንቋዮች የነበሩ ካመኑ በኋላ ግን ያን ክፉ የጥንቆላ ሥራ የሚሰሩበት የነበረውን መጽሐፋቸውን ያቃጥሉት ነበር። "ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ።"
ከእግዚአብሔር መንግስት የሚለይ ተግባር ።
መጠንቆልና ማስጠንቆል ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለይ ተግባር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይነግረናል። ሐዋርያው በገላትያ መልእክት 5፥20 ላይ ከዘረዘራቸው የሥጋ ሥራዎች መካከል የተዘረዘሩት መዋርት አንዱ የጥንቆላ መንገድ ነው። የሥጋ ሥራ የሆነውን መዋርትን የሚያደርግ መንፈሳዊ የሆነችውን የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም።
እንዲሁም ባለራእዩ ቅዱስ ዮሐንስ አስማተኞች እና ጠንቋዮች ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ እንዳሉ በራእይ ተመልክቶ ሲነግረን እንዲህ ይላል "ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።" (ራእይ 22 : 15)
እንዲሁም እንዲህ ያሉ ሰዎች በሕይወታችን በጉዟችን ከእኛ መካከል እንዳይኖሩ እግዚአብሔር ሲናገር እንዲህ ይላል "ወንድ ልጁን ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥ አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኵሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል።" (ዘዳግም 18 : 10 -12)
እንዲሁም አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ባለ የሰይጣን ሥራ ውስጥ እንዳንሳተፍ ስያዘን "አስማት አትሥሩ" (ዘሌ 19፥26) ይለናል። ስለዚህ እኛም ከእንዲህ አይነቱ አሰራር እራሳችንን ልናርቅ የገባንም በንስሐ እራሳችን ልናድስ እና ወደ እግዚአብሔር መንገድ ወደ ሕይወት መንገድ ልንመለስ ይገባል። ዛሬ በዘመናችን እኛን መስለው ብዙዎች ትውልዱን የሰይጣን ባርያና ተገዢ እንጂሆን በማድረግ ለኪሳቸው ገንዘብ የሚሰበስቡ የጥልቁ መንፈስ አገልጋዮች በቴሌግራም እና በፌስቡክ ብዙዎችን እያታለሉ ይገኛል። ከእንደዚህ አይነቱ የሰይጣን አሰራር ርቀን በአንዱ በእግዚአብሔር ብቻ እና ብቻ ልናምን እና ልንታመን ይገባል። እንዲሁም መጽሐፈ ፈውስ፥ መፍትሔ ሥራይ እና ሌሎች ጠርተን የማንጨርሳቸው በርካታ የጥንቆላ መጽሐፍት በማሳተም ሠይጣናዊ አሰራርን የሚያስፋፉ ትውልዱን የሰይጣን ተላላኪ የሚያደርጉ ለሚመጣው የአውሬው መንፈስ መንገድ ጠራጊዎች በሊቃውንት እና በደብተራ ስም የጥልቁን መንፈስ የሚያታልሉ፥ ከቤተክርስቲያን እና ከእግዚአብሔር ጋር የተጣሉ፥ የማያምኑ የሰይጣን ባርያዎችን ልናውቅባቸው እና ልንጠነቀቅ እራሳችንን እና በዙርያችን ያሉትን ልናድናቸው ልንጠብቃቸው ይገባል። ምክንያቱም መንገዱ የሞት መንገድ ነውና።
"ሰው ወይም ሴት መናፍስትን ቢጠሩ ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ ፈጽመው ይገደሉ፤ በድንጋይ ይውገሩአቸው፤ ደማቸው በላያቸው ነው።" (ዘሌ 20 : 27)
(መምሕር ዲያቆን ወሰን የለው በሃሩ )
SARE SARE
https://t.me/zdfitsumkebe
https://t.me/zdfitsumkebe
https://t.me/zdfitsumkebe
3.9K views✞£iŧsûm✞, edited 14:33